Sunday, September 15, 2013

ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔዶም ገነት አስወጣው፡፡



አዳን ከኤዶም ገነት ልምን ተባረረ
ብዙዎች አዳም ከኤዶም ገነት የተባረረው እፀ በለስን ስለበላ፤ህግ ስላፈረሰ፤አትብላ የተባለውን ስለበላ፤ የእግዚብሔርን ትእዛዝ ቸል ስላለ የመሳሰሉ መልሶችን ሰተውኛል፡፡
ይህንን ትምህርት ሁላችንም መጀመሪያ የምንሰማው የምንማረው እውነት ነው ማንም ቢጠየቅ መጀመሪያ የሚመልሰው ይህንኑ ነው፡፡ በእርግጥ መጽሐፉ አዳም ስለተባረረበት ነገር ምን ይላል፡፡ አዳምን ከኤዶም ገነት እንዲባረር ያደረገው ፍቅር ነው ብንልስ አዎ አዳምን ከኤዶም ገነት እንዲባረር ያደረገው በእግዚአብሔር በመፈለጉ እና በመፈቀሩ ነው፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ አላማ የእግዚአብሔርን ፍቅር መናገር ነው፡፡ ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምረን እስከ የዮሐንስ ራዕይ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን ብናነበው የሚነግረን የእግዚአብሔርን ፍቅር ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ፍቅሩን የገለጸበት ማህደሩ ነው መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር የፍቅሩ መግለጫ ክታቡ ነው የሚሉት፡፡ ሁላችንም በየእለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ያለብን እግዚአብሔር ምን ያክል እደሚወደን እንድንረዳና እንድናውቅ ጭምር ነው፡፡ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚውደን ለመመስከር መጽሐፍ ቅዱስን ማነበብ ይገባናል፡፡ ፍቅር የሚለው ቃል እንደወረደ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ቦታዎች ላይ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡
በኦሪት ዘፍጥረት 34፤3

ልቡናውም በያዕቆብ ልጅ በዲና ፍቅር ተነደፈ፥ ብላቴናይቱንም ወደዳት፥ልብዋንም ደስ በሚያሰኛት ነገር ተናገራት። ከሚለው የዘፍጥረት መጽሐፍ እሰከ ትንቢተ ሆሴዕ ምዕራፍ 11፤4


በሰው ገመድ በፍቅርም እስራት ሳብኋቸው ለእነርሱም ቀምበርን ከጫንቃቸው ላይ እንደሚያነሣ ሆንሁ፥ ድርቆሽም ጣልሁላቸው። እሰከሚለው የብሉይ ከዳን መጽሐፍ 40 የሚያክ ቦታዎች ሲጠቀስ በአዲስ ኪዳን ደሞ



ከማቴዎስ ወንጌል 24፤12

ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች።ከሚለው ጥቅስ ተነስተን

የዮሐንስ ራእይ 2፤19




ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ።





እስከሚለው  የዮሐንስ ራእይ የትንቢት መጽሐፍ ድረስ 94 ቦታዎች ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ ይሁንና እነዚህ ቃላት በቀጥታ ከሚገልጹልን ፍቅር ይልቅ እግዚአብሔር በማድረጉና በሠራቸው ሥራዎች የገለጣቸው ፍቅሮች ብዙዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው አዳምን ከኤዶም ገነት ማስወጣቱ ነው፡፡ ምናልባት እንዴት ተድላና ደስታ ከሞላበት የእግዚአብሔርን ድምጽ እየሰማ ከሚያመሰግንበት ከኤዶም ገነት እያስወጣው እንዴት ፍቅሩን አሳየ የምንል ሰዎች እንኖር ይሆናል፡፡ አዳም ከገነት ስለተባረረበት ትክክለኛ ምክንያን መጽሐፍ ቅዱሱ እንዲህ ይላል፡፡ ኦሪት ዘፍጥረት 3፤22

እግዚአብሔር አምላክም አለ። እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፥ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔዶም ገነት አስወጣው፡፡
ስለዚህ ተብሎ የተጠቀሰው አዳም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር ነው፡፡ ስለዚህ አዳን ከገነት ለመባረሩ እፀ በለስን መብላቱ ህግ ማፍረሱ ምክንያት ይሁን እንጂ ከገነት የተባረረው ትክክለኛ ምክንያት ግን ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ እና ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር ነው፡፡
በዚህ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔር ፍቅር ማየት ቀላል ነው፡፡ አዳም ህግ ማፍረስ አለመታዘዝ የእግዚአብሔርን ጸጋ መናቅ በውስጡ እያለ በአጠቃላይ በሀጢአት ወድቆ ፤ተይዞ ለዘላለም የምታስኖረዉን እፀ ህይወት ቀጥፎ ቢበላ ኖሮ ኑሮው ሁሉ እንደ አጋንንት/ሰይጣን/ ይሆን ነበር፡፡ ሰይጣን ህያው ነው ለዘለላለምም መኖር ይችላል፡፡ የአዳምም እጣ ይህ እዳይሆን እግዚአብሔር የአዳምን አለመታዘዝና ሀጢአት ከውስጡ አጥቦ አሶግዶ ንፃህ ባህሪዉን ከመለሰለት በኋላ ለዘለአለም የሚያኖረውን የህወት እንጀራ ስጋውን ቆርሶ እስኪሰጠው ድረስ ከገነት ገለል አደረገው፡፡ ለዚህም ነው የክርስቶስን ስጋ መልበስና መምጣት ተንተርሶ ዮሐንስ በመልእክቱ ሲጽፍ 
በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ያለው 1 ዮሐንስ መልእክት 4፤9 የሚገለጥ ያለና የነበረ ነገር ግን የተሸፈነ እውነት ነው፡፡ ይህም አዳምን ከገነት ገለል ያደረገበት እውነተኛ ፍቅር ልጁ በመወለዱ ተገለጠ ይለናል፡፡
ወስብሀት ለእግዚአብሔር
የእግዚአብሔር ፍቅሩ አይለየን
መ/ር ሰሎሞን ፋንቱ
መልስ ለሰጣችሁኝ ለበረታችሁኝ ለመልካም ምኞታችሁ ታላቅ ክብር አለኝ

No comments:

Post a Comment