የእገሌ
እናት
በዚህ
በሰሜን ሸዋ ክልል በተለይም ይፋት አካባቢ ባል ሚስቱን ሲጠራት በስሟ እገሊትዬ አይላትም የእገሌ እናት ወይም የእገሊት እናት ነው
ጥሪው፡፡
በእርግጥ
ባሎች ሚሰቶቻቸውን ሲጠሩ ለምን እንደዚህ እንደሚሉ የተጠና ነገር ባይኖረኝም አንድ አባወራ ግን ሰው ፊት እገሊትዬ ብሎ ጠርቶ ብዙ
ጊዜ እንዳፈረበት ሰምቻለሁ፡፡ እኔ ላነሣ የፈለግኩት ሀሳብ እነዚህ የጠቀስናቸው አካባቢ ሰዎች ሚስቶቻቸውን ስለሚጠሩበት ሀሳብ አይደለም፡፡
መነሻ ቃሉን ይዤ በሌላ መንገድ ላየው ነው እንጂ፡፡ ጋብቻ በሁለት ተፈላላጊ ጾታዎች መካከል የሚደረግ እና በማንኛውም ኅብረተሰብ
የተፈቀደና የተከበረ ስርዓት ነው፡፡
የመሠረተውም
እግዚአብሔር ነው፡፡ ዘፍ 2፤18-25 ይህንንም የጋብቻ ስርዓት ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋለ ሥጋዌው በቃሉ አጽድቆታል፡፡ ማቴ.19፤3-6
እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን እንዲህ ሰው አይለየው በማለት ፡፡ ክፋት ሁሉ በሰው እና ለሰው የመጣ በመሆኑ ጋብቻችንም እንዲህ
ያለው የሰው ክፋት እንዳያገኘው በማጠር አፀደቀው፡፡
ይህም
ማለት እግዚአብሔር የጋብቻን ስርዓት ሠራ አፀደቀውም ስለዚህ ጋብቻም ክቡር ሆነ መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንፁህ ይሁን፡፡
ዕብ.13፤4 ፡፡ ነገር ግን ዛሬ እንደምናየው ይህንን እግዚአብሔር የባረከውን ጋብቻ ሰው አክብሮት አናይም በሚደንቅ ሁኔታ በአዳራሽ
ፊት ለፊት ገብተው ጋብቻ የፈጸሙ ሰዎች እዚያው አዳራሽ ውስጥ ፍቺያቸውን ፈጽመው በጓሮ የሚወጡበት አገር እየበዛ ነው፡፡
ከዚህም
በላይ ይህንን ክቡር ጋብቻ የሚረሱ የሚዘነጉ ሚስቶች ባሎቻቸውን፤
ባሎችም ሚስቶቻቸው የሚያታልበት ከዚህም የተነሳ በሥጋም የሚጎዱበት እንደ ሰደድ እሳት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ዓለምን
እያጥለቀለቀ ባለ በሽታ የሚሞቱበት ዜና አሁን አሁን ተዋሕዶናልና አዲስ አይደለም፡፡
ስለዚህ
ቤተ ክርስቲያን በማኅበረሰቡ መካከል ልትሠራ ከሚገባቸው ሥራዎች መካከል የጋብቻን ጤና መጠበቅ ከፍተኛውን ድርሻ ሊይዝ ይገባል፡፡
ጋብቻን ለማጽናት መምህራን፤ ሊቃውንት እንዲሁም ተመራማሪዎች ብዙ ይመክራሉ፤ እስኪ በዚህ ጽሑፍም ጥቂት እንበል፡፡
መጀመሪያ
ጋብቻ በባህሪው ንጹኅ የሆነ አምላክ በንጽሕና የመሰረተው መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ መቼም ቢሆን እግዚአብሔር የማይጠቅመንን
ሠርቶልን አያውቅም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ስላከበረው ልናከብረው ይገባል፡፡
ሁለተኛው
መቻቻል ነው የተለያየ አመለካከት ካለው ቤተሰብ የሚገኙ በተለያየ የአስተዳደግ ስነምግባር ውስጥ ያለፉ ወይም የሚኖሩ ሁለት ተፈላላጊ ፆታዎች ናቸው አንድነትን የሚመሰርቱት፡፡ ስለዚህ ባል የሚስቱን
ሚስትም የባሏን አስተዳደግ፣ አመለካከት ማጥናትና ማክበር ይገባል፡፡ በተጨማሪም ትዳር ባልና ሚስት ወይም ተጋቢዎች ከሁለት ወንዝ
ለአንድ ትዳር/ኑሮ/ የሚቀዱበት ሕይወት እንጂ ከአንድ ወንዝ የሚቀዱበት አይደለም፡፡ ይህንንም እግዚአብሔር በድንቅ አሠራሩ አደረገ
ለዚህም ነው ዝምተኛዋ ለፍላፊ፣ ቸሯ ቆጣቢ፣ ትዕግሰተኛው ግልፍተኛዋን ሲያገባ እናያለን ይህ እግዚአብሔር ዓለምን ለመቀደስ የሚጠቀምበት
ጥበቡ ነው፡፡ እስኪ እናስብ እግዚአብሔር ጨዋዎቹን ቢያጋባ እኛ ባለጌዎቹ የት እንገባ ነበር፤ ዝምተኞቹን ቢያጋባ እኛ ለፍላፊዎቹን
ምን ይውጠን ነበር፤ ለጋሶቹን ቢያጋባ እኛ ቆንቋኖቹ ከማን ጋር እንድር ነበር፤ ማስተዋል ይገባል:: ማጥናት ስንል ለምሳሌ አስተዳደግንና
የቤተሰብን ተፅእኖ ብንመለከት እቤት ሲገባ የጣፈጠ ምግብ እየሠራች የምታበላውን ባለቤቱን ምግብሽ በጣም ይጣፍጣል እንዲህ መጨነቅሽ
ለእኔ ያለሽን ክብር ያመለክታል እያለ ሚስቱን በሚያሞግስ ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ልጅ/ ነገ ሚስት/ ለሷ የፍቅር መገለጫው ለባሏ
የጣፈጠ ምግብ ማዘጋጀት ሊሆን ይችላል ምክንያቱም ከቤተሰቦቿ /እናቷ/ ያየችው ይህንን ነውና፡፡
በተቃራኒው
ባሏ አባቱ ሲገባ እናቱን የሚላፋት የሚዳራት ስለሚበላው ነገር የማይጨነቅ ነገር ግን መተሸሸት ፍቅር መግለጫው ሲያደርግ ሲያይ ያደገ
ወጣት የነገ ባል ለእሱ የፍቅር መግለጫው ሚስቱን መዳራት መላፋት ነው ብሎ አምኖ ያድጋል፡፡ እስኪ እነዚህን ሰዎች በእኛው ስርዓት
እናጋባቸው እሷ ከቤት እንደተማረችው ከሥራ ወጥታ ደክማ መጥታ የጣፈጠ ምግብ ስታዘጋጅ ትውላለች ባሏ እንዲደሰት፤ ባል ከሥራ እንደገባ
ለተሠራው ምግብ ደንታ ሳይኖረው ካልተሻሸሁሽ፤ ካልተላፋሁሽ ቢል እንደተማረው ፍቅሩን መግለጹ ነው፤ እሷም ለሱ ክብር እጅግ ደክሜ
ተጨንቄ የሠራሁትን ምግብ ቀምሶልኝ በልቶልኝ ይጣፍጣል ሳይለኝ እንዴት
ይወደኛል ስትል ባልም በበኩሉ ስጠጋት የምትሸሸው እኔን ለመሸሽ ማዕድቤት የምትወተፈው ባትወደኝ ነው በማለት ለመቀራረብ ያሰቡት
ዘዴ ለልዩነት ትልቅ በር የሚሆንበት አጋጣሚው ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ ስለዚህ ትዳር እንዲጸና ቆም ብሎ ያደገበት ስርዓት፤ ያደገችበት አስተዳደግ
ምንድነው ብሎ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ከዚህም
በዘለለ ቤተሰቦቿጋ፤ ቤተሰቦቹጋ ሲሆኑ በነጻነት መልቀቅና የአኗኗር ስርዓቷን ስርዓቱን ማየት በቀላሉ ለመግባባት ያደርሳል፡፡ ሌላው
በእምነት መጽናት ነው፡፡ እግዚአብሔርን እንዲወድ እንድትወድ መመራራት፤ መመካከር ያስፈልጋል፡፡ ለእግዚአብሔር ካልሆነ ላንቺ አይሆንም፡፡
እግዚአብሔርን በራሱ እንጂ በአንቺ ሊወደው ወይም በእሷ ልትወደው
አይገባም፡፡ ነገሩ እንዲህ ከሆነ በአንቺ የወደደውን እግዚአብሔርን የጠላሽ ዕለት ይተወዋል፡፡ የተወችህ እለት እግዚአብሔርን አብረህ
ልትተወው አይገባምና፡፡ በተጨማሪም ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮች ሰዎች ከተጋቡ በኋላ ከመጋባታቸው በፊት የነበረውን መቀራረብ መተሳሰን
አብሮ መዝናናት መተዋቸው ነው፡፡ እንደውም በአንድ ወቅት ሁል ጊዜ አብረው በመታየታቸው ያስደንቁ የነበሩ ፍቅረኛሞች አንድ ቀን
ልጁ ብቻውን ይገኝና ምነው ምን ሆናችሁ ሁሌ አብራችሁ ስትታዩ ታምሩ ነበር አሁን የት ሄደችና ብቻህን ሆንክ ብቻህ አየንህ ቢሉት
አይ እሷንማ አገባኋት እኮ ብሎ ግርምት ፈጥሯል አሉ፡፡
መዋደድና
መፋቀር እኮ ወደ ጋብቻ የሚያደርስ ድልድይ ብቻ አይደለም በዘመናቸው ሙሉ የሚሰንቁት የሕይወት ስንቅ እንጂ፡፡ ይህ ፍቅር ታዲያ
አፍ ላይ ብቻ የሚቀር ከሆነ ጉዳቱ ያመዝናል መተማመንን ያሳጣል የመከራ ሁሉ መጀመሪያ አለመተማመን ነው ለዚያውም ለ80 ሚስቱ፡፡
በነገራችን ላይ የ80 ሚስት ማለት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል የእድሜ ልክ ሚስት ወይም ባል ማለት ነው፡፡ የሰው እድሜ 70 ቢበረታም
80 ዓመት ነው፡፡ መዝ. 89፤ 10 ይላልና፡፡ ታዲያ እንዴት ለ80 ዓመት ከእግዚአብሔር የተቀበለውን ክቡር ስጦታ ሳይታመንለት
ይቀራል? ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ይሁንና በዘመናችን እንደምናየው የኮንትራት ጋብቻ በመሰለ ኑሮ በዚች አጭር እድሜ ሲሸነጋገሉ የምናያቸው
ብዙ ናቸው፡፡ እንትናዬ፣ ውርዬ፣ ወናዬ እየተባባሉ፡፡
የባል
ዘመድ በምኑ አመድ እየተባለም ብዙ ትዳርን ወላጅ ጓደኛ ቤተሰብ ቤተ ዘመድ እየገባበት ለችግር ሲወድቅም ይታያል፡፡
እንዲህ
አይነቱን ችግር በመመካር መፍታት ያስፈልጋል መጀመሪያ የባል ዘመድ ሲባል ከቀደሙት ጀምሮ እሰከሚመጡት ነውና ዛሬ የምትፈርጂ ሚስት
ነገ የባል እናት/ዘመድ/ መሆንሽን መዘንጋት የለብሽም ብድር እንዳታቆዪ፡፡
የባል
ዘመድ ይፈጥራሉ የሚባሉት ችግር የሚመነጨው ከክፋት እንዳልሆነ ይሰማኛል፡፡ ችግሮቹ ሊነሱ የሚችሉት በብዙ ምንገዶች ቢሆኑም ጥቂቶቹ
ግን እንዲህ ይመስሉኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ወንድ ለቤቱ ክብር ኩራት ነው ስለዚህ ማንም ሰው ክብሩንና ኩራቱን በቀላሉ አሳልፎ አይሰጥም፡፡
ቢሰጥም ከዚህም የተነሳ ቤተሰቦቹ እህቶቹ የሚያደርጉለትን እንክብካቤ ሚስት እንድታደርግለት ይፈልጋሉ፡፡ ወንድ ልጅ በቤተሰቦቹ ቤት
ኩሩ ነው ቀብራራ ነው ስራ አይሰራል ምግብ እንዲያበስል አይደለም ኩሽና እንዲጠጋ አይፈቀድለትም ልብሱ ካልሲው ይታጠብለታል በአጠቃላይ
ወንድ ልጅ በቤቱ ለንጉስ የሚደረግለት እንክብካቤ እየተደረገለት ያድጋል፡፡ ስለዚህም ቤተሰቦቹ ይህንን ሁሉ እክብካቤ ሚስቱ እንድታደርግለት ይጠብቃሉ፡፡ ሰለዚህም እናት ወይም እህት ወንድሟ ካልሲ
ሲያጥብ ያገኙት እንደሆን ውድ ሚስቱን አካሉን ሊረዳ ማማሰያ ይዞ ያዩት እንደሆነ ጸብ ይቀሰቀሳል ይዶለትባታል፡፡ አንዳንድ ግዜም
ልጃቸው ወንድማቸው ማን እንደሆነ እንዴት እንደታደለች ሊያስረዱሽ ይፈልጉ ይሆናል ታዲያ እነሱ የሚሉትን ማንነት በሚስት አይንሽ
ለማግኘት ከሞከርሽ ነገር ተበላሸ የአንቺ አይንና የቤተሰቦቹ አይን ወንድን አኩል እንደማይመለከቱት ጠንቅቀሽ ማወቅ አለብሽ፡፡ ብዙ
እህቶቼ ለቤተሰቦቹ እናንተ የነገራችሁኝን እከሌን ላገኘው አልቻኩም እያሉ ሲቸገሩ አውቃለሁ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ለገብርዬ አንተ ብታከብረኝ
ብትፈራኝ ቀበቶየን አጥልቄ ዝናሬን ታጥቄ በንግስና ወንበር ተቀምጬ ምንትዋብ በሰፌድ ልምታህ ብትለኝ ግን ዝናሬን አውልቄ ቀበቶዬን
ፈትቼ ራቁቴን ስለምታውቀኝ ነው ያለችውን አትዘንጊ፡፡ አንተም በቤትህ ታገኝ የነበረውን እክብካቤ ከሚስትህ የምትጠብቅ ከሆነ መሳሳትህ
አይቀርም፡፡ ስለዚህ ቤተሰቦችህ ሌሎች ትዳርህና ህይወትህ ሌላ መሆኑን በመረዳት ለትዳርህ ታማኝ ልትሆን ትዳርህን ልታከብር ግድ
ይልሃል፡፡ በጋብቻ አጋርነት የምናገኘው የትዳር ጓደኛችን ከእግዚአብሔር የሚሰጠን እሱ ብቻ የሚችለን እሷ ብቻ ልትችለን የምትችል
ስጦታችን ነው ይህንን አክብረን ከያዝን ሌላ ስጦታ ይጨመርልናል፡፡ ስህንን አክብረን ካያዝን ግን. . . በትንሹ ያልታመነ በብዙ
አይሾምም
እናስተውል
እግዚአብሔር አክብሮ በሰጠን ጋብቻ የምናገኘውን አጋር እንደ ሣራና አብርሃም ጌታዬ እመቤቴ መባባል እያለ የእገሌ እናትንስ ምን
አመጣው ሰዎች በጋብቻ ሲኖሩ መመካከር ይቀርናና አቃተኝ፣ መሸከም አልቻልኩም፣ 11ኛው ሰዓት ላይ ደርሻለሁ የሚባሉ ቃላትን እንሰማለን፡፡
ይገርማል! በእርግጥ ተናጋሪው አንተን መሸከም አንቺን መሸከም ሰለቸኝ ካሉ እነሱን ራሳቸውን እግዚአብሔር እንደተሸከማቸው ረስተዋል
ማለት ነው፡፡ እንዲህ የከፋ ወይም የከፋች የትዳር ጓደኛ ሲያጋጥምህ/ሽ እግዚአብሔር ያለአንተ ያለ አንቺ የሚችልልኝ የለም ብሎ
የሰጠን ስጦታ መሆኑን ማወቅና ማመን ያስፈልጋል፡፡ እርሱ እግዚአብሔር ከሰባት ቢሊዮን ህዝብ በላይ ከነፀባዩ ተሸክሞ አንድ ሰው እርዱን ቢለን እንቢ
ማለት ተገቢ ነውን? አይመስለኝም፡፡ አንዳንዴ ያየሁባት ነገር አብሮ አያስኖርም ያየሁበት ነገር እንቅልፍ ነሳኝ የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
እኛ ባየናት ጥቂት ነገር ይህንን ያህል ስንቸገር እግዚአብሔር ያየውን ሁሉ ብናይ ምን እንሆን ነበር ከዚህ ሰውሮናል፡፡ ስለዚህም
ጋብቻን በሚባርክ እግዚአብሔር ታምኖ መኖር ይገባል፡፡፡
አስብበት
የእገሌ አባት
አስቢበት
የእገሌ እናት
ይሕ ጽሑፍ
የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት አንቀጸ ብርሃን በሚል በጥር ወር 2004 ዓ/ም ባሳተመው ጋዜጣ ላይ የጻፍኩት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment