ለማመን ቀላሉ የቱ ነው??
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ ተመዝግቦ የምናገኘው ገና ክርስትና እንጭጭ በነበረበት በዚያ ዘመን
ላይ የተነሱት ተጠራጣሪዎች/መናፍቃን/ እነ አሬዎስ መቅዶንዎስ አውጣኪ ንስጥሮስ እና የመሳሰሉት የመጽሐፍ ቅዲስን እዉነት ሲጠራጠሩ
እጅግ ግራ የገባቸው ጉዳይ የክርስቶስ ማንነት ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሷል ሲባል መለኮትን የተዋሃደ ነው? መለኮትን
የተቀባ ነው? መለኮት ስጋን ውጦታል/ስፖንጅ ውሃን / እንደሚመጠዉ ድንግል ማርያም የሰው እናት ናት የመለኮት እናት ናት? እነሆ
አኔ ባሪያው ነኝ ይሁንልኝ ይደረግልኝ ብላ የመልአኩን ቃል ባመነች ግዜ ቃልን ጽንስ ቀድሞታል ወይስ ጽንስ ቃልን ቀድሞታል? የሚሉና
የመሳሰሉ ግራ የሚያጋቡ ሀሳቦችን እያነሱ የልጇ የመሰወሪያው ማእበል እያማታቸው፤ ከመጠራጠር ክደው ከመካድም አስክደው እንዳጠፉ
እናነባለን፡፡ ይህ ለእኔ አንድ ነገር ይነግረኛል እንኳን አምኖ ለማሳመን ለመካድም እውቀት ያስፈልጋል፡፡
ዛሬ በዘመናችን የምናየው ግን ከዚህ በእጅጉ የራቀ ነው ዛሬ የጥርጥር መጀመሪያው የክህደት
መነሻው ማርያም አታማልድም ማለት ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን አኩርፎ የሚወጣ ሁሉ ማርያም አታማልድም በማለት ይጀምራል መውጣቱን ያውጃል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ማን እንደሆነ ላመነና አመሰግነዋለሁ ለሚል ሰው የክህደቱን መነሻና መለያ
የኢየሱስ እናት እያለ የሚጠራት እና እናትነቷን ያመነውን የማርያምን የምልጃ ሁኔታ ከሆነ ማስተዋል የጎደለው መነሻ ይመስለኛል፡፡
ለመሆኑ መለኮትን በማህጸን ተሸክሞ ከመውለድና እና የወለዱትን ከመለመን የቱ ይበልጣል
አነሳሴ ስለ ድንግል ማርያም ምልጃ መጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሼ መከራከሪያ ለማቅረብ አይደለም መለኮትን
ከማቀፍ ከመውለድ ከማጥባት እና ከማማለድ የትኛው ይቀላል በማለት ፀሐፍቱ ስለ መለኮት የገለፁበትን መንገድ በጥቂቱ ለማየት ነው፡፡
መለኮት ስንል ምን እያልን ነው እግዚአብሔርንስ እንዴት ነው የምንረዳው እስኪ የቤተ ክርስቲያን
ሊቃውንት እግዚአብሔርን ወይም መለኮትን የገለጹበትን እይታ እንመልት፡፡
ቅዱስ ኤጲፋኔዎስ በቅዳሴው እንዲህ ይላል፡፡
እግዚአብሔር በገናናነቱ ገናና ነው፤
በቅድስናውም የተቀደሰ ነው፤
በምስጋናውም የተመሰገነ ነው፤
በክብሩም የከበረ ነው፡፡
እግዚአብሔር ከመቼ ወዲህ የማይሉት ቀዳማዊ ነው፡፡
እስከ ዛሬ የማይሉት ማእከላዊ ነው፤
እስከዚህ የማይሉት ደኃራዊ ነው፡፡
ለአነዋወሩ ጥንት የለውም፤
ለአኳኋኑም ፍጻሜ የለውም፤
ለዘመኑ ቁጥር የለውም፤
ለአመታቱም ልክ ቁጥር የለውም፤
ለውርዝውናው ማርጀት የለበትም፤
ለኃይሉም ጽናት ድካም የለበትም፤
ለመልኩም ጥፋት የለበትም፤
ለፊቱ ብርሃን ጨለማ የለበትም፡፡
ለጥበቡ ባህር ድንበር የለውም፡
ለትዕዛዙም ይቅርታ መስፈርት የለውም፡
ለመንግስቱ ስፋት ዐቅም ልክ የለውም፡
ለአገዛዙም ስፋት ወሰን የለውም፡፡
በህሊና የማያገኙት ሥውር ነው፤
በልቡናም የማይደርሱበት ምጡቅ ነው፤
አንስርት የማይደርሱበት ረጅም ነው፤
ዓሳዎች የማይዋኙበት ጥልቅ ነው፡፡
ከተራሮች ራስ ይልቅ ከፍ ያለ ነው፤
ከባህር ጥልቀት ይልቅ ጥልቅ ነው፤
ነገስታት የማይነሱበት ጽኑ ነው፤
መኳንንት የማይቃወሙት አሸናፊ ነው፡፡
የጥበበኞችን ምክር የሚያጠፋ ጥበበኛ ነው፤
የሚመክሩትን ሰዎች አሳባቸውን የሚያስረሳ ዐዋቂ ነው፤
የጸኑ ልጓሞችን የሚፈታ ኃያል ነው፤
የኃጥአንን ጥርሶች የሚያደቅ የትዕቢተኞችንም ክንድ የሚቀጠቅጥ ብርቱ ነው፡፡
የግብዞችን ፊት የሚያዋርድ ክቡር ነው፡፡
የዝንጉዎችን ብርሃን የሚያርቅ ከሃሊ ነው፡፡
እያለ እግዚአብሔርን ይገልጠዋል እውነትም ነው ይህንን እግዚአብሔር ቅዱስ አባ ህርያቆስ በቅዳሴ
ማርያም ደሞ መለኮት እያለ ይህንን መለኮት ስጋ እንዴት ቻለው እያለ በማድነቅ እንዲህ ይላል፡፡
እግዚአብሔር አብ ንጽህናሽን
ባበ ጊዜ ስሙ ገብርኤል የሚባል ብርሃናዊ መልአኩን ወደ አንቺ ላከ መልአኩም መንፈስ ቅዱስ በላይሽ ይመጣል የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል አለሽ፡፡ ሉቃስ 1፤35
ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ ሳይወሰን ጸነስሽው በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር
በማህጸንሽ ተወሰነ፡፡
መመጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መለኮት በሆድሽ አደረ ፡፡
በምድራዊ እሳት እንመስለው ዘንድ አይገባም ለእሳትስ መጠን አለው ልክም አለው መለኮት ግን
ይህንን ያህላል ይህንንም ይመስላል ሊባል አይቻልም፡፡
ለመለኮት እንደ ፀሐይና እንደ ጨረቃ ክበብ እንደ ሰውም መጠን ያለው አይደለም ፤ ድንቅ ነው
እንጂ የሰው ህሊና የመላእክትም አእምሮ በማይደርስበት በአርያም የሚኖር ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት ወርድና ቁመት ላይና ታች ቀኝና ግራ ያለው አይደለም በሁሉ የመላ ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት የሚዘረጋበትና የሚሰበሰብበት
ያለው አይደለም ግዛቱ ባገሩ ሁሉ ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት በላይ ጠፈር በታችም
መሰረት ያለው አይደለም ጠፈሩ እርሱ መሰረቱ እርሱ ነው እንጂ ፡፡
ለመለኮት ከምድር ከውስጥዋ የሆነውን
ያነሳ ዘንድ ማጎንበስ ራስንም ዝቅ ማድረግ ያለበት አይደለም ለጴጥሮስ እንዳሳየው ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት በሚታይ ገንዘብ በሚወሰንም
ገንዘብ ደረትና ፊት የኋላም ጀርባ ያለው አይደለም በነደ እሳት የተሸፈነ ነው እንጂ ፡፡ ነደ እሳት ግን እርሱ ነው ፡፡ መለኮትስ
ንጹሕና ጽሩይ ብሩህም ነው፡፡
.
.
.
መለኮት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስም ነው፡፡ አንድ አምላክ አንዲት መንግስት አንዲት ሥልጣን
አንዲት አገዛዝ ናቸው ፡፡
ይልና አባ ህርያቆስ ቀጥሎ እጅግ የሚያስደንቀውን መለኮት ሰው የመሆኑን ምስጢር እንዴትስ ይህ
መለኮት ሥጋ ለበሰ እንዴትስ ሥጋን ተዋሃደ እያለ ይጠይቃል፡፡
በእውነትም እጅግ ድንቅ ነው፡፡
አባ ህርያቆስ እንዲህ ይላል የቅድስት ድንግልንም ለሁሉ ድንቅ የሚሆን የፅንሷን ነገር እንዲህ
እያልን እንመርምራት፡፡ ይልና ይጠይቃል፡፡
ድንግል ሆይ እሳተ መለኮት በሆድሽ ባደረ ጊዜ ፊቱ እሳት፤ ልብሱ እሳት፤ ቀሚሱ እሳት ነው
እንደምን አላቃጠለሽ፡፡
ሰባት የእሳት ነበልባል መጋረጃ በሆድሽ ውስጥ ወዴት ተዘጋጀ ወዴትስ ተተከለ ታናሽ ሙሽራ ስትሆኝ፡፡
ከገረድነት ጋር እናትነት እንደምን ያለ ነው ከስፋት ጋር የሆድ መጥበብ እንደ ንብ ያለ ሩካቤ ከቃል ድምጽ የተገኘ ጽንስ ከድንግልና ጋር አንድ የሆነ ሐሊብ፡፡
ይህ መለኮት ስጋ ለብሷልና ሰው ሆኖአልና፤ ይህ ግሩም እና ድንቅ የሆነ አምላክ ሰው ሆኗል
ተገልጧል ሲል እንዲህ ይለዋል፡፡
የማይደፈር ግሩም ነው በእኛ ዘንድ ግን ትሁት ነው፡፡
የማይገኝ ልዑል ነው በእኛ ዘንድ ግን አርአያ ገብርን ነሣ/የባርያን መልክ ይዞ ታየ ተገለጠ/፡፡
የማይዳሰስ እሳት ነው እኛ ግን አየነው ዳሰስነውም ከእርሱ ጋራ በላን ጠጣን፡፡ በማለት 1ኛ
ዮሐንስ መልእክትን ተረጎመው
1ኛ ዮሐ ምዕ 1 ከቁጥር 1-2 እንዲህ ይላል “ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና የሰማነውን በአይናችንም ያየነውን
የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም
የተገለጠውን የዘላለም ህይወት እናወራላእኋለን፤”
አባ ህርያቆስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አባ ኤውስጣጤዎስ እያልን ቅዳሴውን ስነጠቅስ የሚጠሉ እና
ቅር የሚላቸው ቅዱሳኑን ስንጠራ መጽሐፍ ቅዱሱን የምንረሳ የሚመስላቸው ቢኖሩም እንኳን ከላይ ስለ መለኮት የተገለጠውን እውነት የሚቃወም
ማንም ይኖራል ብዬ ተስፋ አላደርም፡፡
እንግዲህ እንዲህ ድንቅ የሆነ መለኮት ሥጋ ሲለብስ የመረጣትን ድንግል ማርያምን ታማልዳለች
አታማልድም ብሎ ከማለት በፊት እሳተ መለኮትን እንዴት አድርጋ ወለደችው ብሎ ማድነቅ አይቀድምምን?
ከዚያስ እሳተ መለኮትን፤ ሰማይና
ምድር የማይችሉትን ፤ መሰረቱ እርሱ ጠፈሩ እርሱ የሆነውን ድንቅ አምላክ፤ የእግዚአብሔር አብ የባህሪይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን
ጸንሶ ከመውለድ አቅፎ ከማጥባት፤ አዝሎ ከመሰደድ እና ከማማለድ ለማመን ቀላሉ የቱ ነው??
.
.
. ከላይ እንዳየነው
ለመለኮት ወርድና ቁመት ላይና ታች ቀኝና ግራ ያለው አይደለም በሁሉ የመላ ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት የሚዘረጋበትና የሚሰበሰብበት
ያለው አይደለም ግዛቱ ባገሩ ሁሉ ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት በላይ ጠፈር በታችም
መሰረት ያለው አይደለም ጠፈሩ እርሱ መሰረቱ እርሱ ነው እንጂ ፡፡
ለመለኮት ከምድር ከውስጥዋ የሆነውን
ያነሳ ዘንድ ማጎንበስ ራስንም ዝቅ ማድረግ ያለበት አይደለም ለጴጥሮስ እንዳሳየው ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት በሚታይ ገንዘብ በሚወሰንም
ገንዘብ ደረትና ፊት የኋላም ጀርባ ያለው አይደለም በነደ እሳት የተሸፈነ ነው እንጂ ፡፡ ነደ እሳት ግን እርሱ ነው ፡፡ መለኮትስ
ንጹሕና ጽሩይ ብሩህም ነው፡፡
ካልን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሉቃስ 1፤19 ላይ “በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል
ነኝ” ማለቱ ምን ማለት ነው ይቖየን

እናንተ እንደ ዳዊት የምትደጋግሙት የቃና ሰርግ እኮ ከመናገር ዉጪ መንም አላረገችም ምክንያቱም እርሷ ሳትሆን ልጇ ነዉ ሁሉን ማረግ የሚችለው ሌላው ደግሞ እሱ ማስታረቅ አይደለም
ReplyDelete