Tuesday, September 9, 2014

የቅርጫት ሥጋ አንሱ ልጅ መሳይ ላኩና ሥጋው አንዳገር ነው ጮማም አለውና ዘመን ሲለወጥ



እሰይ ሰማይ ጠራ
ምድሯ ልታፈራ
ዕፅዋት ሊያብቡ
እንሥሣት ሊጠግቡ
ጉሙም ጠርጎ ሄደ ጭጋጉም ገፈፈ
አዲስ ዘመን መጣ ግዜውም ከነፈ
ደህና ሁን ነጎድጓድ አንተ ዋልክና ደፍ
በቅርብ ላንገናኝ ቃላችንን ላናጥፍ
ብርሃን ተገለጠ
የዘመናት ቅምር በስንዝር በለጠ
አዲስ ሥራ እንጀምር ዘመን ተለወጠ
ደመናው ተነነ
ጢሱ ተበተነ
የፀሐይም ብርሃን ሙቀቱ ገነነ
ትናንትም አርጅቶ ስሙም አምና ሆነ
የእንቁጣጣሽ ትዝታ
ትዝ አለኝ
እንኳን ተዘዋወርክ ወደ አዲሱ ዓመት
እንኳን አደረሰህ ለዐውደ ዓመት እለት
የማውቃቸው ሲሉኝ ከልብ በመመኘት
ትዝ አለኝ ትዝ አለኝ
መልካም እንቁጣጣሽ መልካም አዲስ ዘመን
እንኳን አብረን ደረስን
ይድገመን በብዙ ደጋግሞ ይድገመን
በኛ በሁላችን ትደግ ሀገራችን
ብለው ሲናገሩ የመንደሩ ልጆች
ወጣቶች ገና ቡቃያዎች
ትዝ አለኝ
በሣህን ዳቦው ሲደረደር
በዋንጫ ጠላው ሲንቆረቆር
አዮሃ አበባዬ
ሲሉ ወንዶቹ
አደይ የብር ሙዳይ
ኮለል በይ ሲሉ ሴቶቹ
እደጉ ብለው ሲመርቋቸው
ሽማግሎቹ
ታወሰኝ ትዝ አለኝ
የእንቁላል ልጆች የእንቁላል እናቶች
ፈርተው ተደናግጠው
ሲጮሁ ሲያለቅሱ ማሩን ተውን ብለው
ተቀልተው ሲበሉ ተቆርጦ አንገታቸው
የቅርጫት ሥጋ አንሱ ልጅ መሳይ ላኩና
ሥጋው አንዳገር ነው ጮማም አለውና
የመንደሩ ሰዎች ጥሪያቸው ታወሰኝ ታየኝ አሁን ገና
የእንግጫ ጉንጉን
ታስሮ በራሳችን
ምኞት ተመኝተን
ዓውደ ዓመት ሌላ ዓመት ይደጋግመን ብለን
ታወሰኝ
’’እማማ እንዳለች አንድ ግዜ ኑና
እንጠጣ እባካችሁ አንድ ስኒ ቡና’’
እያለ ሲለፍፍ በረፋድ ተነስቶ
አፉ በጣም ወዝቶ ጉንጩ እጅግ ፋፍቶ
ሆዱ ሞላ ብሎ ወደፊት ተገፍቶ
ዳቦ መሳይ ጎርሶ
አዲስ ሱሬ ለብሶ
ሞንደል ሞንደል ሲል ከቤታችን መጥቶ
የማሚቱ እናት ልጅ የአዲሱ ዘመን ሰው ታየኝ
በመንፈስ በሩን አልፎ ገብቶ
ታየኝ ታወሰኝ
አበባ እንቁጣጣሽ ልጆቹ ሲያመጡ
ገብተው ከመንደሩ ለሰዎች ሲሰጡ
ሲሳሳቁ ከውጭ እየተሯሯጡ
ታወሰኝ
ትናትም ቀን ነበር እንደዛሬ ሁሉ ከሌለት በፊት
ዛሬም በበኩሉ ከሌሊት በኋላ ይሆናል ትናንት
የግዜ አቀማመር
የዕድሜ አቆጣጠር
የዘመን ህላዌ የሠአቱ ምስጢር
ይገለጥ ይፈታ ይበጠር ይንጠርጠር
ትናንትና ዛሬ ነገ ሲባል ውሎ ለትናንቱ ነገ
የነገውን ዛሬ ትናንት ማድረግ ከፈለገ
ዘመን ተለወጠ ብለህ የምትጮኸው
ተጠየቅ በናትህ ተጠየቅ ባባትህ
አምና እንደምን ነበርክ ዘንድሮስ እንዴት ነህ?
ያኔ በዛሬው ቀን ምን ምን ታውቅ ነበርህ
የርቀትህ መጠን የሀሳብህ ስፋት
የነገርህ ወሰን እውቀትና ርዝመት
ከየት ተጀምሮ በየት በየት አልፎ እምን ላይ ያበቃል
የትኛውን ጨርፎ የቱን አጠቃሎ ከየትኛው አርፎ ምን ይመለምላል
ሃሳበ ግትር ነህ ዛሬም እንደወትሮ
ማን አለብኝ የሚል ሞኛ ሞኝ ደንቆሮ
እንግዲህ ወዳጄ ዘመን ቢለወጥም
መስከረም ቢጠባም
መንፈስህ ታድሶ ካልተለወጠ አብሮ
ከአምናው ከአቻምናው
ከትናንት በሽታህ አልዳንክም ዘንድሮ
ከቀድሞው ሥርአተ ትምህርት የ9 ክፍል የአማርኛ መማሪያ መጽሐፍ ላይ የተወሰደ
ለማከብራችሁ ወዳጆቼ በሙሉ ይልቁንም በዚህ ስርዓተ ትምህርት በዚህ ክፍል አብራችሁን ለነበራችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲሁም ይህችን ግጥም ለፈተና ተማሪ ፊት ላነበባችኋት በሙሉ መልካም ትዝታ ይሁንላችሁ
 መልካም አዲስ ዓመት
ዘመኑን የማስተዋል ዘመን ያድርግልን
መ/ር ሰሎሞን ፋንቱ 2007 ዓ.ም



No comments:

Post a Comment