ጮሀ የማታውቅ ወፍ ብትጮህ
እለቁ እለቁ ትላለች
የቀደሙት ሊቃውንት ይልቁንም
ከ 325 ዓ/ም ጀምሮ በተደጋጋሚ በቤተ ክርስቲያኒቱ የጠራ ትምህርት ላይ የኑፋቄ ትምህርታቸውን ሊዘሩ የተነሱ መናፍቃንን ከረቱ
እና ርትእት የሆነችውን እምነት ካጸኑ በኋላ የሚቀጥለውም ትውልድ እንዲሁ የአባቶቹን ፈለግ ተከትሎ ትክክለኛውን ኦርቶዶክሳዊ እምነት
እንዲጠብቅ ህግ አቁመው ድንጋጌ አጽንተው ስርዓት ሰርተው አልፈዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል አንዱ
በዓመት ሁለት ግዜ በጥቅምትና በግንቦት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲያደርግና ስርዓት እዲሰራ፣ ሀይማኖት እንዲያጠራ፣ መጻሕፍትን
እየመረመረ ደጉን ከክፉው እንዲለይ በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በማንኛው ግዜ የሚነሱ ማናቸውንም አይነት አደጋዎች እንዲከላከል
መደንገጉ ነው፡፡
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ
ኦርዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከንጉሳዊ ስርዓት ወይም ከሲሷዊ/በንጉሱ ግዜ ከምንግስት መሬት ሲሶውን በመውሰድ ራሷን ታስተዳድር
ነበር/ አስተዳደር ስትወጣ ለአስተዳደር የተመቸ እንዲሆን በማሰብ ሰበካ ጉባኤን በመቋቋም ላፉት 37 ዓመታት ቆይታለች፡፡ ይኸው
ላፉት 37 ዓመታት ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ግዜ በጥቅምትና ግንቦት ወር ምልዓተ ጉባኤ ያደርጋል፡፡
ከነዚህ የ37 ዓመታት
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ቢያንስ ለ10 ዓመትታ ተሳታፊ ነበርኩ በነዚህ ዓመታት ብዙ ነገሮችን ታዝቤአለሁ ሰምቻለሁ አይቻለሁ፡፡
ሁሉም ሰው ያየውንና የሰማውን በሙሉ እንዳይጽፍ እንዳይናገር እንዳይተች ኤኔን የያዘ እንደያዘው አምናለሁ፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ
ያለውን የአስተዳደር ግድፈት የአሰራር ብልሽት ብዙዎች በጥቂቱ የሚነካኩት ቢሆንም ሌሎች ብዙ ሊባልላቸው የሚችሉ እውነቶች እንዳሉ
ቢታወቅም ብዙዎች ለአባቶች ክብር ለቤተ ክርስቲያኑቱ ክብር ሲባል ሰድቦ ለሰዳቢ ከምስጠት እንዲስተካከል ብንጸልይ ይሻላል እየተባሉ
የተተው ብዙ የብዙ ብዙ ነገሮች እንዳሉ እምነቴ ነው፡፡
ነገር ግን ስህተት፣
ችግር በጊዜው በቀላሉ ሊነቀል የሚችል ችግኝ ሆኖ እያለ ሲውልና ሲያድር ግን ግንድ እያወጣ ለመንቀል እየቸገረ ብዙ የችግር ግንዶች
እዛ ቤት ይታያሉ፡፡ አሁንም አልነካቸውም ለምን ቢባል ለመልስ ሌላ ብዙ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ጊዜዬን አሁን ለተነሳሁበት ሀሳብ
ብቻ ለማድረግ፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም አይነካቸውም አያርማቸውምም፡፡
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሊወስዳቸው ከሚገቡ እርምጃዎች መካከል ችግሮችን እየነቀሱ በቤተ ክርስቲያቱ ላይ የተደቀነውን ማንኛውም
ዓይነት ማንኛውም! ችግሮችን በመንቀስ አሁን በማህረ ቅዱሳን ላይ ሊወሰድ እንደሚታሰበው አይነት ቁርጥ ውሳኔ መውሰድና ለቤተ ክርስቲያኒቱም
ሆነ ለአማኞች እረፍት መስጠት ያስፈልጋል፡፡
እንደዚህ አይነት ውሳኔ
የሚያስፈልጋቸው ብዙ ጉዳዮች ብዙ ችግሮች በቅዱስ ሲኖዶስ እየቀረቡ እንዲህ አይነት ቁርጥ ያለ ውሳኔ ሲተላለፍባቸው ማህበረ ምእመናኑንም
ሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱን እፎይ የሚያሰኝ ውሳኔዎች እኔ በተሳተፍኩባቸው
የ10 ዓመታት ምልዓተ ጉባኤ ቆይታ አላጋጠመኝም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ተሰብሳቢዎች በነበርንበት ዘመን ከምናገኛቸው ከኛ ቀድመው
ይህንን ምልዓተ ጉባኤ ከሚሰበሰቡ ሰዎች ስለቀደሙት አምስትና አስር ዓመታት የጉባኤው ሁኔታ ሳንጠይቅ አንቀርም፡፡ አንደምንሰማው
ከምናየው የተለየ አልነበረም፡፡ በእርግጥ ከመላው ኢትዮጵያም ሆነ ከውጪው ሀገራት የሚመጡ የሰበካ ጉባኤ ምልዓተ ጉባኤ ተሳታፊዎች
ወይም ተወካዮች በየ አካባቢያቸው ያለውን ለቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ ለአማንያኑ ፈተና የሆኑ ችግሮችን ሳያነሱ ያልፋሉ ማለት አይደለም
እያወራን ያለነው ስውሳኔው ነው፡፡ የመፍትሄ ሃሳብ እና ውሳኔ ግን
…..
ከሰላሳ ሰባት ዓመት
የዝምታ ጉዞ በኋል ቤተ ክርስቲያን ለውሳኔ ብትነሳ ማህበረ ቅዱሳን ላይ አረፈች ጮሀ የማታውቅ ወፍ ብትጮህ እለቁ እለቁ ትላለች
ማለት ታዲያ ይሄ አይደለ፡፡
አነሳሴ ስለ ማህበረ
ቅዱሳን ለማውራት አይደለም አደረጃቱን ሥራውን ለማንሳትና ለመፈተሽም ለመዘርዘርም አይደለም ግን አሁን ሊወሰንበት የታሰበው ውሳኔ
የተወራበት የተከሰሰበት ክስ ይገባዋል? ማለት ግን ያስፈልጋል፡፡
ማህበረ ቅዱሳን ነቅ የሌለበት ማህበር ነው ለማለት እንኳን እኔ አባላቱም አይደፍሩም፡፡ አንኳን ማህበሩ እውቅና የሰጠችውም ቤተ
ክርስቲያን መልካም አስተዳደርን፣ ሙስናን ዘረኝነትን እና የመሳሰሉትን በተመለከተ ፍጹን ነኝ የምትል አይመስኝም፡፡
ማህበሩ ሊሰራቸው በሚያስባቸው
መልካም ስራዎች የተጣደፈ ሩጫ ያለአግባብ የረገጣቸው ብዙ ሰዎች፣ ነገሮች እንዳሉ አያጠራጥርም፡፡ ባለፈው በመንግስት አካላት የአሸባሪነት
ስም ሲለጠፍበት ማህበሩ ብዙ የጠለቀ ግንዛቤ ሳይኖረው በውል ሳይረዳ አለአግባብ ተሀድሶ የሚል ስም ሲለጥፍባቸው የነበሩትን ሰዎች
ስሜት ለመረዳት ግዜው አሁን ነው ብዬ ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካላት ሊደገፍና ለውሳኔ ይበቃል ብዬ ሳላስብ /በነገራችን ላይ አለ አግባብ የተለጠፈባቸውን
ወይም በስህተት የታሙትን ማለቴ እንጂ በዚህ የተሀድሶ ተልእኮ እንቅሳቃሴ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች አልነበሩም ለማለት አይደለም/
፡፡ አሁን ግን ደነገጥኩ፡፡ ለምን የሚለኝ ሰው እንደማይኖር አምናለሁ፡፡ ይቅርታ አለ እንጂ ከሳሾች፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ
ስብከት መሰብሰቢያ አዳራሽ በነበረው ስብሰባ ጥቂት ተናጋሪዎች ስለ ማህበሩ ሲናገሩ ሰምቼ ያለሁበት ነው የጠፋኝ እውነት እነዚህ
ተናጋሪዎች በመንፈስ ቅዱስ ከሚመራ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተልእኮ ስር ናቸው ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል፡፡ ስለ ሰብሳቢው ግን ምንም
ማለት አልፈልግም እኔ እንጃ ምናልባት ደረጃዬ አይደል ይሆናል፡፡ ወይም አልናገርም ማለቴ መናገር ይሁንልኝ፡፡
ከማህበሩ ጋር የጠበቀ
ዝምድና የለኝም የጠበቀ ጠላትነትም የለኝም በጥቂት አለመግባባቶች ፊት ለፊት ተቋቁመን እንደምናውቅ ብዙዎች ያውቃሉ፡፡ ምን አልባትም
ስለ ማህበሩ ችግሮች አውሩ ብንባል ቀን ሙሉ ማህበሩ ሊያስተካክላቸው ስለሚገቡ ነገሮች ልናወራ እንችል ይሆናል፡፡ እውነት ለመናገር
ግን አን ቀን አይደለም አንድ ዓመት ማውራት ብንችልም እንኳን አሁን የተከሰሰበትን ክስ ግን ማንሳት አልችልም፡፡ ባጭሩ ይሔ ከእግዚአብሔር
አይደለም፡፡ በዚህኛው ክስ የተነሳ እስከመጨረሻው እኔ ከማህበሩ ጎን የምቆምበት እውነት አለኝ፡፡
በዚህ ሳቢያ ብዙ ጽሑፎችን
አንብቤአለሁ አንዳንዶች ማህበሩ በተከሰሰበት ክስ ሳይጠየቅ መልስ ሳይሰጥ እንዴት ይወነጀላል ሌሎች ደሞ ማህበሩ አሳዘነኝ በሚሉ
ጽሑፎችን ጽፈዋል፡፡
ማህበሩ ሳይጠየቅ ለማለት
አኮ የሚጠየቅበት አግባብ ሲኖር ነው፡፡ ለመሆኑ ከሳሾች ምን ብለው እንዳነሱት ሲገርመኝ እንደው ማህበሩ ቢጠየቅ ምን ብሎ ሊመልስ
ነበር? እንደው ሲከሰስ ቢውል የሚከሰስትን አምኖ መልስ ማዘጋጀትስ በምን መልኩ ይቻለዋል፡፡ ማህበሩ አሳዘነኝ ብለንስ የምንተወው
ነውን?
ዘመናቸውን በሙሉ ተኝተው
ሲነቁ እንዴት ማህበር በማፍረስ ላይ ይነቃሉ፡፡ አንድ ግዜ እንዲህ የሚባል ነገር ሰምቻለሁ፡፡ የፓርላማ አባል ነው አሉ ፓርላማው
ላይ ስንት ጉዳይ ሲነገር ተኝቷል ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አይተውት እኛ ስለ ሀገራችን እንደክማለን እንተጋለን ይሄ ግን ተኝቷል
ብለው ሲናገሩ አንዱ ከጎኑ ተነስ ስለአንተ ነው የሚወራው ብሎ ሲቀሰቅሰው እንደነቃ ደንግጦ ሻለቃ አድማሴን እቃወማለሁ አለ ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ምነው እንደነቁ ማህበሩ ላይ አረፉ::
መቼም በሀገራችን ሰው
የእምነቱን እንዲናገር አይፈቀድለትም ስለ ማህበረ ቅዱሳን ከተናገረ ተሐድሶ ስለተሐድሶ ከተናገረ ማህበረ ቅዱሳን ስለ ደርግ ከተናገረ
የንጉሱ ርዝራዥ ስለንጉሱ ከተናገረ የደርግ ካድሬ ስለ . . . . . . መባሉ አይቀርም እኔም አንዱን እንደምቀበል አምናለሁ፡፡ ነገር ግን የቱንም
ያህል ብቀበል ማህበሩ በዚህ ሰሞን የተነሳበትን አምኜ ከምቀበል ይሻለኛል፡፡
በዚህ አይነት የቤተ
ክርስቲያኒቱ ጉዞ ወዴት ነው???
በማህበሩ ላይ ሊወሰድ
ያለውን ውሳኔ በመስማት ምናልባት መነካታችሁን በማሰብ የተደሰታችሁ አበጀ እሰየው ያላችሁ ለተግባራዊነቱ የበኩላችሁን ለማድረግ የተጣደፋችሁ
የቸኮላችሁ ሁሉ አንድ ነገር ብቻ ልላችሁ እወዳለሁ፡፡አገሩን ከመጠቀምና ከመጎዳት ጋር ከዕልህ ጋር ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱን ከሚመራት
ከመንፈስ ቅዱስ እንድታዩት ለምናለሁ፡፡
እኔ በግሌ ማህበሩ የውስጥ
አደረጃጀቱን እንዲያስተካከል ስህተቶችን እንዲነቅስ እንጂ እንዲህ እንደከሰስና እንዲፈርስ ግን አልፈልግም፡፡
መ/ር ሰለሞን ፋንቱ
ጥቅምት 7 ቀን
2007 ዓ/ም
No comments:
Post a Comment