5. መዘጋጀት
ዝግጅት ማለት ለሚመጣና ለሚቀበሉት፤ ለሚያልፉበት ማንኛዉም ነገር ብቁ ሆኖ መጠበቅ ነዉ፡፡ የክርስትና ህይወት ጉዞ የመከራ ህይወት ጉዞ እንደሆነ በመጠኑ ለማየት ሞክረናል፡፡ የቤተ ክርስቲያን የጉዞ ህይወት የክርስትና እምነት ጉዞም ነውና በቤተ ክርስቲያን የደረሰ የመከራ ህይወት በክርስትና እምነት ላይ የወደቀ መከራ ነው ''ወአናቅፀ ሲኦልኒ ኢይኃይልዋ፤ የሲኦል ደጆችም አይበረቱባትም'' ያለውን የወንጌል ቃል ዮሐንስ አፈወርቅ በተረጎመበት ጊዜ ዲያብሎስ ቀስቱን ወረወረ አራገፈ ቤተ ክርስቲያንን ግን አልጎዳትም ይላል፡፡ ‹‹ባለጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና›› 1ጴጥ 5÷8 ጌታም ‹‹ስምዖን ስምዖን ሆይ
እንሆ ሰይጣን እንደስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ›› ሉቃ 22÷31
‹‹መጋደላችን ከደምና
ከስጋ ጋር አይደለምና ከአለቆቻችንና ከስልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋራ በሰማያዊው ስፍራ ካለ ከክፋት
መንፈሳውያን ሰራዊት ጋራ ነው እንጂ›› ኤፌ 6÷12 እያለ ወንጌሉ በክርስትና
ህይወት ዉስጥ ያለዉን መንፈሳዊ ተጋድሎ ይነግረናል፡፡
ይህንን መንፈሳዊ ተጋድሎ አሸንፎ የመንግስቱ ወራሽ ለመሆን መንፈሳዊ ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡
ሀገራችን ድንገተኛ በሆነ ጦር ብትከበብና የሚከላከል ሀይል ቢያስፈልግ ሱሪ የታጠቀ ወንድ ሁሉ መሳሪያ ተሸክሞ እንዲዘምት አይጠራም፡፡ ይነስም ይብዛም ቢያንስ ስለያዘዉ መሳሪያ አጠቃቀም የትንሽ ጊዜ ስልጠና ወይም ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ይህ ካልሆነ በያዘዉ ወገኑን የሚጨርስ አልፎ ተርፎም እራሱን የሚያበላሽ አይጠፋም፡፡
የክርስትና ህይወትም በዘመናት ሁሉ ሃይልን በሚሰጠን ካመንበት እኛን ለማዳን በታመነዉ አምላክ አሸናፊዎች ሁል ጊዜም ክርስቲያኖች ነን እንጂ የክርስትና ህይወት በራሱ የጦርነት መድረክ ነዉ፡፡ ‹‹በወደደን
በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን›› ሮሜ 8÷3
''ከእንቅልፍ የምትነሱበት ሰዓት አሁን እንደደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደኛ ቀርቧል፡፡ ሌሊቱ አልፏል ቀኑም ቀርቧል፤ እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውልቀን የብርሃን ጋሻና ጦር እንልበስ'' ሮሜ 13÷11
ሐዋርያው ሁላችን ለዚህ የመንፈሳዊ ትጥቅ ትግል ዝግጁዎችና አሸናፊዎች እንድንሆን አጋንንትን፤ ክፋትን የምንዋጋበት የብርሃንን ጋሻና ጦር እንድንለብስ ይጋብዘናል፡፡ያለ ዝግጅት ማሸነፍ ከቶ አይሞከርምና፡፡ ‹‹ፈጽማችሁ ለመቆም
እንድትችሉ የእግዚአብሔርን እቃ ጦር ሁሉ አንሱ›› ኤፌ 6÷13
ሙሴ ግፋቸዉ የበዛ የመከራ ቀንበር የወደቀባቸዉን ሕዝበ እስራኤል ከግብፅ ባርነት ለማዉጣት ከመመረጡ በፊት አርባ ዓመት በፈርኦን ቤትና የዮቶርን በጎች እየጠበቀ ይዘጋጅ ነበር፡፡ ያ ዘመን ለሙሴ የዝግጅት ጊዜው ነበር፡፡ በፈርኦን ቤት ሳለ ከቡደ መዝራዕት ሙሴ ምድራዊ ተስፋ ከነዓን፣ ሰማያዊ ተስፋ መንግስተ ሰማያት ያላቸው የእግዚአብሔር
ህዝብን ማንም እንዳይነካ ቅናት ሰላደረበት ግብፃዊውን በጥፊ መትቶ በአሸዋ ውስጥ ቀበረው፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ ዕብራዉያን እርስ በርስ ሲጣሉ አይቶ እናንተ እንዴት እርስ በርስ ትጣላላችሁ ወንድማማቾች አይደላችሁም አላቸው፡፡ ዕብራውያን
ወንድሞቹ ግን በእኛ ላይ አንተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብፃዊውን
እንደገደልኸው ልትገለኝ ትሻለህን? ብለው ግብፃዊውን በጥፊ እንደገደለው ገልጠው ቢነግሩት ለእስራኤል ህዝብ ፍቅር ሲል በግብፅ በፈርኦን ቤት የልጅ ልጅ ተብሎ
ከሚኖርበት ቤተመንግስት ወጥቶ ኮበለለ፡፡ ዘፀ 2÷11-15 በዮቶር ቤት ሳለ እግዚአብሔር ጠርቶት ህዝቡን ከፈርኦን እጅ አስለቅቆ ወደ ምድራዊቷ ተስፋ ከነዓን እንዲመራቸው ጌታ
አርጎ ሾመው፡፡
''ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተዉ በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት የንጉሱንም አዋጅ አልፈሩም፡፡ ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርኦን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፡፡ ከግብፅ ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንደሆነ አስቧልና፡፡ ለጊዜዉ በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቷልና፡፡''ዕብ 11÷24
መድኀኒዓለም ከርስቶስም በዚህ ምድር ተመላልሶ ያስተማረዉ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ነዉ፡፡ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ተመላልሶ ለማስተማር በምድር ላይ ሠላሳ ዓመት ተቀምጧል /ተመላልሷል/፡፡ ከእናቱና ከዮሴፍ ጋር በግብፅ በረሃ ከመሰደዱ ጀምሮ በቤተ መቅደስ ተገኝቶ ሲጠይቅ ሲመልስ መገኘቱ አነዚህ ሁሉ ለክርስቶስ የዝግጅት ጊዜዎቹ ናቸው፡፡
እንደ ሰው በየጥቂቱ አድጓልና፡፡
ክርስቶስ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ለማስተማር ሠላሳ
ዓመት ተዘጋጅቶአል ሲባል ክርስቶስ የሚሰራውን ለመስራት ዝግጅት የሚያሰፈልገው ሆኖ ሳይሆን እርሱ ያለፈበትን ህይወት እንድናልፍ ማስተማሩ ነዉ፡፡ ያልሄደበትን መንገድ ሂዱ ያላለፈበትን መንገድ እለፉ አላለምና፡፡
6. ወደ ኋላ አለመመለስ
ከሶዶምና ገሞራ መውጣት ብቻውን ለድነት በቂ አይደለም ባለፈው ክፍል ለመመልከት እንደሞከርነው ሎጥ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ስላገኘ እግዚአብሔር ከሶዶማውያን ጋር እንዳይጠፋ እጁን ይዞ ባወጣው ጊዜ ከትዕዛዝ ጋር ነበር፡፡ ወደ ኋላችሁ አትመልከቱ!
የእግዚአብሔር የትኩሳቱ ግለት ሰዶምን ባቀለጣት ጊዜ ዞረው እንዳያዩ ነገር ግን ወደ ተራራው ወጥተው እንዲያመልጡ ታዘው ነበር፡፡ ትዕዛዝ ተቀብለው ሲወጡ የሎጥ ሚስት ዘወር ስትል የጨዉ ሀዉልት ሆና ቀረች፤ ይለናል ታሪኩ፡፡ ዘፍ
19÷1-16
እንግዲህ ከጥፋት ለመዳን ከሶዶምና ገሞራ መውጣት ብቻውን በቂ ቢሆን ኖሮ የሎጥ ሚስት ትዕዛዝ ሰምታ ህግ አክብራ ወደ ተራራው ወጥታ ነበር፡፡ ነገር ግን ዳር አልደረሰችም፤ እስከ መጨረሻው አልዘለቀችም፡፡ የጨው ሀውልት ሆና ከተራራው መሃል ቀርታለች፡፡
ብዙዎች የክርስቶስ የማዳኑ ኃይል ስቧቸው ብዙዎችም በተለያየ መንገድ በአጠቃላይ አምስት ገበያ ህዝብ ተከትለውት ነበር፡፡ ነገር ግን ሁላችሁም መዳን ካማራችሁ መከተላችሁ ለህይወት ከሆነ ስጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ ዮሐ 6÷54 -
56 ባለ ጊዜ የቀሩለት አስራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ሰላሳ ስድስቱ ቅዱሳን እንስት እንዲሁም ሰባ ሁለቱ አርድእት ብቻ ነበሩ፡፡
በዘመናችንም የክርስቶስ የማዳኑ ወንጌል ሲሰበክ በፍቅር ተስበን ልባችን ተነክቶ እንቀርባለን፤ ወደ ቤቱም እንሳባለን ወደ ተራራውም እንሸሻለን፡፡ ነገር ግን እንደገና እንመለሳለን
የወጣንበት ይናፍቀናል ያለፍንበት ይጠራናል ''በቶሎ ወደኔ እንድትመጣ ትጋ ዴማስ ያሁኑን ዓለም ወዶ ትቶኛልና ወደተሰሎነቄም ሄዷል'' ይላል 2ጢሞ 4÷9 -
10
ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ቤት መምጣታችን፣ ወንጌል መማራችን፣ ማስቀደሳችን፣ ቅዱስ ስጋዉን፣ ክቡር ደሙን መውሰዳችን ብቻውን ለድህነት በቂ አይደለም፤ ወደ ኋላ አለመመለስ ደግሞም አለመውደቅ ይጠበቅብናል፡፡
ከደቀመዛሙርቱ ጋር የተቆጠረ ካበረከተው በልቶ፣ ተአምራቱን አይቶ የመንግስቱ ወራሽ ለመሆን የተዘጋጀ በሞትና በህይወት ላይ ስልጣን ሊሰጠዉ አንድ ቀን ብቻ የቀረው ይሁዳ በምኞቱ ተጠልፎ በገንዘብ ፍቅር ተነድፎ
አምላኩን በመሸጡ ከህይወት መፅሃፍ ተሰርዟል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ብቻውን ለድነት በቂ ቢሆን ኖሮ ከራሱ ከህይወት ራስ ከክርስቶስ እንደ ይሁዳ የተማረ አልነበረም፤ መመለሱ አስቀረው እንጂ
በሐዋርያት ሥራ ላይ የምናገኛቸው በወንጌል ልባቸዉ የተሰበረ ስለክርስቶስ ፍቅር ንብረታቸውን የሸጡ ነገር ግን በዚህ ሁሉ ተጋድሏቸዉ ለህይወት ያልተጠሩ ባልና ሚስት ናቸው ሐናንያና ሰጲራ
በጊዜዉ ልቡ በክርስቶስ ማዳን ፍቅር የቀለጠችበት ሁሉ ንብረቱን እየሸጠ በሐዋርያት እግር ስር ያስቀምጥ ነበር፤ ከዚያም እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነዉ ይኖሩ ነበር፡፡ ይህም ታላቅ የፍቅር ማኅበር የብዙ አህዛብን ልብ በጊዜዉ ይስብ እንደነበር የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይነግረናል፡፡
የቤ.ክ.ታሪክ በዓለም መድረክ ገፅ . 37. ታዲያ ሐናንያና ሰጲራ ይህ ታላቅ ፍቅር ስቧቸዉ ንብረታቸዉን ሽጠዉ በሐዋርያት እግር ስር ሊያስቀምጡ ከተስማሙ በኋላ ከሽያጩ ቀንሰዉ አስቀሩ መንፈስ ቅዱስንም ሊያታልሉ ሞክረዋልና በሦስት ሰዓት ልዩነት ሁለቱም ሞተዉ ተቀበሩ፡፡ ሐዋ 5÷1
በዘመናችን ያለ ሰዉ ምንም ለቃሉ ቢታዘዝ ለፍቅር
ቢገዛ ብዙ ተጋድሎ ቢኖረዉ ንብረቱን ሽጦ በሐዋርያት እግር ስር፣ በማዳኑ ደጃፍ፣ በምህረቱ አደባባይ ለማስቀመጥ ልቡ የሚገዛለት ሰዉ እጅግ በጣም ጥቂት ብቻ ነዉ፡፡ በዚህ እይታ ሐናንያና ሰጲራ የመንግስቱ ወራሽ የህይወት ባለቤት ለመሆን የሄዱበት መንገድ ብዙዉን ጉዞ ነበር፡፡ ነገር ግን በመጨረሻዉ ሰዓት ወደ ኋላ ተመልሰዉ ከድነት መዝገብ ተፋቁ፡፡ ስለዚህ በክርስትና ህይወት ወደ ኋላ መመለስ አደጋ አለዉ፡፡ ያዉም የሞት አደጋ! ስጋ ለባሽ የሆነ ሁሉ በምድር ሲመላለስ በኃጢአት ይመላለሳል፤ ይህም በስጋና በፍላጎት አስገዳጅነት ነዉ፡፡
''ህግ መንፈሳዊ እንደሆነ እናዉቃለንና እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የስጋ ነኝ፡፡ የማደርገዉን አላዉቅምና የምጠላዉን ያን አደርጋለሁና፤ ዳሩ ግን የምወደዉን እርሱን አላደርገዉም፡፡›› ሮሜ 7÷14
''ነገር ግን እላለሁ በመንፈስ ተመላለሱ የስጋንም ምኞት ከቶ አትፈፅሙ፡፡ ስጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በስጋ ላይ ይመኛሉና፡፡ እነዚህም እርስ በእርሳቸዉ ይቀዋወማሉ፡፡ ስለዚህ የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም፡፡'' ገላ 5÷16
ሰዎች ከኃጢአት በታች ለሆነ ለስጋ የተሸጡ ናቸዉና
ስጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በስጋ ላይ ሲቀዋወሙ ያልፈለጉትንና የማይወዱትን የሚሰሩ በደለኞች ይሆናሉ፡፡
ሁላችንም በድለናልና ከበደላችን ጀርባ ወይም ከበደላችን በኋላ የሚገርፈን የመንፈስ የፀፀት ጅራፍ ይህንን ገልጦ ያሳየናል፡፡ ማንም ሌባ፣ ማንም አመንዝራ፣ ተሳዳቢ፣ ሰዉ የሚያማ፣ የሚገድል መሆን አይፈልግም በፍፁም! ነገር ግን በዉስጡ የሚፈጠረዉን የስጋና የነፍስ ፍላጎት ፍልሚያ መቋቋምና ማዳመጥ ማስታረቅም ስለሚያቅተዉ ከማይታየዉ ፈቂቅና መንፈሳዊ ዓለም ይልቅ ለግዙፍ ስጋ ስለሚገዛና ስለሚማረክ ስለሚያደላም ለኃጢአት ይረታና የማይፈልገዉን ያን ያደርጋል፡፡ የማይፈልገዉን ያን ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም ሰዉ ንፁህና ፃድቅ እርሱ ብቻ ኃጢአተኛ የሆነ ስለሚመስለዉ ከመቀላቀል መሸሽን፤ ከማመስገን መርገምን፤ ከመዘመር መዝፈንን መርጦ ላይመለስ ጭልጥ ይላል፡፡
ኃጢአት አላደረግንም ብንል ሀሰተኛ እንሆናለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም
1ዮሐ 1÷10 ስለዚህ ሰዉ ኃጢአት ከሰራ በኋላ በንስሃ መመለስ ታላቅ መንፈሳዊ ብልህነት ነዉ፡፡
ከወንድሙ ከኤሳዉ ብኩርናን ነጥቆ ወስዶ የሸሸዉ ያዕቆብ እግዚአብሔር ከወንድምህ ከኤሳዉ ፊት በሸሸህ ጊዜ የጠበቅሁህ አምላክህ ነኝና ተነስተህ ወደ ቤቴል ዉጣ በዚያም መሰዊያዉን አድርግ ባለዉ ጊዜ ያዕቆብ ቤተሰቦቹንና ከእርሱ
ጋር ያሉትን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ቤቴል እንድንወጣ እግዚአብሔር አዞአልና እንግዳ አማልክቶቻችሁን አስወግዱ አላቸዉ፡፡ እነርሱም እንግዶች አማልክቶቻቸዉን አስወገዱ፤ ዘፍ 35÷1-4
በማስተዋል የምንመረምር ከሆነ ያዕቆብ ቤተሰቦቹና ወገኖቹ እግዚአብሔር ለያዕቆብ ከመገለጡ በፊት እንግዶች አማልክትን ያመልኩና ያስከትሉ ነበር ያዕቆብም እንግዶች አማልክቶቻቸሁን አስወገዱ ንፁሀንም ሁኑ ብሎ አላዘዛቸዉምም ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ ቤቴል አንዲወጡ እግዚአብሔር በጠራቸዉ ጊዜ ግን ያዕቆብ ‹‹እንግዶች አማልክትን አስወግዱ ንፁሃንም ሁኑ›› አለ፡፡
እኛም በዓለም ስንኖር ከእንግዶች አማልክቶቻችንና ከኃጢአታችን ጋር የነበረ ሲሆን የእግዚአብሔር የማዳኑ ኃይል በልባችን በርቶ በፍቅሩ ተስበን በምንመጣ ጊዜ ስጋዊ ምኞታችንንና ክፉ ፍላጎታችንን በሴኬም ዛፍ ስር ቀብረን ልንጠጋዉ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ወደ ኋላ አለመመለስ፡፡ ባለማወቃችን አስቀድሞ የኖርንበትን ክፉ ምኞት መተዉ ያስፈልጋል፡፡
አለበለዚያ ግን
v
ኃጢአታችንን ማወቅ ብቻዉን በቂ አይደለም፤ እስካልተፀፀትን ድረስ
v
መፀፀታችን ብቻዉን በቂ አይደለም፤ ንስሃ እስካልገባን ድረስ
v
ንስሃ መግባታችን ብቻዉን በቂ አይደለም ቅዱስ ስጋዉንና ክቡር ደሙን እስካልተቀበልን ድረስ
v
ቅዱስ ስጋዉንና ክቡር ደሙን መቀበል ብቻዉን በቂ አይደለም እስካልፀናን ድረስ
''እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ፤ ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ብሎ እንደተፃፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናነተ ደግሞ በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ'' 1ጴጥ 1÷14
ክፍል ሁለት
ሰዎች ለምን ሥር ሰደዉ እንዳያድጉ ሆኑ
No comments:
Post a Comment