እድሜህ
ስንት ነው? አራተኛ መንጃ ፈቃድ አውጥቻለሁ
አነጋገሩ
ገርሞታል ማስተዋል ተሞልቷል ከዚህ በፊት የሕይወት ተሞክዉን ሊያካፍለው ሲሞክር እንኳን ያሾፍበት ነበርና ንግግሩን አቋረጦ ለመሆኑ
ስንት ዓመት ሞላህ? ስንት ዓመት ሆነህ? አለው ምናልባትም ከእድሜ የመጣ ብስለት እንደሆነ ጠርጥሮ:: አሁን አራተኛ መንጃ ፈቃድ
አውጥቻለሁ አለው፡፡ ኖ ኖ የጠየኩህ ስለምትሰራው ሥራ ወይም ስለምትነዳው መኪና አይደለም እድሜህን ነው የጠየኩህ? አዎ ገብቶኛል
እኔም የነገርኩህ እኮ እደሜዬ አርባ ሞላኝ ለማለት ነው፡፡ አርባ ሞላኝ ለማለት አራተኛ መንጃ ፈቃድ አውጥቻለሁ ማለትን ምን አመጣው?
መንጃ ፈቃድ እኮ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ከዛም ልዩ የሚባል አለው እድሜህን ከመንጃ ፈቃድ ጋር ልታዛምደው እንዴት ተመቸህ?፡፡
አዎ መንጃ ፈቃድ እንዳልከው ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ከዛም ልዩ የሚባል አለው የምናልፍባቸውን የሕይወት እርከናት እንደዚህ አይቼው
ነው፡፡
ለምሳሌ
አንደኛ መንጃ ፈቃድ:: በአንደኛ መንጃ ፈቃድ የሚነዱ ተሸከርካራች ባጃጅ እና ሞተር ሳይክል ናቸው;; እነዚህን የሚነዱ አሽከርካሪዎችን
አይተሃቸው ከሆነ በጣም ፈጣኖች ምንም እንዲያቆማቸው የማይፈልጉ ናቸው፡፡ ጠባብ መንገድ ዳገት ቁልቁለት የተጨናነቀ ትራፊክ ፒስታ
መንገድ ብቻ ምንም እንዲይዛቸው አይፈልጉም የትራፊክ ውጥረት ቢኖር በመኪናና በመኪና መካከል እየተሸሎከሎኩ ካልሆነም በእግረኛ መንገድ
እየወጡ ይከንፋሉ እንደውም ከመሄድ ከመብረር ውጪ ምንም የሚታያቸው አይመስለኝም አስተውለህ ከሆነ አንዳንድ ቦታ ባጃጆችን ቢንቢ
ይሏቸዋል ውር ውር እያሉ ስለሚያስቸግሩ
በዚህ
የመንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክሩትን ከልደት ጀምሮ እስከ ሀያ ዓመታቸው ድረስ ሕይወትን በሚመሩት ብንመስላቸውስ? በዚህ የእድሜ ክልል
ሕይወታቸውን የሚመሩ ሕፃናት በደንብ አስተውለሀቸው ከኆነ ከላይ እንዳየናቸው አብራሪዎች ናቸው በቃ መሄድ መሮጥ መብረር ማንም እንዲያቆማቸው
አይፈልጉም፡፡ የሚደርሱበት የሚያውቁበት እድሜ ላይ ባይሆኑም ግን መፍጠን ይፈልጋሉ መፍጠን መብረር መሮጥ ሕይወት አስፋልት ብትሆን
ኮሮኮንች ወይም ፒስታ መንገድ ወይም በዚሕ የሕይወት ጎዳና በእድሜ የበለጸጉ ከእድሜ የተማሩ መንገዱን ቢይዙትም እነሱ ግድ የላቸውም
እየተሸሎከሎኩ መብረር ይመኛሉ፡፡ ታዲያ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ማገድ አይቻልም፡፡ መምራትና መንገድ ማስተካከል ነው የሚገባው አሁን
አሁን አኗኗራችንም ወደላይ ወደላይ እየሆነ ብዙዎች እንደልባቸው እንዳይበሩ እንዳይሮጡ በሁኔታዎችና በወላጆቻቸው ይታገዳሉ ይህንን
ማድረግ አለአግባብ መንጃ ፈቃዳቸውን መንጠቅ ነው፡፡ ማነው ሕፃናት ወላጆቻቸው ያለፉበትን መንገድ እንዳያልፉ በወላጆቻቸው የሚታገዱ
ፍጡራን ናቸው ያለው?፡፡
ሁለተኛ
መንጃ ፈቃድን ደግሞ እድሜያቸው ከሀያ እስከ ሠላሳ ዓመት የሆናቸውን ብንመስላቸውስ? ሁለተኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ የሚይዙ አሽከርካሪዎች
አነስተኛና የቤት መኪናዎችን የሚይዙ ናቸው እነዚህን አሽከርካሪዎች አስተውለሃቸው ከሆነ ከላይ እንዳየናቸው እጅግ ፈጣኖች ናቸው
ከላይኞቹ የሚለዩት ግን ሾልከን ወይም በእግረኛ መንገድ ወጥተን እንሂድ የሚሉ አይደሉም ለምን ከፊቴ ቆምክ ለምን ቆመህ አታሳልፈኝም
ብለው ሀገር ምድሩን በጥሩንባ የሚያሸብሩ ናቸው እንጂ፡፡ እንዴት መንገድ ዘግተህ አላሳልፍ ትለኛለህ? ብለው መንገድ ዘግተው ለቦቅስ የሚጋበዙ መንገድ ሲዘጋጋ እንዴት ለመኪናዬ ክንፍ
አልሰራላትም ብለው የመኪና ባለሙያቸውን የሚያማርሩ አይነት ናቸው በየትኛውም አቅጣጫ መሄድ የሚችሉ መሆናቸውን የሚያምኑ አይነት
ናቸው፡፡ መንገድ የያዘባቸው የመሰላቸውን ሁሉ የሚያስጨንቁ ዘለው ማለፍ የሚፈልጉ ሙጣጭ ትእግስት የሌላቸው አይነት ናቸው፡፡ መብራት
ላይ ቆመው የሚቁነጠነጡ የሚበራበትን ሰከንድ የሚቆጥሩ አረንጓዴ ሳይበራ በጥሩንባ ሊበራ ነው ተዘጋጁ ብለው የሚንጡ የማስጠንቀቂያ
መብራት ሲበራ ቀድሞ የገባው በፍጥነት እንዲወጣ መሆኑን ረስተው በመጡበት ፍጥነት በመፈትለክ ለማምለጥ የሚፈልጉ ወይም አደጋ የሚያደርሱ
እግረኛን የማያከብሩ ከመኪና ሲወርዱ እግረኛ መሆናቸውን የሚረሱ፡፡ ዜብራ የማይታያቸው ብዙ ግዜ ለአደጋ የተጋለጡና አደጋ አድርሰውም
ሰው ገፍተው ጥለውም ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ ወርደው ለተጎጂው ቦቅስ መመረቅ የሚፈልጉ አይነት ናቸው፡፡
በዚህ
የሕይወት ክልል ውስጥ የሚኖሩትንም ብናያቸው እንዲሁ ናቸው፡፡ እሳታዊ ባህርይ የሚታይባቸው ወደፊት ከመሄድ የፈለጉትን ለመፈጸም
ማንም ሊያግዳቸው እንደማይችል የሚያምኑ ማንም መንገድ እንዲዘጋባቸው፣ እንዲይዝባቸው የማይፈልጉ ማስተዋል ልብ መግዛት የሚባል ቋንቋ
መስማት፣ ስለ ጽድቅና ኩነኔ ማሰብ የማይፈልጉ አይነት ናቸው፡፡ እንደውም በዚች የድህነት ተምሳሌት በሆነች ሀገችን ይህንን አሳፋሪ
ስም ለመቀየር ሌት ተቀን የሚለፉ የደከመ ሰውነታቸውን በጥቂቱም ቢሆን ለማሳረፍ ጋደም ባሉበት ደዌ ጥሎአቸው ካልጋ የዋሉ ረፍት
ሲናፍቃቸው ወልደው የተኙ ልጆቻቸውን አባብለው በመከራ ባስተኙበት ብቻ ምን አለፋህ ለነገ ሥራ ዛሬ ማረፍ የፈለገውን ሁሉ እያሸበረ
የሚቀሰቅሰው ከየመስጊዱ የሚወጣው ከየቤተ ክርስቲያኑ እና አዳራሹ የሚሰማው ጩኸት ሰላም የሚነሳው ሁሉ ለእኔ በዚህ የእድሜ ክልል
ሕይወታቸውን በሚያሽከረክሩ ሹፌሮች የሚመራ ይመስለኛል፡፡ አየህ ይሄ ሁሉ ጩኸትና ሽብር በእጃቸው ያለውን ለማጽናት አይመስለኝም
አባል ለመሰብሰብና ለማብዛት እንጂ ለኔ በግቢያቸው በቅጥራቸው ቃላቸውን ሊሰማ ምን እንስራ ምን ይበጀናል ሊል የመጣውን መንጋቸውን
በተመጠነ ድምጽ ከመምከርና ከማጽናናት ይልቅ ቅጥራችሁን አልፈልግም ቃላችሁን አልሰማም ብሎ ጆሮውን ጠቅጥቆ ርቆ የተኛውን ግድ ካልሰማህ
ብለው በጩኸት የሚንጡ ይመስለኛል አየህ በእጃቸው ያለው የማያሳስባቸው
ከእጃቸው የወጣው ብቻ የሚያንገበግባቸው ይመስለኛል እንደውም በእጃቸው ያለውን የሚጥሉ የጣሉትን ሲያነሱባቸው ግን የማይወዱ የሚያሸብሩ
ይመስሉኛል፡፡ ግፋ ያዘው በለው ጩህ የሚባሉ ነገሮች ብቻ የሚመቻቸው ይመስሉኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ግን የሚመለከተው አካል ገብቶ
ሀይ ካላለ ከየመስጊዱ ቤተ ክርስቲያንና አዳራሹ በሚለቀቅ ልክ በሌለው ጩኸት/ድምፅ/
ምክንያት ሀገሪቷ በቂ እንቅልፍ የተመቸ
እረፍት ታሞ መዳን ባልቻለ ንክ ልትሞላ እንደምትችል ለመናገር ነቢይ መሆን አያስፈልግም፡፡
ወጣትነት መልክ
ያሳምራል እንጂ ንግግር አያሳምርም የሚባል አባባል ሰምቻሁ?
ወዳጅየው ግሩም
አድማጭ ወጥቶታል መሀል እየገባ ብቻ ትንሽ ይጠይቃል ሦስተኞችስ እነማንን ይወክላሉ? እንዴት ይመስልሀል? አለው፡፡ ሦስተኛ መንጃ ፈቃድ የያዙትን ደግሞ እድሜአቸው ከሰላሳ እስከ
አርባ የሞላቸውን ሰዎች ይመስሉኛል ሦስተኛ መንጃ ፈቃድ የያዙ አሽከርካሪዎች አነስተኛ የሕዝብ መኪና የሚይዙ ናቸው፡፡ ከራሳቸው
ውጪ አነስተኛ ሰው ይደርባሉ ስለዚህ ፍጠን ፍጠኝ የሚለው ስሜታቸው ቢታገላቸውና ቢያስጨንቃቸው እንኳን የጫኑት ሰው ረጋ በል እንጂ!
አያለ አደብ ያስገዛቸዋል መብራት እኮ ነው አቁም፣ በጣም ፈጥነሃል ወንድሜ ያልበላሁት እቁብ አለ፣ ያልፈፀምኩት ውጥን አለ ረጋ
በል! እግረኛ አክብር እንጂ አሳልፋቸው እያለ ይይዛቸዋል አሁን ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለተሳፋሪው ሲሉም ጭምር ባይፈልጉ እንኳን
መረጋጋት ይጀምራሉ ፡፡ በዚህ ሦስተኛ የህይወት ጉዞ ሽክርክሪት ላይ የሚገኙትም እንዲሁ ናቸው በወጣትነት የነበሩበትን የብቸኝነት
ቀላልና ግልጽ ሕይወት እየተው ወደ ከባድና ውስብስብ ሕይወት ይሸጋገራሉ፡፡ የሕይወት አጋር ያበጃሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ለራሳቸው ብቻ
ማሰብ ያቆማሉ ከብዙ ነገር ስለ ኑሮአቸው ሲሉ ይቆጠባሉ አለባበሳቸው አነጋራቸው አመጋገባቸው ውሎአቸው ሁሉም ነገር ይቀየራል፡፡
ቀድሞ ማርክ ያለው ልብስ ጫማ ይለብሱ ያጠልቁ እንደሆነ አሁን እሱ ይቀራል፡፡ በምትኩ የሚያሳስባቸው የአገልግሎት ዘመኑን ያልጨረሰ
ጡጦ ወተት የመሳሰሉት ይሆናል፡፡ የአውሮፓ ልብስና ጫማ እንደሚያደምቃቸው
ያምኑ እንዳልነበር አሁን ውበታቸው ቤታቸው እንደሆነ ወደ ማመን ይመጣሉ፡፡ የቻይና ጫማ የሀገር ውስጥ ምርት ማድረግ ይጀምራሉ፡፡
አስተውለህ እንደሆነ በዚህ መንጃ ፈቃድ የሚነዱ ሹፌሮች መኪናቸው ዳሽቦርድ ላይ የልጃቸውን ወይም የሚስታቸውን ፎቶ ይለጥፋሉ ለምን
ብትላቸው የእጅ ፍሬን ናቸው ይሉሀል፡፡ አሁን ከወንበራቸው ጎን ፋብሪካው የሰራው የእጅ ፍሬን አይደለም የእጅ ፍሬናቸው ከፊት ለፊት
የሚያዩት ፎቶ እንጂ ማርሽ ሲቀይሩ መፍጠን ሲያምራቸው ፎቶዉ ቀስ! ይላቸዋል በዚህ የህይወት ዘመንም ያሉ እንደዚሁ ናቸው፡፡ በዚህ
ጊዜ እንደበፊቱ አንተ በፈለክበት ቦታ አታገኛቸውም እንዳገኘህም አትጎትታቸውም እንደተመቸህ አታበድራቸውም አትበደራቸውምም አሁን
የሚመራቸው የቀድሞ ትኩስ የወጣትነት መዘወሪያ ሳይሆን ትዳራቸው ቤታቸው ይሆናል፡፡ አስተውለው ሲያወሩ አስቀምጠው ሲመክሩ ብታይ
አትደነቅ አሁን የሚያወራዉ ከራሱ ያመኘጨውን ብቻ አይደለም ከትዳሩ ጋር መክሮ የተስማማበትን ነው፡፡ መፈክራቸው ሮጦ ከመቅረት ቃስ
ብሎ መድረስ ይሆናል፡፡
አራተኛ መንጃ ፈቃድ
የያዙ ሹፌሮች የሚነዱት መኪና ድርርርር ተሽሽሽሽ የሚል ከባድ መኪና ነው እንፍጠን ቢሉ እንኳን መኪናው በራሱ ይይዛቸዋል ስለዚህ
አስተውለው የሚነዱ ተረጋግተው የሚጓዙ ድርርርር ተሸሽሽሽ እያደረጉ የሚነዱ ይሆናሉ፡፡ እግረኛ የሚያከብሩ እባክህ ቃስ ብለህ ንዳ
እያሉ የሚመክሩ አምልጠው ለመሄድ የማይሞክሩ ናቸው አነስተኛ ህዝብ ከሚጭን መኪና የተላለፉ ናቸው ከበፊቱ በዛ ያለ ህዝብ የሚጭን
መኪና ይነዳሉ ስለዚህ አሁን ለብዙ ህዝብ ዋስትና እንደሚሰማቸው ያውቃሉ ስለዚህም ህዝቡን ያከብራሉ ቃስ ብለውም ይጓዛሉ፡፡
እኔ እንደሚመስለኝ
በዚህ የህይወት ክልል ውስጥ የሚገኙት እድሜአቸው ከአርባ እስከ ሃምሳ ያሉት ናቸው፡፡ ማስተዋል ታይባቸዋለህ ሁሉን አክባሪ ይሆናሉ
የተጣላ አስታራቂ ናቸው አሁን የሚያሳስባቸው የቤታቸው ጉዳይ ብቻ አይደለም የጎረቤታቸው፣ የመንደራቸው፣ የሀገራቸው ጉዳይ እንደሚያገባቸው ይሰማቸዋል፡፡
ለሽምግልና ለዋስትና ለእርቅ የምትፈልጋቸው እነሱን ይሆናል ብዙ ጊዜ ሀገር ለመምራትም የሚመረጡት በዚህ እድሜ ክልል ያሉ ግለሰቦች
የሚሆኑትም ለዚህ ይመስለኛል፡፡ ቃስ ብሎ የተጓዘ ሩቅ ይሄዳል ይላሉ፡፡
አሁን አንተም መገመት
አያቅትህም፡፡ በአምስተኛ መንጃ ፈቃድ የሚነዱ መኪኖች እጅግ በጣም ተላልቅና በመቆምና በመሄድ መካከል ያሉት ነው፡፡ ረጅም መንገድ
የሚጓዙ መኪኖችን የሚያሽከረክሩ መኪኖችን እና ሌሎች ከባድ እቃዎችን
የሚያዝሉ ተሸከርካሪዎችን የሚነዱ ናቸው፡፡ እንኳን ዳገትና ቁልቁለትንም መብረር የማይችሉትን መኪኖች ነው የሚይዙት፡፡ ታዲያ በዚህ
የህይወት ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎችን ከሃምሳ እስከ ስድሳ ዓመት የሞላቸውን ሰዎች ብንመስላቸው ሕይወታቸውን በቀላሉ ማዛመድ እንችላለን፡፡
በፍጹም ትዕግስት የተሞሉ ሁሉን እንደየጸባዩ የሚሸከሙ ምክራቸው የሚናፈቅ ሁሉ የሚጠጋቸው አይነት ሰዎች ናቸው የተሰጣቸውን ሀላፊነት
የሚያከብሩ አሁን ለቤቴ ለኑሮዬ ብለው የማይዋሹ የተረጋጉ አይነት ሰዎች ናቸው፡፡ ባሳለፉት ሰፊ የሕይወት ልምድ የተሞሉ ከማውራት
ይልቅ ማድመጥን የሚወዱ ናቸው፡፡ በዚህ እድሜአቸው ብዙ ሀላፊነት ይሸከማሉ ቀድሞ ለታጩበት ሀላፊነት አሁን ይሾማሉ፡፡ ቤታቸውን
መንደራቸውን ቀበሌአቸውን ሀገራቸውን በአግባቡ መምራት ይችላሉ፡፡ የረጉ ናቸው የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣው የለ፡፡ እንደ ወተት ከረጋ
ኑሮአቸው ውስጥ ለህይወትህ ማጣፈጫ የሚሆን መልካም የምክር ቅቤ ታገኛለህ፡፡
አሁን ልዩ መንጃ
ፈቃድ አልቀረም በልዩ መንጃ ፈቃድ የሚነዱ ምን ምን ናቸው ሩሎ ዶዘር እስካባተር የመሳሰሉት አይደለም? የተሸከርካሪ መጨረሻ ሩሎ
ዶዘር እስካባተር የመሳሰሉትን ተሸከርካሪዉች/ተሸከርካሪ ከማለት ግን ዞሮ የሚመጣ ጎማ ያላቸው ማለት ሳይቀል አይቀርም መሰለኝ/ የሚነዳ ሰው መቼም ሹፌር ነኝና ለሚስቴ ከሰል ልጫን የሚል አይመስለኝም ሥራቸው
በተወሰነ ቦታ ነው ተሸከርካሪቸው ሩቅ ቦታ ቢፈለግ እንኳን በሌላ መኪና ተጭነው ነው የሚሄዱት:: እየሄዱ ነው ባይባልም ቆመዋል
ግን አያስብልም:: በአጠቃላይ መሬት እየቆጠሩ የሚጓዙ ናቸው፡፡ በዚህ የመንጃ ፈቃድ አሽከርካሪዎች የምመስላቸው እድሜአቸው ከስድሳ
ዓመት በላይ የሆናቸውን ነው ጉዞአቸው የተመጠነ ነው ሩቅ መሄድ እንኳን ቢያምራቸው ረዳት ያስፈልጋቸዋል አሁን ለቤቴ ለትዳሬ ለሀገሬ
ማለታቸው ይቀንስና ለነብሴ ማለት ይጀምራሉ፡፡ በቀስታ እና በጥንቃቄ የተፈጠሩባትን ምድር እየቃኙ ይጓዛሉ፡፡ አሁን የሚገቡባት ቤታቸው
ናትና የአፈር ጉዳይ ያሳስባቸዋል ያስጨንቃቸዋል፡፡ በአፈር ጉዳይ በዚህ የእድሜ ክልል ካሉ ሰዎች ጋር በፍፁም አትስማማም:: ሃያ
ሣንቲ ሜትር አፈር ከክልላቸው መንካት አትችል፡፡ መሬትን ማልማት ችግኝ መትከል እና መንከባከብ ይጀምራሩ መግያችን ነሽ መምጣታችን
እርግጥ ነው እያሉ ያባብሏታል፡፡ ንስሃ ይግቡ አይግቡ ባይታወቅም እያሉ መቃብር ቤታቸውን ያሰራሉ፡፡ ሙቀት ልምላሜ እየተለያቸው
ይመጣሉ፡፡
እያለ ዝም ብሎ
ያለ ማቋረጥ ሲያብራራ ወዳጁ በመደነቅ ፈዞ ያየዋል ማብራራቱን አቆምና በተራዉ ለመሆኑ አንተስ እድሜህ ስንት ነው? አለው፡፡ የኔ
የኔ አዎ አምስተኛ መንጃ ፈቃድ አውጥቻለሁ አለው፡፡ ገምቻለሁ አለበለዚያ እንዲህ ማቆሚያ የሌለው ዲስኩር ስደሰኩር ዝም ብለህ አትሰማኝም
ነበር፡፡
ዞሮ ዞሮ ከቤት
ኖሮ ኖሮ ከመሬት አይቀርም የሚለውን ማመን ጀምረሀላ አለው በመቀለድ
ቀጠለናም አስረግጦ እንዲህ አለ ታዲያ ያለ እድሜያቸው የከባድ መኪና ተሸከርካሪ የሚያወጡና
በአግባቡ የሚያሽከረክሩ እድሜአቸው ከፍ ካለ በኋላ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ የሚያወጡ እንዳሉ ሁሉ፡፡ የቤት መኪና ይዘው
የተረጋጉ ከባድ መኪና ይዘው አካኪ ዘራፍ የሚሉ እንደማይታጡ ሁሉ በልጅነታቸው አስተዋይ የሆኑ ቤተሰብ መንደር ሀገር የመሩ፡፡ እንዲሁም
እድሜያቸው ማስተዋል ያላብሳቸዋል ሲባሉ ባህሪያቸው የተበላሸ በስነምግባር የዘቀጡ እንደማይታጡ መጠርጠር የለብንም ብሎ አከለበት፡፡
ይቅርታ እኔ አራኛ
መንጃ ፈቃድ አውጥቻለሁ እናንተስ?
ለክቡራን አንባቢዎቼ
ይመስለኛል እያልኩ መፃፌን እንዳትዘነጉብኝ
አመሰግናለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment