ብዙ ወንድችና እህቶቼ በፌስቡክ አድራሻዬ ጥያቄዎች ይልኩልኛል እስከ አሁን በዚያው
አድራሻ መልሱን የምሰጥ ቢሆንም ዛሬ ግን ሴት ልጅ ሱሪ መልበሷ ሃጢአት የሆነው ለምንድን ነው; በሚል ለደረሰኝ ጥያቄ ብዙ
አንባቢም ቢያየው በማለት በ2000 ዓ ም ስር ሰዳችሁ እደጉ በሚል ጥንስስ ተነስቼ
ክርስቲያናዊ ህይወትና አስተዳደጉ በሚል ካሳተምኩት መጽሐፍ በክፍል
ሁለት” 1.3 ስሜታዊ መሆን በሚል የሰፈረውን
ሀሳብ እንዳለ ባቀርበው ከላይ ለተነሳዉ ጥያቄ መልስ
ይሆናል ብዬ ገምታለሁ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ይቺን ብዙ አንባቢ ያላገኛትን መጽሐፌን ስር ሰዳችሁ እደጉ በሚል ርዕስ ስር በተከታይ የማቀርባት መሆኔን በትህትና ገልጣለሁ፡፡ መልካም ንባብ
አስተያየታችሁን ጥቆማችሁን አትንፈጉኝ
1.3 ስሜታዊ መሆን
ስሜታዊ መሆን በክርሰትና ህይወት ላይ ትልቅ አደጋን ያስከትላል፡፡ ስሜታዊነት ከዚህ በፊት በጥቂቱ ለማየት እንደሞከርነዉ በተገቢዉና በአስፈላጊዉ ቦታ ካልተጠቀምንበት በክርስትና ህይወታችን ላይ ጥላ ያጠላብናል፤ ስሜታችን ሲቀዘቅዝ ነገር ሁሉ ይቀዘቅዛል፡፡ እግዚአብሔር የረሳን የተወን ይመስለናል፤ ስሜታችን ሲግል የቅድስና ኮርቻ የተፈናጠጥን ያክል ይሰማናል፡፡ ስሜታዊ ስንሆን ደስ ሲለን እናመሰግናለን፤ ሲከፋን እንሳደባለን በአንድ ወቅት
የምናመልከውን ሀያልና ገናና አምላክ በቤተሰባችን ወይም በራሳችን ላይ አደጋ ሲደርስ የምንቀየም የምናኮርፍ የማንፀልይ
የማናመሰግን እንሆናለን ይህም የስሜታዊነት ችግር ነዉ፡፡ በጣም ስሜታዊ ስንሆን ስሜታዊነት ከሚወልዳቸዉ ነገሮች አንዱና ብዙ ሰዎች ላይ
የሚታየዉ በአንድና ጥቂት ነገር ላይ ማተኮርና ማጥበቅ ነው፡፡
ብዙዎች ወደ እግዚአብሔር ቤት ሲመጡ ለወንጌሉ ሲታደሙ መስማትና መማር የሚፈልጉት ስለ አንድ ነገር ብቻ ይሆናል፡፡ መናፍቃንን መርታት ስለሚችሉበት ነገር፡፡ በእርግጥ አንዳንድ መምህራንም ኮርስ የሚሰጡትም ጭምር የኦርቶዶክስ እምነት መሠረቱ ነገረ ቅዱሳን እንደሆነ አበክረዉ ሲናገሩ ይሰማሉ፤ ከዚህ የተነሳ ተማሪዎችም ስለ ነገረ ቅዱሳን ተምረዉ መናፍቃንን ማሳፈር ከመፈለግ ዉጭ ለህይወታቸዉ መሰረት የሚሆን ነገር አይጨብጡም፡፡ ይህ ማለት ግን ስለ ነገረ ቅዱሳንና ስለ እመቤታችን አማላጅነት፤ መማርና ማወቅ አያስፈልግም ማለት አይደለም፡፡ የእምነቷ መሠረት ግን ቅዱሳንን ቅዱስ ያሰኛቸዉ የቀደሳቸዉ እናቱ ማርያምን በእናትነት የመረጣት ማኅተመ ድንግልናዋን ሳያጠፋ ድንግል ተብላ ተመስግናና ተከብራ እንድትኖር የቀደሳት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነዉ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ምዕመናን ብቻ አይደለም መምህራንም ስሜታዊ እንሆናለን፡፡ መምህራንም እንዲሁ ከግንዱ ይልቅ በቅርንጫፉ ላይ ስለምናተኩር በጥቃቅን ነገር ምዕመናንን መዝለፍ ይቀናናል ከመጠመቅ ውጭ ምንም እዉቀት የሌላቸውንና በአመት አንድ ጊዜ አክሱም ጽዮን ወይም ግሸን
ማርያም የሚገኝን ምዕመን በተገኘዉ አጋጣሚ ስለክርስቶስ ልዩ የመስቀል ፍቅር ከመስበክ ይልቅ ፀጉርሽን ቀለም የምትቀቢ፤ ሊፒስቲክ የምትለቀለቂ፤ ጥፍርሽን የምታሳድጊ፤ በሱሪ የምትወጠሪ በማለት ማስበርገግ ይቀናናል የብዙዎቻችን ህይወት በምንዝርና ተበክሎ ለሴት ሱሪ ስለመልበስ እንጨነቃለን
ከጋብቻ ውጪ የሚደረግን ዝሙት ዘንግተን በሰርግ (በተክሊል) የሚያገባ ሰው በቬሎ ስለመቅረብና አለመቅረብ እንጠበባለን
በአጠቃላይ ግመሉን እየዋጥን ትንኙን ለማጥራት ጊዜ እናባክናለን፡፡ መምከሩ ተገቢ ቢሆንም ድሮም በትግል የመጣና በአጋጣሚ የተገኘ ምዕመን ይህንን የተግሳጽ ቃል ዳግመኛ ላለመስማት ጠፍቶ ይቀራል፡፡ ይህ ማለት ግን እነዚህ
ከላይ የጠቀስናቸውን ነገሮች ማበረታታት አይደለም፤ የክርስቶስን የፍቅር ልክ መንገር አይቀድምም ወይ; ለማለት እንጂ ሱሪ መልበስስ
የሚያመጣው ችግር ምንድን ነው?
በዚህ ነጥብ ላይ ብዙ መምህራን የተለያየ ሀሳብ አለን፤ የምንቃወመውም የምናወግዘውም ብዙዎች ነን፡፡ ነገር ግን ሱሪ የሚለብሱ እህቶቻችን ቁጥር በጣም እያሻቀበና
ባስ ሲልም ወደ እናቶቻችን ልማዱ
ችግር ካልነውም ችግሩ ሲጋባ እንጂ ሲቀንስ አይታይም፡፡ ዛሬ በየቤተ ክርስቲያኑ፤ በየገዳማቱ ከሚገኙ ሴቶች ምዕመናን በእርግጠኝነት ከግማሽ በላዩ ሱሪ ለባሾች
እየሆኑ ነዉ፡፡
ይህም ሀሳብ በትምህርትነት ሲቀርብ #ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ፡፡ ይህንንም የሚያደርግ በአምላኩ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና$ ዘዳ 22÷5 የሚለዉን የሙሴ ህግና ሐዋርያዉ ጳዉሎስ ለልጁ ለጢሞቴዋስ #እንዲሁም ሴቶች ደግሞ በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን የሚሉ ሴቶች እንደሚገባ መልካም ለማድረግ እንጂ በሹሩባና በወርቅ ወይም በእንቁ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ$ 1ጢሞ2፣ 9 በሚለው ትምህርት ላይ እንንተራሳለን ይህም የሴቶች ሱሪ መልበስ ለዝሙት የሚያጋለጥ መንፈስ ትውዝፍት ወይም የምንዝር ጌጥ እንደሆነ በማመን ነዉ፡፡ ከመቼ ጀምሮ ኣጋንንት ለእግዚአብሔርና ለቤቱ መቅናት እንደጀመሩና ጥብቅና እንደቆሙ ባይታወቅም አንድ አንድ የአጋንንት መንፈስ አለብን የሚሉ ሰዎች ሱሪ የለበሱ እናቶችን
እና እህቶችን በየገዳማቱ ሲሰድቡ ሲያዋርዱ ሱሪ ሲቀዱና ሲደበድቡ ይታያሉ፤ ግማሹ ይደግፈዋል ለግማሹ አይዋጥለትም ተኩላ ቢለምድ በግ አይሆንምና
የምንዝር ጌጥ ስሙ እንደሚያመለክተው ለግልሙትና ሥራ የሚውልና ለዝሙት ግብር ሰዎችን የሚያነሳሳ አልባሳትንና ጌጣጌጦችን አብዝቶ መጠቀምን የሚያመለክት ነው፡፡ የውስጥ ሰውነትን የሚያሳዩ ሆዳቸውን እምብርታቸውን ጭናቸውን የሚያሳይ አለባበስ ለመንገደኛ ሁሉ የተገለጠ ነውና ይህንን ማብራራት አያስፈልግም፡፡ ታዲያ በእውነት ሁሉም ሴቶች ሱሪ የሚለብሱት በውስጣቸዉ ያለ የዝሙት መንፈስ ሲጨምር የተደበቀው መጎምዠታቸው እድገቱን ሲጨርስ በላይኛው ገፅታ የሚታይ ምልክት ነውን;
አንድ ጊዜ በአንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ሱሪ መልበስ ለዝሙት ያነሳሳል ወይ; በሚል ሰፊ ፕሮግራም እንደነበረ ሁላችንም በየቤታችንም አስተያየት የሰጠንበት ነውና አልመለስበትም፡፡
ግን በሰዶምና ገሞራ ጊዜ ህዝቡ ዝሙት በላያቸዉ ነግሶ እግዚአብሔር እስኪቆጣና ከተማዋን እስኪያጠፋት በደረሰ ጊዜ (ዘፍ 25÷1)
የተስፋይቱ ምድር ወራሾች በዝሙት ምክንያት ከአህዛብ ሴት ጋር በወደቁና እግዚአብሔር በቀሰፋቸዉ ጊዜ (ዘፍ25÷1)
ታላቁ ናዝራዊ ሶምሶን ከደሊላ ጋር ወድቆ ፀጋዉ እስኪገፈፍ ድረስ ቢደርስም (መሳ16÷1)
የታላቁ ንጉስ የዳዊት ልጅ ሰለሞን ከአህዛብ ሴቶች ጋር በፍቅር የወደቀው በቁጥር የሚበዙ እቁባቶችና ሚስት ያበጀው (1ነገ 11÷1- 13)
የሰዉ ልጅ ለዝሙት ባለዉ ታላቅ የመጎምዠት ፍላጎት እንጂ ማበረታታትና ማደፋፈር
እንዳይሆን እንጂ ሴቶቻቸዉ ሱሪ ለብሰዉ ፍላጎታቸውን ገዝተው
አሳስተዋቸው ነው ማለት ይከብዳል፡፡
ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ግን ለማበረታታት ወይም ለመደገፍ ሳይሆን መወገዙ ኃጢአት መሆኑ አለአግባብ እንዳይሆንና ብዙዎች እንዳይርቁ ነዉ፡፡ ባናበረታታ ነገር ግን ባናወግዝ ስንት የቤተክርስቲያን ልጆችን ወደ ሱሪ መልበስ እንገፋለን ወይስ ስንት ሱሪ ለባሾችን ወደ ቤተክርስቲያን እንስባለን;;
ለፀሎት አለመመቸትን እንደምክንያት ብንጠቅስ የሚያስኬድ ይመስላል የአካልን ቅርፅ ያሳያልና የሚፀልዩ ሰዎችን ሀሳብ ሊበትን ይችላል፡፡ የካህናትም በቅዳሴ ጊዜ ወጥ የሆነ ልብሰ ተክህኖ መልበሳቸዉ እንዲህ ያለ የመንፈስ ዝለትን ለመጠበቅ ነዉ፡፡
ይሁንና በቤተክርስቲያን የቅዳሴ ጊዜ ወይንም የፀሎት ሰዓት ሀሳብን የሚሰርቀው ሱሪ መልበስ ብቻ አይደለም የተጣበቀ ቀሚስና የተቆረጠ ነጠላ ጭምር ሊስተካከሉ ይገባቸዋል፡፡
እንግዲህ ሱሪ የለበሱትም ይሁኑ ነጠላቸዉ የተቆረጠውን እህቶቻችንን ከማሸማቀቅና ከማውገዝ ይልቅ ቢማሩና በፍቅር ብንስባቸዉ የሚያልፉበት የቤተክርስቲያን አገልግሎት እንዴት መልበስ እንዳለባቸው ያሳያቸዋልና አቅርቦ ማስተማር ቢቀድም መልካም ነው፡፡ ቬሎ ለብሶ መዳርም በዚህ ርዕስ ላይ ቀድሞ ከተነሳው ጉዳይ /ሀሳብ/ የተለየ ነጥብ የለም አይኖርም፡፡
የዚህ ጽሁፍ አላማ ለምን ተከለከለ ለምን ቀረ ለማለት ሳይሆን ከዚህ ጀርባ ያለውን ሀሳብ መፈተሸ ነው፡፡ ለመሆኑ
ቤተክርስቲያኗስ ቬሎ መልበስን ከልክላለች; ሁሉም የሚያስተውለው እውነት አለ፤ ቬሎ ለመልበስ ካለ ፍቅር የተነሳ የአንድ ሰዉ ሠርግ ሁለቴ ስለመሆኑ! ይህ ችግር ከተራው አማኝ ጀምሮ ተምረናል እስከሚሉት ምሁራን እና
አገልጋዮች ድረስ እውነት እየሆነ ይመስላል፡፡ ተክሊል ሀሙስ ሠርግ እሁድ ከዚያም የራቀ ሊኖር ይችላል፡፡
እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው ማቴ 19፤ ይህ ህያው የሆነ የማይሻር የማይለወጥ የማይሻሻል የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ነገር ግን ሀሙስ በስርዓተ ተክሊል አንድ የሆኑ ባልና ሚስት ቅዳሜ ወይም እሁድ ድጋሚ እስኪያገናኛቸው መለያየታቸው ገሀድ የወጣ እውነት እየሆነ
ነው፡፡
ለቬሎ የሚሰጡት ትርጉሞች ወይም ክልከላዎች የበዙ ቢሆኑም የምዕራባዉያኑ ባህል ነው፤ ስጋዉና ደሙን ያረክሳልና ........ የመሳሰሉት ሲነገሩ ወይም በትምህርት መልክ ሲሰጡ ይሰማሉ፡፡
አንድ ሰሞን ሚስቶቻቸው ቬሎ እንዳይለብሱ የሚከለክሉ ባሎች እነሱ በሱፍ ተውበዉ ይቀርቡ ነበር፡፡ የኋላ የኋላ ግን ለሁለቱም ስምምነት ሲባል ይመስላል ሀሙስ በነጠላና ቀሚስ እሁድ በቬሎና በሱፍ ሆኗል፡፡
እስኪ ይህንን ሀሳብ በቀደመው ከውሳኔ ባለመድረስ ሀሳብ በጥቂቱ እንፈትሸዉ፡፡ ቬሎ በእዉነት የእኛ ባህል ስላልሆነ ነዉ ቤተክርስቲያን የከለከለችዉ; በእርግጥስ ከልክላለች; ወይም ምዕመናን እዛዉ ተከላከሉ; በእርግጥ ሰባክያነ ወንጌልም በዚህ ላይ የሰላ ትችት ሲሰነዝሩ ይሰማሉ፤የዉጪ ባህል ነዉ ብለን የምንል ከሆነ ግን ትንሽ ያስቸግራል፡፡ በቤተ ክርስቲያን የውስጥ አገልግሎት ጭምር የምንገለገልባቸው ብዙ የውጪ ባህል መገልገያዎች
አሉ፡፡
ወደ ሥጋወ ደሙ በመቅረቡ የክርስቶስን ስጋና ደም ያረክሰዋል የሚሉም ካሉ ማለታቸዉ ሊያሳፍራቸዉ ይገባል፡፡
ቬሎዉ የጌታን ስጋና ደም ያረክሰዋል ወይስ የጌታ ሥጋና ደም ቬሎዉን ይቀድሰዋል ወይስ የአንድ ሰዉ ጋብቻ ሁለቴ መፈፀሙ ቬሎ ለብሶ ከመቁረብ የተሻለ ነዉ; አንባቢ ይፍረድ፡፡
ሌላ ሻገር ያለ ምልከታስ ቢኖረን፡፡ አሁን ለሠርግ ልብስ የምንጠቀምበት የሀገር ባሕል ልብስ የማን ልብስ ነዉ; የየትኛዉ ሀገር፤ መቼም ከዳር እስከ ዳር ላሉ ሰዎች የባህል ልብሳቸዉ ነዉ ማለት ይከብዳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቤተክርስቲያንን ሳናዉቀዉ ብሔርተኛ እንዳናደርጋት ያስፈራል፡፡ ዛሬ ብቻም ሳይሆን ድሮም ነጠላ ያልለበሰ ሰዉ ለማስቀደስ አይችልም፡፡ ዛሬ ደግሞ ሊያዉም ነጠላዋን የነጠላ ቁምጣ አድርገዋታል፡፡ ይሁንና ይህች ቤተክርስቲያን ዓለም አቀፋዊት ናትና በዉጪ ያለዉን አማኝ ትተን ወደ ሀገራችን ደቡብ ክልል ቤተ ክርስቲያን እምነቷን ብታስፋፋ ነጠላ ይዛ ልትዞር ነዉ; ወይስ አፋር ቢያምን በግልድም አትቀርብም ሊባል; ስለዚህ ማስተዋል እንጨምርበትና ሠርግን ወደ አንድ ለማምጣት ሁላችንም እሰኪ የበኩላችንን እንበል፡፡
ይሁንና ይሄ ማለት ነጠላ ለብሶ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አያስፈልግም ማለት ሳይሆን ቤተክርስቲያን ከሚለበሰዉ ነጠላ ሳይሆን ቅድሚያ ከነጠላዉ ስር ስላለዉ አካሉ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነዉን ምዕመን ቅድሚያ ይሰጠዉ ለማለት ነዉ፡፡
ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ አይደል ቃሉ፡፡
መቼም ነጠላ እቤቱ እያለ እንዲሁ ብሔድ ያለነጠላ በጃቴ ወይም በሱፌ ባስቀድስ ምናለበት ብሎ ራቁቱን የሚመጣ ሰዉበተወዉ ነጠላ ሳይሆንበልቡ ባለ ክፋት እግዚአብሔርን እንዳላከበረ ወይም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ህዝብ እንደማይሆን መናገር ላይከብድ ይችላል፡፡ ታዲያ በዚህ ሰዉ ላይ የሚወሰደዉ የተግሳፅ እርምጃ የእግዚአብሔር ፍቅር በዉስጣቸዉ እያለና እየተቀጣጠለ የሚለብሱት ነጠላ ስለሌላቸዉ ያለ ነጠላ የሚመጡ ሰዎችን ማስደንገጥ የለበትም፡፡
የማርያም እናት ሃና የምትለብሰዉ ልብስ ስለሌላት ከቤተ መቅደስ ልትቀር እንደነበር ተአምረ ማርያም ይነግረናል፡፡ (ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ገጽ 48)