Monday, September 30, 2013

የሞት ሽታ



ሞት ምን ምን ይሸታል አንዳንዴ ሰዎች ሞት ሞት ሸቶኛል ሲሉ እንሰማቸዋለን ምን ምን ሸቷቸው ይሆን፡፡
ሞት በቁሙ የህግ መተላለፍ ቅጣት የሀጢአት ውጤት ነው፡፡
በስጋዊ አፍንጫችን ስናሸት ለሚሸተተው ነገር በወጣለት እና በተሰጠው ህግ/ማንነት/ ብቻ እናሸተዋላን ወደ አፍንጫችን የሚገባው ሽታ መጥፎ መአዛ ካለው ይህ ሉሁሉም ሰው መጥፎ መአዛ ነው መልካም መአዛ ከሆነ ደሞ ለሁሉም ሰው መልካም መአዛ ነው፡፡ ከአንድ ኩሬ በአንድ ግዜ መራራና ጣፋጭ እንደማይቀዳ ሁሉ ማለት ነው፡፡ ይህ የስጋዊ አፍንጫችን እውነት ነው፡፡
በመንፈሳዊ ህይወት ግን እንዲህ አይደለም ከአንድ ነገር ላይ በማመን እና ባለማመን የህይወትን አና የሞትን ሽታ እናሸታለን
የሀዋርያው ጳውሎስን መልዕክት ስናነብ የምናገኘው እውነት ይህንን ያስረግጥልናል  
 በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነን፤ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያ ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን፡፡ 2ቆሮ 2፤15 
ጳውሎስ አንድ ነው ደቀ መዛሙርቱም እንደዚሁ፤ ነገር ግን የክርስቶስ መዓዛ ሲሆኑ ሁለት መዓዛ አላቸው የሞትና የሕይወት ሽታ፡፡ ቃላቸውን ለሚሰሙትና ለሚድኑት ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ለማያምኑባቸው ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ፡፡
የሐዋርያትን የአገልግሎት ዘመን ስንመለከት ልዩነቱ ገና ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ ቀን ጀምሮ ይጀምራል፡፡ የሐዋ.ሥ 2፤4 በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው መንፈስም ይናገሩት ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር፡፡ በሌላ ልኖችም ሲናገሩ የሚናገሩት ግስና ባለቤት ያለው ቋንቋ ስነበር ሁሉም በየራሳቸው ቋንቋ ሲናገሩ ይሰሙዋቸው ነበር በዚህም ተደነቁ ይህንን ያደረገውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ በዛችም እለት ከቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት የተነሳ ሦሥት ሺህ ነፍሳት አመኑ፡፡
በተቃራኒውግን በዚሁ ምእራፍ ቁጥር 13 ላይ ሌሎች ግን እየፌዙባቸው፡፡ ጉሽ የወይን ጠጅ ጠጥተዋል አሉ፡፡ የሚል ቃል እናገኛለን ከአንዱ የክርስቶስ መአዛ ላይ ሞትና ሕይወት ማሽተት እንዲህ ነው፡፡
ሉቃስ 7፤23 በእኔ የማይሰናከል ብፁዕ ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር ሲመጣ ለሁለት ነገር እንደመጣ ደጋግሞ ሲያስተምር እንደነበር ወንጌል ይነግረናል አንድም ለሞት አንድም ለሕይወት፡፡ ለዚህም ነው  በእኔ የማይሰናከል ብፁዕ ነው፡፡ ያለው
ማቴ 10፣34
በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልጣሁም፡፡ ሰውን ከአባቱ፤ሴት ልጅንም ከእናትዋ ምራትንም ከአማትዋ እለይ ዘንድ መጥቻለሁ፡፡
ዮሐ 9፤39 ኢየሱስም፡፡ የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩ እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጥቻለሁ፡፡
ሉቃ 2፤34-35 ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፤
እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚነግሩን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚጠፉትና በሚድኑት መካከል የሕይወትና የሞት መዓዛ/ሽታ/ እንደሆነ ነው፡፡
በክርሰቶስ የማያምኑትን አህዛብን አንኳን ትተን አንድ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበብን አንድ ጌታ ኢየሱስን እናመልካለን የምንል ህዝቦችን እንኳን ብንመለከት እጅግ ብዙ ቦታ ተሰነጣጥቀን ብዙ ቤተ እምነቶችን አቋቁመን እንታያለን፡፡
በነዚህ  ቤተ እምነቶች ሁሉ ክርስቶስ የሚሰበክ ቢመስልም ሥሙ እየተጠራ ተአምራት የሚደረግ ቢመስልም ሁሉም ከክርስቶስ መልካሙንና የሕይወት መአዛ አሽቶአል ማት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም
በኢየሱስ ክርስቶስን ማመን ስሙን መጥራት በስሙ ተአምራትን ማድረግ ጭምር  በራሱ ብቻ የክርስቶስ መሆንን አያመለክትም፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላልና፡፡
ማቴ 7፤21 በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆን ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግስተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ ቁጥር 23 ከቶ አላውቃችሁም፤እናንተ አመፀኞች ከእኔ እራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ፡፡
ክርስቶስ በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ ሁልት ሽፍቶች አንዱ በቀኝ ሌላው በግራ ተሰቅለው ነበር ሁለቱም ክርስቶስን ከግራና ከቀኝ እኩል ያዩትም ነበር፡፡ ነገር ግን ከክርስቶስ ላይ አንዱ ሕይወትን ሌላኛው ሞትን ያሸቱ ነበር፡፡ ዛሬም በስሙ እናምናለን የምንል  ሁላችን እንዲሁ ክርስቶስ በቀራንዬ በመስቀል በተሰቀለ ጊዜ ከግራና ከቀኙ እንደተሰቀሉት ሁለት ሽፍቶች በሁለት አቅጣጫ እናየዋለን አንዳችን ለሕይወት ሌላችን ለሞት ክርስቶስ ለአንዳችን ለህይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ለአንዳችን ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ነው፡፡
2ነገ 3-22 ላይ የሞአብ ንጉስ የሞሳ እና የአክአብ ልጅ የኢዮራም ታሪክ ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ስላለው እዚህጋ እናንሳው
የሞአብ ንጉስ ሞሳ ለእስራኤል ንጉስ አክአብ ከበጎች ጠጉር ግብር ይገብር ነበር ነገር ግን ንጉሱ አክአብ ሞቶ ሊጁ ኢዮራም በተተካ ግዜ ግን ንጉስ ሞሳ አልገብርም ብሎ አመጸ በዚህ ግዜ ንጉስ ኢዮራም የይሁዳ ንጉስ ኢዮሳፍጥን እና የኤዶምያስን ንጉስ አስከትሎ ወደ ሞአብ ዘመተ በኤዶምያ በረሃ ሰባት ቀን ከተጓዙ በኋላ ግን ውሃ ጠፋ ሶስቱ ነገስታትም ተጨነቁ  እግዚአብሔር ግን በነቢዩ ኤልሳዕ እንዲህ አላቸው ንፋት አታዩም ደመናም አታዩም እግዚአብሔር ግን ይህንን ሸለቆ በውሃ ይሚላል ይህም በእግዚአብሔር አይን ፊት ቀላ ነው አላቸው፡፡ በማግስቱም ሸለቆውን ውሀ ሞላው ለሦሥቱ ነገስታትም  የሕይወት ውሃ ሆነላቸው፡፡ በማለዳም ሞአባውያን ሶስቱ ነገስታት ሊወጓቸው እንደመጡ ሰምተዉ በተራራ ላይ ተከማቹ በማለዳም ሲመለከቱ ውሀው ደም መስሎ ታያቸው እንዲህም አሉ ሦስቱ ነገስታት እርስ በርሳቸው ተዋግተዋል ደማቸውም ይኸው እንግዲህ ሞአብ ሆይ ለምርኮ እንውረድ ብለው ወረዱ ሦስቱ ነገስታትም ከተማቸውን እስኪያጠፉ ድረስ መቷቸው፡፡ ይለናል ታሪኩ
በኤዶምያስን ሸለቆ የሞላው ውሃ አንድ ውሃ ነው ነገር ግን እስራኤል በዚህ ሞአባውያን ከዚያ ሆነው ሲያዩት ግን ልክ ክርስቶስን በሁለት አቅጣጫ በመስቀል ላይ ሲያዩት እንደነበሩ ሁለት ሽፍቶች ሕይወትና ሞት አሸተቱበት፡፡
ደቀመዛሙርቱ
ቅዱሳኑ
መላእክቱ
ድንግል ማርያም
ቤተ ክርስቲያን
በሚጠፉትና በሚድኑት መካከል ለእግዚአብሔር የክርስቶስ በዓዛዎች ናቸው፡፡ ለነዚህ ለህይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ለነዚያ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ
እኛስ ከዚህ ምን ሸቶን ይሆን ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ወይስ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
መ/ር ሰሎሞን ፋንቱ

Sunday, September 15, 2013

ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔዶም ገነት አስወጣው፡፡



አዳን ከኤዶም ገነት ልምን ተባረረ
ብዙዎች አዳም ከኤዶም ገነት የተባረረው እፀ በለስን ስለበላ፤ህግ ስላፈረሰ፤አትብላ የተባለውን ስለበላ፤ የእግዚብሔርን ትእዛዝ ቸል ስላለ የመሳሰሉ መልሶችን ሰተውኛል፡፡
ይህንን ትምህርት ሁላችንም መጀመሪያ የምንሰማው የምንማረው እውነት ነው ማንም ቢጠየቅ መጀመሪያ የሚመልሰው ይህንኑ ነው፡፡ በእርግጥ መጽሐፉ አዳም ስለተባረረበት ነገር ምን ይላል፡፡ አዳምን ከኤዶም ገነት እንዲባረር ያደረገው ፍቅር ነው ብንልስ አዎ አዳምን ከኤዶም ገነት እንዲባረር ያደረገው በእግዚአብሔር በመፈለጉ እና በመፈቀሩ ነው፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ አላማ የእግዚአብሔርን ፍቅር መናገር ነው፡፡ ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምረን እስከ የዮሐንስ ራዕይ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን ብናነበው የሚነግረን የእግዚአብሔርን ፍቅር ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ፍቅሩን የገለጸበት ማህደሩ ነው መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር የፍቅሩ መግለጫ ክታቡ ነው የሚሉት፡፡ ሁላችንም በየእለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ያለብን እግዚአብሔር ምን ያክል እደሚወደን እንድንረዳና እንድናውቅ ጭምር ነው፡፡ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚውደን ለመመስከር መጽሐፍ ቅዱስን ማነበብ ይገባናል፡፡ ፍቅር የሚለው ቃል እንደወረደ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ቦታዎች ላይ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡
በኦሪት ዘፍጥረት 34፤3

ልቡናውም በያዕቆብ ልጅ በዲና ፍቅር ተነደፈ፥ ብላቴናይቱንም ወደዳት፥ልብዋንም ደስ በሚያሰኛት ነገር ተናገራት። ከሚለው የዘፍጥረት መጽሐፍ እሰከ ትንቢተ ሆሴዕ ምዕራፍ 11፤4


በሰው ገመድ በፍቅርም እስራት ሳብኋቸው ለእነርሱም ቀምበርን ከጫንቃቸው ላይ እንደሚያነሣ ሆንሁ፥ ድርቆሽም ጣልሁላቸው። እሰከሚለው የብሉይ ከዳን መጽሐፍ 40 የሚያክ ቦታዎች ሲጠቀስ በአዲስ ኪዳን ደሞ



ከማቴዎስ ወንጌል 24፤12

ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች።ከሚለው ጥቅስ ተነስተን

የዮሐንስ ራእይ 2፤19




ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ።





እስከሚለው  የዮሐንስ ራእይ የትንቢት መጽሐፍ ድረስ 94 ቦታዎች ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ ይሁንና እነዚህ ቃላት በቀጥታ ከሚገልጹልን ፍቅር ይልቅ እግዚአብሔር በማድረጉና በሠራቸው ሥራዎች የገለጣቸው ፍቅሮች ብዙዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው አዳምን ከኤዶም ገነት ማስወጣቱ ነው፡፡ ምናልባት እንዴት ተድላና ደስታ ከሞላበት የእግዚአብሔርን ድምጽ እየሰማ ከሚያመሰግንበት ከኤዶም ገነት እያስወጣው እንዴት ፍቅሩን አሳየ የምንል ሰዎች እንኖር ይሆናል፡፡ አዳም ከገነት ስለተባረረበት ትክክለኛ ምክንያን መጽሐፍ ቅዱሱ እንዲህ ይላል፡፡ ኦሪት ዘፍጥረት 3፤22

እግዚአብሔር አምላክም አለ። እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፥ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔዶም ገነት አስወጣው፡፡
ስለዚህ ተብሎ የተጠቀሰው አዳም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር ነው፡፡ ስለዚህ አዳን ከገነት ለመባረሩ እፀ በለስን መብላቱ ህግ ማፍረሱ ምክንያት ይሁን እንጂ ከገነት የተባረረው ትክክለኛ ምክንያት ግን ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ እና ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር ነው፡፡
በዚህ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔር ፍቅር ማየት ቀላል ነው፡፡ አዳም ህግ ማፍረስ አለመታዘዝ የእግዚአብሔርን ጸጋ መናቅ በውስጡ እያለ በአጠቃላይ በሀጢአት ወድቆ ፤ተይዞ ለዘላለም የምታስኖረዉን እፀ ህይወት ቀጥፎ ቢበላ ኖሮ ኑሮው ሁሉ እንደ አጋንንት/ሰይጣን/ ይሆን ነበር፡፡ ሰይጣን ህያው ነው ለዘለላለምም መኖር ይችላል፡፡ የአዳምም እጣ ይህ እዳይሆን እግዚአብሔር የአዳምን አለመታዘዝና ሀጢአት ከውስጡ አጥቦ አሶግዶ ንፃህ ባህሪዉን ከመለሰለት በኋላ ለዘለአለም የሚያኖረውን የህወት እንጀራ ስጋውን ቆርሶ እስኪሰጠው ድረስ ከገነት ገለል አደረገው፡፡ ለዚህም ነው የክርስቶስን ስጋ መልበስና መምጣት ተንተርሶ ዮሐንስ በመልእክቱ ሲጽፍ 
በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ያለው 1 ዮሐንስ መልእክት 4፤9 የሚገለጥ ያለና የነበረ ነገር ግን የተሸፈነ እውነት ነው፡፡ ይህም አዳምን ከገነት ገለል ያደረገበት እውነተኛ ፍቅር ልጁ በመወለዱ ተገለጠ ይለናል፡፡
ወስብሀት ለእግዚአብሔር
የእግዚአብሔር ፍቅሩ አይለየን
መ/ር ሰሎሞን ፋንቱ
መልስ ለሰጣችሁኝ ለበረታችሁኝ ለመልካም ምኞታችሁ ታላቅ ክብር አለኝ

Wednesday, September 11, 2013

አዳም ከኤዶም ገነት የተባረረው ለምንድን ነው?

በሁሉም አካባቢ ለምትገኙ የፌስቡክ ጓደኞቼ በመጀመሪያ እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ በሰላም አሸጋራችሁ ዘመኑ የሰላም የፍቅር የመተሳሰብና የሰላም ይሁንላችሁ፡፡
አሮጌ አመት አልፎ አዲስ ዘመን ሲመጣ ሁሉም ሰው በአዲስ ሀሳብ በአዲስ እቅድ ዘመኑን ለመቀላቀል ይወስናል በአመቱ ውስጥ ሊሰራቸው የሚፈልጋቸውን ሥራዎች ይነድፋል እንዲከናወኑለት ይፀልያል ለተግራዊነታቸውም ቃል ይገባል፡፡
ምን ያህሉ ባለመውና ባቀደው በነደፈው እቅድ እንደሚመራ ልብ ይቁጠረው፡፡
ከብዙ የፌስቡክ ጓደኞቼ ጋር በውስጥ ገጽ ብዙ እናወራለን እንመካከራለን ጥያቄና መልሶችንም እንለዋወጣለን፡፡ ታዲያ እነዚህ ጓደኞቼ ጥያቆዎቻችንን ለምን በፊት ገጽ አናደርጋቸውም ምንአልባት እኮ አንድ ሰው ሊማርባቸው ይችላል ብለውኝም ነበር በዚህም የተነሳ መ/ር ሰሎሞን ፋንቱ የምትል ገጽ ከፈትኩና እሁን ብዕራቸው ያማረ ምክራቸው የሰመረ ትምህርታቸው የጠነከረ ብዙ ፀሐፊዎች ባሉበት አሁን እኔ? ብዬ ተውኩት ጥቂቶች ታዲያ የያዘውን የወረወረ እኮ ብለው ስላሉኝ በዚህ ዓመት እኔስ ለምን የምችለውን ያክል ለመጻፍ አልሞክርም ብዬ አቀድኩ ወሰንኩም የመጀመሪያውን ሃሳብ በማንሳትም እቅዴን አንድ ብዬ ተግባራዊ አደረኩ እግዚአብሔር ይርዳኝ፡፡
እኔ ለጥያቄዎች መልስ ለመስጠት  ለመምከርና ለመጻፍ ስነሳ በዚህ የመጻፊያ መሳሪያ ከሚጽፉ ወንድሞቼ የተሻለ እውቀት ኖሮኝ የእውቀት ክፍተታቸውን ለመሙላት አይደለም ይልቁንም የሥራ ፀባዬ ከዚህ የመጻፊያ መሳሪያ ጋር የተገናኘ በመሆኑ የግዜ ክፍተታቸውን ሊሞላ ይችል ይሆናል፡፡
በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ዓመትና የመጀመሪያ የመነሻ ሃሳብ የመጀመሪያዉን ሰው ብናደገውስ  
በጥያቄ ልነሳና የብዙዎቻችሁን መልስ ካየሁ በኋላ ታናሻችሁ የምሆን እኔ ደሞ ሃሳቤን ገልጣለሁ
አዳም ከኤዶም ገነት የተባረረው ለምንድን ነው?

ምክንያታዊ መልስ እፈልጋለሁ አደራችሁን ጥያቄዬን እንዳትንቋን ምናልባት መልሱን ካገኛችት . . . . . ሁላችሁም ተሳተፉበት