ካለፈው የቀጠለ
4. የተጠራንበትን ጥሪ ማወቅ
ሰዎች በክርስትና ህይወት የተረጋጋና የሰከነ ህይወት ኖሯቸዉ እንዲጓዙ
ከሚያስችሉዋቸዉ ነገሮች አንዱ የተጠሩበትን ጥሪ ማወቅ ነዉ፡፡ ወደ ክርስትና የመጡ ሁሉ ተጠርተዋል፡፡ ለምን እንደተጠሩ ማወቅ ደግሞ ለተጠሩበት አጠራር የቀና ጎዳና
ይሆንላቸዋል፤ ነገር ግን የተጠራንበትን ጥሪ ሳናዉቅ በራሳችን ፍላጎት ብቻ ሰልፍ እየገባን እኛ ግራ ተጋብተን ሰዉ ግራ የምናጋባ ብዙዎች ነን፡፡ ‹‹ወንድሞች ሆይ
መጠራታችሁን ተመልከቱ›› 1ቆሮ 1÷26
እግዚአብሔር ሰዎችን ለተለያዩ አገልግሎቶችና
/ተልዕኮዎች/ ይጠራል እነርሱም
·
ለህይወት የሚጠራቸዉ አሉ
·
ለምህረት የሚጠራቸዉ አሉ
·
ለአገልግሎት የሚጠራቸዉ አሉ
·
ለንስሀ የሚጠራቸዉ አሉ
4.1 ለህይወት የሆነ ጥሪ
አዳም እንደተጠራበት ያለ ጥሪ፡፡አዳም የእግዚአብሔርን ፀጋ ንቆ አምላክነትን ተመኝቶ እፀበለስን በበላ ጊዜ እንደተመከረዉ አይኑ ቢገለጥለትም ያየዉ ግን ብርሃን አልነበረም ጨለማን እንጂ፡፡ የአምላክነት መጎናፀፊያ ሲጎናፀፍ አይደለም የልጅነት ፀጋዉ ሲገፈፍ እንጂ፡፡ እርቃኑን እንደሆነ ተመለከተ፤ አፈረ፡፡ ከበለስ ቅጠልም ቆርጦ አሸረጠ እፍረቱንም ከለለ ነገር ግነ እርቃኑን ያስቀረዉ የበለስ ፍሬ ነዉና ቅጠሉም ሊከልለዉ አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ነዉ በገነት ዉስጥ የህይወት
ጥሪ ያስተጋባዉ ሁሉን የሚያዉቅ አምላክ አዳም የተደበቀበት ጠፍቶት ሳይሆን በምን ሁናቴ ላይ በየትኛዉ ቅድስናና የሃጢአት ደረጃ ላይ እንዳለ ይጠይቀዉ ዘንድ ስለወደደ አዳም አዳም ወዴት ነህ; አለዉ፡፡ አዳምም አዚህ ተደብቄያለሁ አለዉ፡፡ እግዚአብሔርም አዳም ያለበትን አዉቋልና ለአዳም አዘነለት፤ ወደደዉ ተድላና ደስታ ካለበት ከገነት አባረረው፡፡ ይህም እግዚአብሔር አዳምን ምን ያክል እንደሚያፈቅረዉ ያሳያል፡፡ ዘፍ 3÷10
ብዙዎች እግዚአብሔር አዳምን ተድላና ደስታ ካለባት ገነት ስላባረረዉ እንዴት ያፈቅረዋል ልንል እንችላለን ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ነገር ግን በማስተዋል ብንመረምር አዳም አመፀኛ ከመሆን ጋር ህግ አፍራሽ ከመሆኑ ጋር አምላክ ለመሆን ካለዉ ምኞት ጋር ለዘላለም መኖር ቢችል ኖሮ ኑሮዉ ሁሉ ክፋትን ተሞልቶ ከሚኖር ከአጋንንት ጋር ይመሳሰል ነበር፡፡
ብዙ ሰዎች አዳም ከገነት የተባረረዉ እፀበለስ ስለበላ ብቻ ነዉ ብለዉ ያምናሉ፡፡ ይሁንና መፅሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን አዳም እፀበለስን ስለበላ ብቻ አይደለም ከገነት የተባረረዉ እፀበለስን መብላቱ መነሻ ቢሆንም መፅሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ብሎ የሚነግረን ግን እግዚአብሔር አምላክም አለ #እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ አሁንም
እጁን እንዳይዘረጋ ደግሞም
ከህይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ ለዘላለምም ሕያዉ ሆኖ እንዳይኖር ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔደን ገነት አስወጣዉ$ ዘፍ፣3፡ 22
ስለዚህ እግዚአብሔር አዳምን ከገነት ያስወጣበት ምክንያትና መነሻዉ እፀበለስን መብላት ይሀን እንጂ ስለዚህ ብሎ እንደነገረን የህይወትን ዛፍ በልቶ ከነክፋቱ ለዘላለም መኖር እንዳይችል ነዉ፡፡ ይልቁንም አለመታዘዙን በመታዘዝ፣ ክፋቱን በበጎነት ለውጦ አምላክ የመሆን ምኞቱን አሟልቶ በቀራንዮ ተሰቅሎ ለዘላለም የሚኖርበትን የህይወት እንጀራ እስኪሰጠዉ ድረስ ከገነት ገለል አደረገዉ፡፡ ለዚህም ነዉ ሐዋርያዉ ዩሐንስ #የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ አለም ልኮታልና$ ያለው 1ዩሐ 4÷1
የሚገለጥ ያለና የነበረ ነገር ግን የተከደነ ነገር ነዉ፡፡ በዚህ
ለሕይወት በሆነ ጥሪ እኛስ ወዴት ነን;
4.2 ለምህረት የሆነ ጥሪ
ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 19 ላይ የምናገኘዉ ታሪክ የአብርሃምን የአጎት ልጅ የሎጥን ታሪክ ነዉ፡፡ በዚህም
እግዚአብሔር ለሎጥ የምሕረት ጥሪ እንዳደረገለት እንመለከታለን፡፡
በአብርሃምና በሎጥ ንብረት /////ከብቶች/ መብዛት እረኞቻቸዉ እየተጣሉ ችግሩ ወደ ጌቶቻቸው ከመምጣቱ በፊት አብርሃም ሎጥን አለዉ፡፡ እኔና አንተ ወንድማማቾች ነን፡፡ በእኔና በአንተ በእረኞችህና በእረኞቼ መካከል ፀብ እንዳይፈጠር አይንህን አቅንተህ ወደ ወደድከዉ ሂድ፡፡ አንተ ወደ ቀኝ ብትሄድ እኔ ወደ ግራ አሄዳለሁ አንተ ወደ ግራ ብትሄድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ ባለዉ ጊዜ ሎጥ አይኑን አቅንቶ ተመለከተ የሰዶምና ገሞራ ሰዎች ስጋዊ ፍላጎታቸዉ ተቀጣጥሎ ነዶ ሀገሪቷንም ከማጥፋቱ በፊት እስከ ዞዓር ድረስ እንደ ምድር ገነት ያማረች ነበረች፡፡ ሎጥም አይቶ ወደዳት ወደእርሷም ሄደ፡፡ ነገር ግን የሰዶም ሰዎች ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጥያተኞች ነበሩ፡፡
ሎጥ የሚሄድበትን ሲወስን የዉሃዉን በዚያ መሙላት የሳሩን ልምላሜ ድመቀቷን እንጂ እግዚአብሔርን አላሰበም አላስቀደመም፡፡ ስለዚህ በአይኑ ላየዉ ልምላሜ ተገዝቶ ከአህዛብ፣ ከክፉዎች፣ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጢአተኞች ከሆኑት ጋር ተቀላቀለ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘ ነበርና ነፍሱ በእጅጉ ተጨነቀች፡፡
ብዙዎቻችን የሎጥ አይነት ህይወት ያጋጥመናል፡፡ የምንነግድበትንና የምናተርፍበትን የምናርስበትንና ለምለም የሆነዉን ምድር ከመምረጥ ዉጪ እግዚአብሔርን አናስቀድምም፡፡ ብዙዎቻችን ትዳራችንን ስንፈፅም እንኳን የወርቅ እንክብል ወደሞላበት ተድላና ደስታ የሰፈነበት ወደሚመስለን ቤተሰብ እንገባለን፡፡ በዚህ የትዳር ህይወቴ እግዚአብሔርን አላስደስተዉ ይሆን; ብለን ለማሰብ ጊዜም የለንም፡፡ እጅግ የሚያሳዝነዉና የሚያሳፍረዉ የቤቱ አገልጋይ ነን የምንል እንኳ በዚህ ከንቱ ሀሳብ ተጠምደን መንፈሳዊ ህይወታችንን ወጥመድ ዉስጥ የምንከት መኖራችን ነው፡፡
ከአህዛብ ጋር ተቀላቅሎ ነፍሱ እንደተጨነቀችበት እንደሎጥ ለኑሮአችን ማማርና መሳካት
እግዚአብሔርን ደስ ከማያሰኙት ጋር ተቀላቅለን ግብራቸዉን ስንከተል ስንፈፅምና እግዚአብሔርንም ስናሳዝን የምንኖር ጥቂቶች አይደለንም፡፡
ሎጥ ከአህዛብ ጋር ተቀላቅሎ ነፍሱ ኃጢአታቸዉን ተፀይፋ በሚኖርበት በዚያች ምድር የህዝቡ ኃጢአት በርክቶ በእንግድነት ወደ ሎጥ ቤት የመጡትን የእግዚአብሔር መላእክት በሩካቤ ስጋ ካላወቅናቸዉ ብለዉ እምቢ ስላሉ ‹‹ጥፊ ያላት ከተማ ነጋሪት ቢጎሰምባት አትሰማ›› ነዉና
የእግዚአብሔር ቅጣት የተገባቸዉ በመሆኑ የሰዶም ከተማ እጅ ሳይነካት በተገለበጠች በእግዚአብሔር የትኩሳቱ ሀይል በቀለጠች ጊዜ ለሎጥ የምህረት ጥሪ ደረሰዉ #ተነሣ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ዉሰድ፤ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፋ እያሉ ያስቸኩሉት ነበር$ ዘፍ 19÷15
4.3 ለአገልግሎት የሆነ ጥሪ
Xeእግዚአብሔር የሚያገለግሉትን ከማህፀን ጀምሮ ይመርጣቸዋል ከአህዛብ ይለያቸዋል ሃይልና ብርታትን ይሰጣቸዋል፡፡ አገልግሎቱም ብዙ ነዉ ለምስጋና አገልግሎት የሚጠራ፣ ለትንቢት የሚጠራ፣ ለማስተማር የሚጠራ፣ ህዝቡን ከመከራ ለማላቀቅ የሚጠራ አለ፡፡
ከእነዚህ መካከል ሙሴ አንዱ ነዉ፡፡ በረሃብ ምክንያት ወደ ግብፅ የወረዱ እስራኤል ግብፃውያን ታላቅ መከራ አብዝተዉባቸዉ ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ የከፋዉ ህፃናት ሲወለዱ እንዲገደሉ የወጣዉ አዋጅ እና ዛሬ ግብፅ በአለም መድረክ የምትታወቅባቸው ፒራሚዶቿ የተሰሩት በእስራኤላዉያን ላብና ደም መሆኑ ነዉ፡፡ ለፒራሚዱ መስሪያ የሚሆን ጭቃ የእስራኤል ወንዶች እንዲረግጡ ግድ ነበረባቸዉ፡፡ ጭቃ ሲረግጥ የዋለው እብራዊ በድካም ገብቶ ጥቅልል ብሎ
እንዲያድር እንጂ ከሚስቱ ጋር እንዳይገናኝና እብራውያን በመዋለድ እንዳይበዙ ሆነ ተብሎ የተሰራ የግብፃውያንን ጥበብ ያዘለ ህግ ነዉ፡፡ ከዚህም በላይ ባሎቻቸዉ የሞቱባቸዉ እብራውያን ሴቶችም በባሎቻቸዉ ምትክ ጭቃ እንዲረግጡ ህግ ተጥሎባቸዉ ነበርና ባሎቻቸዉ ከሞቱባቸዉ እብራውያን መካከል መንታ ልጆችን አርግዛ የመዉለጃ ጊዜዋ የደረሰዉ ራሔልም በባሏm ምትክ ለዚህ ተጠራች፡፡ በእብራውያን የባርነት ታሪክ የከፋዉና እግዚአብሔርም ህዝቡን በምህረት አይን እንዲያይ ምክንያት የሆነዉ ይህ የራሔል ጭቃ ለመርገጥ የተጠራችበት ጊዜ ነበር፡፡
ራሔል ጭቃ እያቦካች ሳለ የምትወልድበት ጊዜ ደረሰ ምጥም መጣባት አሰሪዋንም ልጆቿን ወልዳ የምትመጣበትን ጥቂት ጊዜ ለመነችዉ ባርነት ክፉ ነዉ፤የምንበላዉን ከጌቶቻችን እጅ ያስለምነናል ባርነት ክፉ ነዉ፤ ለማረፍ ፍቃድ ያስፈልገናል ፍቃድ ያስለምነናል ባርነት ክፉ ነዉ፤ የምጥ ጊዜ ሲመጣ እንኳን ለመዉለድ ፍቃድ ከጌቶቻችን (ካሳዳሪያችን)
ያስለምነናል፡፡ በኃጢአት ባርነት መያዝ ደግሞ ከዚህ ይከፋል፡፡
ዛሬ ለጊዜዉ ምስጋና ይግባዉና እናቶቻችን እህቶቻችን የመዉለጃቸዉ ጊዜ ሲደርስ የወሊድ ፍቃድ ይሰጣቸዋል፡፡ ምጥ ከባድ ነዉና መፅሐፍ የምጥን ከባድነት እንዲህ ይገልፀዋል፡፡
#ህዝብ በህዝብ ላይ መንግስትም በመንግስት ላይ ይነሳልና ረሀብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፡፡ እነዚህ ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸዉ፡፡$ ማቴ 24፣ 3-8
እንግዲህ አስተዋይ ያስተዉል ይህ ሁሉ መከራ የምጥ መጀመሪያ ከሆነ የምጥ መጨረሻው ምን ይሆን; እንዲህ በከበደ ምጥ የተያዘች ራሔል አለቃዋን ብዙ ጊዜ አልጠይቅህም ሰዉ ዕቃ እንደሚያስቀምጥ ልጆቼን ወልጄ ልምጣ ብላ ብትማፀነዉም በጭካኔ የተሞላ የነፍሰ ጡር ሃዘን እንኳን ልቡን ሰርስሮ ሊገባለት እምቢ ያለዉ ግብፃዊ በጭካኔ ተሞልቶ እዚያው ውለጃቸዉ እዚያው እርገጫቸው የእስራኤል ደም ጭቃውን ያጠነክረዋልና አላት፡፡ ራሔልም ልጆችዋን እዛዉ ወለደቻቸው እቅፏን እንደማይናፍቁ ጡቷን እንደማይሹ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህፀኗ እንዳልተቀመጡ በባርነት ህይወት ያለች የመውለድ ፍቃዷን እንኳን ከግብፃዊ አሠሪ የምትለምነውና ያጣችው ምስኪኗ ራሔል ልጆቿን እዚያው ወለደቻቸው እረገጠቻቸውም፡፡
በዚህ ጊዜ ራሔል አምርራ አለቀሰች፤ እንባዋንም ወደ ሰማይ ረጨች #ኢሃሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እስራኤል አዶናይ$ ለመሆኑ ሁሉን የምትችል የእስራኤል አምላክ በዚህ አለህ; ይህንን ግፍ ትመለከታለህ;
ብላ አለቀሰች፡፡
#አሜሃ ተፈፀመ ዘተብህለ በኤርሚያስ ነቢይ እንዘ ይብል ቃል ተሰምዓ በራማ ራሔል እንዘ ትበኪ በእንተ ውሉዳ ወዓብየት ተናዝዞ ወነጊፈ ላህ እመ ኢኮንዋ ውሉዳ ውሉደ$ ማለትም ያን ጊዜ ኤርምያስ ቃል በራማ ተሰማ ብሎ የተናገረዉ ትንቢት ደረሰ ተፈፀመ፡፡ #ራሔል ለልጆቿ ስታለቅስ ለቅሶ መተውን መፅናናትን እምቢ አለች፤ ልጆቿ ልጆች አልሆኗትምና$ ኤር 31÷15
#ድምፅ በራማ ተሰማ ለቅሶና ብዙ ዋይታ ራሔል ስለልጆቿ አለቀሰች መፅናናትም
አልወደደችም ልጆቿ የሉምና$ ማቴ 2÷17
የራሔል እምባ የመላዕክትን ከተማ ረበሸ መንበረ ፀባኦት ደረሰ እግዚአብሔር ለህዝቡ አዘነ የራሔልንም እምባ ተመለከተ፡፡ ሙሴን ያገለግለዉ ዘንድ እግዚአብሔር ለአገልግሎት ጠራዉ፡፡
#አሁንም እነሆ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ እንደወጣ ግብፃውያንም
የሚያደርሱባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ አሁንም ና ህዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ታወጣ ዘንድ
ወደ ፈርኦን እልክሃለሁ$ ዘጸ 3÷9
ሌዋዉያንን እግዚአብሔር ከህዝብ ሁሉ መርጦ ለአገልግሎት መርጧቸዋል፤ አዘጋጅቷቸዋል፡፡ #እኔም እነሆ ሌዋዉያን ወንድሞቻቸሁን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ የመገናኛዉን ድንኳን አገልግሎት ያደርጉ ዘንድ ለእግዚአብሔር የተሰጡ ለእናንተ ስጦታ ናቸዉ$ ዘኁ 18÷6
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነቢዩ ኤርሚያስን ከማህፀን ጀምሮ የጠራዉ ያዘጋጀዉ መሆኑን መጽሀፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ #በሆድ ሳልሰራህ አውቄሀለሁ ከማህፀን ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ ለአህዛብም ነብይ አድርጌሃለሁ$ ኤር 1÷5
4.4 ለንስሀ የሆነ ጥሪ
የነነዌ ሰዎች የተጠሩበት ጥሪ ለንስሃ ጥሪ ተጠሪዎች ቀዳሚ ሆኖ ቢጠቀስ የተመቸ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ከፊቱ ስላገኘኝ ነዉ ያስቸገረኝ ብሎ የነነዌ ህዝብን ለንስሀ እንዲጠራ የታዘዘው ነቢዩ ዮናስ የነነዌ መንገድን ትቶ ወደ ተርሴስ ባቀና ጊዜ በሁሉ ያለና የሚኖር የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዮናስን ማርኮ ወደ ነነዌ መለሰዉ፡፡ ዮናስም መሸነፉን አምኖ ተቀብሎ ለነነዌ ህዝብ የንስሃ ጥሪ ባሰማ ጊዜ ንጉሱ ከዙፋኑ
ወርዶ አመድ ለበሰ ትቢያ ነሰነሰ በነነዌ ያሉት ህዝቦች ብቻ ሳይሆኑ ጥጆች እንኳ የእናታቸዉን ጡት እንዳይጠቡ፤ ከብቶችም ከበረታቸዉ እንዳይወጡ የፆምን አዋጅ አወጀ ሁሉም በንሰሀዉ ጥሪ በፆሙ ዓዋጅ ተሳተፉ፡፡ የፀሎታቸዉም ኃይል ከሰማይ በኃጢያታቸዉ ምክንያት የመጣውን የእሳት ዲን ገፍቶ መለሰው፡፡
ዛሬ የሚያሳዝነው በሀገር ላይ መከራ ሲመጣ ፀሎትን የሚያውጅ የሀገር መሪ የራቀን ቢሆንም እረኞቻችንም እንኳ በእንዲህ ያለ የነነዌ የንስሀ ጥሪ ለፀሎት የማይጠሩን የማይጋብዙን ጊዜ እየበዛ መጥቷል፡፡ ኢየሱስ
ክርስቶሰም አህዛብ ሁሉ ወንጌልን በማመን ወደ ምህረት ይሳቡና ወደ አምላካቸው ዘወር ይሉ ዘንድ የንስሀ ጥሪ አስተላልፏል፡፡ #ነስሁ ወእመኑ እስመ ቀርበት ይእቲ መንግስተ ሰማያት፡፡ መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሀ ግቡ$ማቴ 4÷16
ዛሬም ሁላችንም በተላያየ መልኩ የተጠራን ሲሆን የተጠራንበትን ማወቅና ለምን እንደተጠራን መረዳት እንጂ እርሱ ጥሪው ለበጎ ነው፡፡
#እግዚአብሔርን ለሚወዱት እንደሃሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናዉቃለን አስቀድሞም የወሰናቸዉ
እነዚህን ደግሞ ጠራቸዉ$ ሮሜ 8÷30
የእግዚአብሔር የጥሪዉ ድምፅ ወደ ልቦናችን ገብቶ ወደ ፍቅሩ ሲስበን ለምን እንደተጠራን ልናዉቅ ይገባናል፡፡
ብዙዎቻችን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንጠራለን ነገር ግን ለምን እንደተጠራን ባለማወቅና ባለመረዳት ስንሰናከል በከንቱ ስንፈተንና ስንወድቅ እንታያለን፡፡ ለመዘመር የተጠራን ለመስበክ፣ ለመስበክ የተጠራን ለመቀደስና ለመባረክ መዘጋጀት ጥሪያችንን ካለማወቃችን በላይ በከንቱ እንፈተናለን፡፡ ለፈተናም እንሆናለን፡፡ ጥቂት የማንባል አገልጋዮችም ያለ ጥሪያችን ብቅ በማለት እራሳችንንም ሆነ ሰሚዎቻችንን ይዘን ወደ ጥፋት እንሳባለን፡፡ #ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ በእነዚህ ፅና ይህንን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ$ 1ጢሞ 4÷16
ሁላችንም ተጠርተናል ደሃ፣ ሀብታም፣ ቀይ ጥቁር ሳይል ሁላችንንም ጠርቶናል ሁላችንም ግን የፅድቅ ፈተና ተፈትነን ለማለፍ ለመከራ ተጠርተናል ስለ እርሱ መከራ
ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም ፊልጵ 1÷29
ኃጢአት አድርጋችሁ ብትታገሱ ምን ክብር አለበት;
ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሱ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል የተጠራችሁትም ለዚህ ነዉና 1ጴጥ 2÷20 -
21
ለዚህም ነዉ ክርስቶስ ኢየሱስ መስቀሉን የማይሸከም በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባዉም ያለዉ ማቴ 10÷38 መቼም መስቀሌን የማይሸከም ሲል የተቀበልኩትን መከራዬን በስሜ የማይቀበል ማለቱ እንጂ እንጨት እንድንሸከም እንዳልጋበዘን ግልፅ ነዉ፡፡
ነገር ግን ብዙዎች ወደ ክርስትና ህይወት መቅረብን ከሚፈሩበት ጥቂት ነገሮች አንዱ መከራን ወይም ፈተና መቀበልን ከመሳቀቅ የተነሳ ነዉ፡፡ መከራ ሲባል ትናንት እንደነበረዉ ዘመን በምስማር የምንቸነከርበት በመጋዝ የምንሰነጠቅበት በወፍጮ የምንፈጭበት ያለ አይነት መከራ ዛሬ የለምና ምን አይነት መከራ ያስብል ይሆናል፡፡ ዛሬ በዘመናችን ብዙ አይነት ፈተና ያለ ቢሆንም ዓለምን እያሸነፈ ያለውን የዝሙት ጦር መቋቋም በራሱ ታላቅ ፈተና ነዉ፡፡ በረከታቸው ይድረሰንና የሸዋ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ የነበሩት አቡነ ጎርጎሬዎስ #የስጋን ፍላጎትን መግታት በራሱ ለአክሊል የሚያበቃ ሰማዕትነት ነዉ$ የሚሉትም ከዚህ የተነሳ ነበር፡፡
ጌታ ሆይ መከራዉን የማልፈዉ ፈተናዉን የምችለዉ አድርግልኝ ብሎ መፀለይ እንጂ ሳይፈተኑ ማለፍ የለም፡፡
ይህ ብቻ አይደለም ፈተናዉ በጨመረ ቁጥር ከመሰቀቅ ከመከራው ጽናት የተነሳ ከመንገሽገሽ ይልቅ መረዳት ያለብን ወደ እግዚአብሔር እየቀረብን መሆናችንን ነዉ፡፡ ለምሳሌ በመኪና ስንሄድ መስኮት ከተከፈተ መኪናው በፈጠነ ቁጥር በመስኮት የሚገባውም ንፋስ እየፈጠነ ይመጣል፡፡ መኪናው ሲቆም ንፋሱም ይቆማል፡፡ ሰው በክርስትና ህይወቱም እንዲሁ ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ በተጋድሎ በፈጠንን ቁጥር በመንፈሳዊ ህይወታችንም ፈተናው ይጨምራል ወደ እግዚአብሔር መሄድ ስናቆም ፈተናውም ይቆማል፡፡ ገድሎ የሚቆነጥጥ የለምና ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን በቁጥጥሩ ስር ካደረገን በኋላ ይተወናልና ፈተናውም ይቀላል ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ በመንፈሳዊ ህይወታችን የሚገጥመንን መከራ ወይም ፈተናን ከመሰቀቅ ይልቅ የማይፈተነው ሰው ሊያለቅስ ይገባዋል፡፡
የተጠራንበትን ጥሪ የማናውቅ ከሆነ ያለንበትንም አናዉቅም፡፡ ሁሉን ማድረግ የሚቻለዉ እግዚአብሔር እስራኤልን በድንቅ አጠራር በተዘረጋች ክንድ ከግብፅ የጠራቸዉ
መከራቸውን በማየት ከማዳንም የዘለለ አላማ ስለነበረው ነው፡፡ ይኸውም ከዘራቸው ተስፋ የሚያደርጉት አበው ከእነርሱ የሚገኙ ናቸውና ከዘራቸዉ ሊወለድ ምድራዊ ተስፋ ኢየሩሳሌምን ሊያወርሳቸው ነበር፡፡
ነገር ግን የተጠሩበትን አጠራር ተስፋው ምን እንደሆነ ባለማወቃቸው በእግዚአብሔር ላይ ያጉረመርሙ ነበር፡፡ መና ሰለቸን! በቃን! እስኪሉ ድረስ፡፡ ሙሴን መና ሰለቸን ስጋ አማረን አሉት፡፡ እግዚአብሔር ምኞታቸው እንደገደላቸው ያሳያቸው ዘንድ ድርጭትን ከባህር አወጣላቸው ሳያኝኩትም ሞቱ፡፡ ሥጋውንም ገና በጥርሳቸዉ መካከል ሳለ ሳያኝኩትም የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሰፍት እጅግ መታ ....... የጎመጀ ሕዝብም በዚያ ተቀብረዋልና የዚያ ስፍራ ስም የምኞት መቃብር ተብሎ ተጠራ ዘኁ 11÷33- 35
ስለዚህ ባልተጠራንበት ጥሪ በመገኘት በምኞት መቃብር ሰርገን እንዳንቀር የተጠራንበትን አጠራር ተስፋው ምን እንደሆነ እናውቅ ዘንድ እግዚአብሔር አይነ ልቦናችንን ያብራ!
5. መዘጋጀት