Tuesday, November 18, 2014

ክፍል ሁለት ሰዎች ለምን ሥር ሰደዉ እንዳያድጉ ሆኑ



ክፍል ሁለት

ሰዎች ለምን  ሥር ሰደዉ እንዳያድጉ ሆኑ

            ሰላሳ አምስት ሺህ አብያተ ክርስቲያናት አርባ ሚሊየን የሚጠጋ ምዕመን ያላት ታላቅና ቀዳሚዋ እምነት ናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት፡፡ ይሁንና ከዚህ ሁሉ የበዛ ቁጥር ለክርስቶስ ስም ጥብቅና የሚቆም የቤተክርስቲያንን እርቃን ለመሸፈን ዘብ ለመቆም የሚበቁትን ግን ብዛታቸዉን እግዚአብሔር ይመርምር፡፡
            ጥቂት የሚቀኑ ኦርቶዶክሳውያን መስማት ባይፈልጉም ማጅራት ሲመቱ የሚገኙት ፓሊስ ጣቢያዉን ወህኒ ቤቱን የሚያጣብቡት ኪስ ሚያወልቁት አመንዝራነት በሚያመጣዉ የቅጣት በትር የሚመቱት በጠቅላላዉ ማለት ባይቻልም በአብዛኛዉ ኦርቶዶክሳዉያንነን ባዮች ናቸዉ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በአደባባይ የሚሳደቡ፣ የሚያቃልሉ የሃይማኖት አባቶቻቸዉን ሰድበዉ ለሰዳቢ የሚሰጡ በአብዛኛው እነዚሁ ያልተማሩ ቢማሩም ያልገባቸዉ ምዕመናን ናቸዉ፡፡ አንድ ታሪክ ይነገራል በገጠራማዉ ክልል ረቡዕ ዕለት ጠላቱን ሊገድል አልቤኑን /ጠመንጃዉን/ የሚወለዉል ገበሬ ወደ ዉጭ መዉጣቱ ነዉና
ባልተቤቱ ''ቁርስ አፍሁ ያድርጉ'' ብትለዉ ምን ማለቷ ነው እንዴት ብትደፍረኝ ነዉ ዛሬ እለቱ ረቡዕ አይደለም; አላት ይባላል   ''ከሞፈሩ እርፉ ደነደነ ማለት'' ይሄኔ ነዉ፡፡
            ታዲያ ይሄ ሁሉ መላላትና ልዝብነት ከየት መጣ; ምዕመኑ ስር ሰዶ እንዳያድግ ጋሬጣ የሆነበት ምንድን ነዉ; ለዚህ ብዙ ነገሮችን መጥቀስ ቢቻልም በዚህ ፅሁፍ ግን አቅምና ጊዜ የፈቀደዉን ያክል ችግሮች ሊሆኑ የሚችሉትን ለመጥቀስ ይሞከራል ማንም ሰዉ ከሚሰማዉ በላይ ምስክር አያስፈልግምና ምዕመናን ለምን በኃይማኖት ጠንክረን እንዳንወጣ ዉስጣችን የሚሰማንን ሁሉ በዚህ ፅሁፍ ባይካተተም በኃይማኖት ላለማደግ ምክንያት ሊሆኑ ከሚችሉት መካከል ጥቂቶቹ እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡-
1. ችግሮች በምዕመናን በኩል
1.1 አለመማር
            ''እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገዉ ይጠሩታል; ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ; ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ;''ሮሜ10÷14
በዚህ የመጸሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚጠቃለሉ በበርካታ የህይወት ገፅታ ዉስጥ ያሉ ሲሆኑ በመጀመሪያ የሚጠቀሱት ከከተሞች በራቀ ክልል ዉስጥ የሚኖሩ ምዕመናን ናቸዉ፡፡ በዋና ከተሞች አካባቢ ከየቤተ ክርስቲያኑ የሚወጡ ምዕመናን ብዛት የተመለከተና መንፈሱ በሀሴት የተጥለቀለቀችበት ሰዉ ወደ ገጠሩ ክልል ቢወጣና አምስት ቀዳስያን ሊያውም ከተሟላ! ያለ ምንም አስቀዳሽ ሲቀድሱ ያየ በእርግጠኝነት መንፈሱ በሀዘን ይጎዳል ያለቅሳልም  እጅግ በጣም ብዙዎቹ ገና ይህ የምስራች ወንጌል አልተሰበከላቸዉም፤ አልሰሙትም፤ አያዉቁትምም ለዚህም ይመስላል ባዕድ አምልኮቱ የበዛው

            መምህራኑ የተጠናከረ ትምህርት የሚሰጡትም የሚያዘጋጁትም በከተማ ላሉት አማንያን ብቻ ነዉ፡ በዚህም ቤተክርስቲያኗ  ምዕመኗን በተደራጀ መልኩ ለማስተማር የአወቃቀር ንድፍና የሰባኪ እጥረት ይታይባታል፡፡ ሰባኪያኑ ቢኖሩም ወደዚህ የገጠሪቷ ቤተ ክርስቲያን የመሄድ ችግር ይታይባቸዋል፡፡ ስለዚህም ምዕመናኑ አይማሩም ስላልተማሩም አያምኑም፡፡ በዉርስ የደረሳቸዉ የአባቶቻቸዉን እምነት፣ ባህልና ጣኦት አምልኮ ቀላቅለዉ ይዘዉ ይገኛሉ፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥቶ ላለመማርም መሰናክል ያበዛባቸዋል ስለዚህ አይማሩም
1.2. የተማሩትን አለመተግበር
            ''እንግዲህ እናንተ የዘሪዉን ምሳሌ ስሙ የመንግስትን ቃል ሰምቶ በማያስተዉል ሁሉ ክፉ ይመጣል በልቡ የተዘራዉንም ይነጥቃል በመንገድ ላይ የተዘራዉ ዘር ይህ ነዉ፡፡'' ማቴ 13÷18       
ክርስቶስ ኢየሱስ በዚህ ዓለም በመዋዕለ ሥጋዌ በተመላለሰበትና በሚያስተምርበት ጊዜ በነቢዩ በዳዊት ''አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ ከቀደሞ ጀምሮ ያለዉንም ተምሳሌት እናገራለሁ'' መዝ 77÷2 ንዳለ ለሚሰበሰበዉ ህዝብ ሁሉ በምሳሌ ይናገር ነበርና ይህም ምሳሌ ደቀመዛሙርቱን ይከብዳቸዉ ስለነበር ክርስቶስን ለምን በምሳሌ ትናገራለህ ባሉት ጊዜ ''እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተዉሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ፡፡ መስማትን ትሰማላችሁና አታስተዉሉም ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም'' ማቴ 13÷14
            እነዚህ እያዩ የማያዩ እየሰሙ የማያስተዉሉ የተባሉት ከላይ በዘሪዉ ምሳሌ እንደተነገረ የሚነገራቸዉን የህይወት ቃል በመንፈሳዊ ህይወት ለመግለጥ ጠንክረዉ የሚያደምጡ አይደሉም የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማሉ ያስቀድሳሉ
ማህሌት፣ ሰዓታት ይቆማሉ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል በዉስጣቸዉ ተዘርቶ አድጎ ፍሬ እንዲያፈራ አይፈልጉምና የሰሙትን ይተዉታል፡፡
            የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ ሰዉ ቤተ ክርስቲያን ስለሄደ ተከትለዉ የሚሄዱ፣ የሚናፍቁትንና የሚወዱትን ሰዉ ለማየት የሚሄዱ፣ የመምህሩ የቃል ድርደራና ቃላት ጨዋታ ስለሚማርካቸዉ የሚመጡ፣ እገሌ እኮ ጎበዝ መምህር ነዉ፤ ጎበዝ ቀዳሽ ነዉ፤ ስለተባሉ ሰዉ ያደነቀዉን ሰምተዉና አይተዉ ለማድነቅ የሚመጡ፣ ለሚያፈቅሯት ሴት ወይም ለሚያገቧት ሚስት የቤተ ክርስቲያን ሰዉ መሆን ወይም ወንጌል መስማት እንደ ቅድመ ሁኔታ ስለሚቀመጥባቸዉ በእጃቸዉ እስኪያስገቡ መስፈርት ለማሟላት የሚመጡ ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡

            እነዚህም ከመጡበት አላማ ዉጪ ጆሮአቸዉ ሌላ ለመስማት ስለማይዘጋጅ አያስተዉሉም፡፡ በዘሪዉ ምሳሌ ላይ ''ሌላዉ በእሾህ መካከል ወደቀ እሾሁም ወጣና አነቀዉ''     ማቴ 13÷7 ይህንን የመጽሐፍ ክፍል ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ባብራራላቸዉ ጊዜ ''በእሾህ መካከል የተዘራዉም /ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነዉ/ ይህ ቃሉን የሚሰማ ነዉ፤ የዚህም ዓለም ሃሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉ እንዳያድግ
ያንቀዋል፤ የማያፈራም ይሆናል'' ማቴ13÷22
            እነዚህ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማሉ በዉስጣቸዉም ያድጋል ነገር ግን አድጎ የሃይማኖት ፍሬ እንዳያፈሩ ዉስጣቸዉ ያለ የከፋ ማንነታቸዉ ያንቀዋል፡፡ የምንዝር ስሜታቸዉ ንፅህና በዉስጣቸዉ እንዳያፈራ ያንቀዋል፡፡ ላለመለገስ ስስታቸዉ፤ ላለማመስገን ርግማናቸዉ፤ ላለመዘመር የመዝፈን ፍላገጎታቸዉ የተቸገረዉን ላለመርዳት ምቀኝነታቸዉ እያነቀ ያስቀራቸዋል፡፡

            ለዚህም ነዉ ብዙዎቻችን ዕድሜ ልካችንን በእግዚአብሔር ቤት እየኖርን ግማሹን የህይወታችንን ዘመን በሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎት አሳልፈን ነገር ግን በኑሯችን ሁሉ ቅዱሳን መሆን የሚያቅተን፡፡ ለክፋት ተምሳሌት፣ ለምንዝርና አብነት ሆነን እነሱ ባሉበት የጨለመ አይነጋም፤ የነጋ አይጨልምም የሚባልልን ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል በማመንና በማድረግ ስር ሰደን ላለማደግ ያለማስተዋል ዉጤቶች ነን፡፡
ልበ አምላክ ዳዊት በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች በመንፈሳዊ ሚዛን መዝኖ ሰፍሮ እንዲህ አላቸዉ ''የሚያስተዉል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ ሰዉ እንዳለ ያይ ዘንድ
እግዚአብሔር ከሰማይ የሰዉ ልጆችን ተመለከተ ሁሉም አመፁ  በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሰራ የለም አንድስ እንኳ የለም'' መዝ 13÷2 እና ሮሜ 3÷11-12
            እግዚአብሔር በየዘመናቱ እርሱን የሚፈልግና የሚያስተዉል ሰዉ እንዳለ ያይ ዘንድ ወደ ምድር ይመለከታል ማንን ያገኝ ይሆን; ማስተዋሉን ያድለን!

1.3  ስሜታዊ መሆን
            ስሜታዊ መሆን በክርሰትና ህይወት ላይ ትልቅ አደጋን ያስከትላል፡፡ ስሜታዊነት ከዚህ በፊት በጥቂቱ ለማየት እንደሞከርነዉ በተገቢዉና በአስፈላጊዉ ቦታ ካልተጠቀምንበት በክርስትና ህይወታችን ላይ ጥላ ያጠላብናል፤ ስሜታችን ሲቀዘቅዝ ነገር ሁሉ ይቀዘቅዛል፡፡ እግዚአብሔር የረሳን የተወን ይመስለናል፤ ስሜታችን ሲግል የቅድስና ኮርቻ የተፈናጠጥን ያክል ይሰማናል፡፡ ስሜታዊ ስንሆን ደስ ሲለን እናመሰግናለን፤ ሲከፋን እንሳደባለን በአንድ ወቅት የምናመልከውን ሀያልና ገናና አምላክ በቤተሰባችን ወይም በራሳችን ላይ አደጋ ሲደርስ የምንቀየም የምናኮርፍ የማንፀልይ የማናመሰግን እንሆናለን ይህም የስሜታዊነት ችግር ነዉ፡፡ በጣም ስሜታዊ ስንሆን ስሜታዊነት ከሚወልዳቸዉ ነገሮች አንዱና ብዙ ሰዎች ላይ
የሚታየዉ በአንድና ጥቂት ነገር ላይ ማተኮርና ማጥበቅ ነው፡፡
            ብዙዎች ወደ እግዚአብሔር ቤት ሲመጡ ለወንጌሉ ሲታደሙ መስማትና መማር የሚፈልጉት ስለ አንድ ነገር ብቻ ይሆናል፡፡ መናፍቃንን መርታት ስለሚችሉበት ነገር፡፡ በእርግጥ አንዳንድ መምህራንም ኮርስ የሚሰጡትም ጭምር የኦርቶዶክስ እምነት መሠረቱ ነገረ ቅዱሳን እንደሆነ አበክረዉ ሲናገሩ ይሰማሉ፤ ከዚህ የተነሳ ተማሪዎችም ስለ ነገረ ቅዱሳን ተምረዉ መናፍቃንን ማሳፈር ከመፈለግ ዉጭ ለህይወታቸዉ መሰረት የሚሆን ነገር አይጨብጡም፡፡ ይህ ማለት ግን ስለ ነገረ ቅዱሳንና ስለ እመቤታችን አማላጅነት፤ መማርና ማወቅ አያስፈልግም ማለት አይደለም፡፡ የእምነቷ መሠረት ግን ቅዱሳንን ቅዱስ ያሰኛቸዉ የቀደሳቸዉ እናቱ ማርያምን በእናትነት የመረጣት ማኅተመ ድንግልናዋን ሳያጠፋ ድንግል ተብላ ተመስግናና ተከብራ እንድትኖር የቀደሳት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነዉ፡፡

            አንዳንድ ጊዜ ምዕመናን ብቻ አይደለም መምህራንም ስሜታዊ   እንሆናለን፡፡ መምህራንም እንዲሁ ከግንዱ ይልቅ በቅርንጫፉ ላይ ስለምናተኩር በጥቃቅን ነገር ምዕመናንን መዝለፍ ይቀናናል ከመጠመቅ ውጭ ምንም እዉቀት የሌላቸውንና በአመት አንድ ጊዜ አክሱም ወይም ግሸን የሚገኝን ምዕመን በተገኘዉ አጋጣሚ ስለክርስቶስ ልዩ የመስቀል ፍቅር ከመስበክ ይልቅ ፀጉርሽን ቀለም የምትቀቢ፤ ሊፒስቲክ የምትለቀለቂ፤ ጥፍርሽን የምታሳድጊ፤ በሱሪ የምትወጠሪ በማለት ማስበርገግ ይቀናናል የብዙዎቻችን ህይወት በምንዝርና ተበክሎ ለሴት ሱሪ ስለመልበስ እንጨነቃለን ከጋብቻ ውጪ የሚደረግን ዝሙት ዘንግተን በሰርግ (በተክሊል) የሚያገባ ሰው በቬሎ ስለመቅረብና አለመቅረብ እንጠበባለን በአጠቃላይ ግመሉን እየዋጥን ትንኙን ለማጥራት ጊዜ እናባክናለን፡፡ መምከሩ ተገቢ ቢሆንም ድሮም በትግል የመጣና በአጋጣሚ የተገኘ ምዕመን ይሄን ቃል ዳግመኛ ላለመስማት ጠፍቶ ይቀራል፡፡ ይህ ማለት ግን እነዚህን ነገሮች ማበረታታት አይደለም፤ የክርስቶስን የፍቅር ልክ መንገር አይቀድምም ወይ; ለማለት እንጂ ሱሪ መልበስስ የሚያመጣው ችግር ምንድን ነው?
            በዚህ ነጥብ ላይ ብዙ መምህራን የተለያየ ሀሳብ አለን፤ የምንቃወመውም የምናወግዘውም ብዙዎች ነን፡፡ ነገር ግን ሱሪ የሚለብሱ እህቶቻችን ቁጥር በጣም እያሻቀበና ሲልም ወደ እናቶቻችን ልማዱ ሲጋባ እንጂ ሲቀንስ አይታይም፡፡ ዛሬ በየቤተ ክርስቲያኑ፤ በየገዳማቱ ከሚገኙ ሴቶች ምዕመናን በእርግጠኝነት ከግማሽ በላዩ ሱሪ ለባሾች
እየሆኑ ነዉ፡፡
ይህም ሀሳብ በትምህርትነት ሲቀርብ ''ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ፡፡ ይህንንም የሚያደርግ በአምላኩ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና''  ዘዳ 22÷5 የሚለዉን የሙሴ ህግና ሐዋርያዉ ጳዉሎስ  ለልጁ ለጢሞቴዋስ ''እንዲሁም ሴቶች ደግሞ በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን የሚሉ ሴቶች እንደሚገባ መልካም ለማድረግ እንጂ በሹሩባና በወርቅ ወይም በእንቁ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ'' 1ጢሞ29 በሚለው ትምህርት ላይ እንንተራሳለን ይህም የሴቶች ሱሪ መልበስ ለዝሙት የሚያጋለጥ መንፈስ ትውዝፍት ወይም የምንዝር ጌጥ እንደሆነ በማመን ነዉ፡፡ ከመቼ ጀምሮ ኣጋንንት ለእግዚአብሔርና ለቤቱ መቅናት እንደጀመሩና ጥብቅና እንደቆሙ ባይታወቅም አንድ አንድ የአጋንንት መንፈስ አለብን የሚሉ ሰዎች ሱሪ የለበሱ እናቶችን በየገዳማቱ ሲሰድቡ ሲያዋርዱ ሱሪ ሲቀዱና ሲደበድቡ ይታያሉ፤ ግማሹ ይደግፈዋል ለግማሹ አይዋጥለትም ''ተኩላ ቢለምድ በግ አይሆንምና''
            የምንዝር ጌጥ ስሙ እንደሚያመለክተው ለግልሙትና ሥራ የሚውልና ለዝሙት ግብር ሰዎችን የሚያነሳሳ
አልባሳትንና ጌጣጌጦችን አብዝቶ መጠቀምን የሚያመለክት ነው፡፡ የውስጥ ሰውነትን የሚያሳዩ ሆዳቸውን እምብርታቸውን ጭናቸውን የሚያሳይ አለባበስ ለመንገደኛ ሁሉ የተገለጠ ነውና ይህንን ማብራራት አያስፈልግም፡፡ ታዲያ በእውነት ሁሉም ሴቶች ሱሪ የሚለብሱት በውስጣቸዉ ያለ የዝሙት መንፈስ ሲጨምር የተደበቀው መጎምዠታቸው እድገቱን ሲጨርስ በላይኛው ገፅታ የሚታይ ምልክት ነው;
            አንድ ጊዜ በአንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ሱሪ መልበስ ለዝሙት ያነሳሳል ወይ; በሚል ሰፊ ፕሮግራም እንደነበረ  ሁላችንም በየቤታችንም አስተያየት የሰጠንበት ነውና አልመለስበትም፡፡

            ግን በሰዶምና ገሞራ ጊዜ ህዝቡ ዝሙት በላያቸዉ ነግሶ እግዚአብሔር እስኪቆጣና ከተማዋን እስኪያጠፋት በደረሰ ጊዜ  (ዘፍ 25÷1)
            የተስፋይቱ ምድር ወራሾች በዝሙት ምክንያት ከአህዛብ ሴት ጋር በወደቁና እግዚአብሔር በቀሰፋቸዉ ጊዜ (ዘፍ25÷1)
            ታላቁ ናዝራዊ ሶምሶን ከደሊላ ጋር ወድቆ ፀጋዉ እስኪገፈፍ ድረስ ቢደርስም (መሳ16÷1)
የታላቁ ንጉስ የዳዊት ልጅ ሰለሞን ከአህዛብ ሴቶች ጋር በፍቅር የወደቀው በቁጥር የሚበዙ እቁባቶችና ሚስት ያበጀው (1ነገ 11÷1- 13) የሰዉ ልጅ ለዝሙት ባለዉ ታላቅ የመጎምዠት ፍላጎት እንጂ ማበረታታትና ማደፋፈር እንዳይሆን እንጂ ሴቶቻቸዉ ሱሪ ለብሰዉ ፍላጎታቸውን ገዝተው አሳስተዋቸው ነው ማለት ይከብዳል፡፡
            ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ግን ለማበረታታት ወይም ለመደገፍ ሳይሆን መወገዙ ኃጢአት መሆኑ አለአግባብ እንዳይሆንና ብዙዎች እንዳይርቁ ነዉ፡፡ ባናበረታታ ነገር ግን ባናወግዝ ስንት የቤተክርስቲያን ልጆችን ወደ ሱሪ መልበስ እንገፋለን ወይስ ስንት ሱሪ ለባሾችን ወደ ቤተክርስቲያን እንስባለን;;
            ለፀሎት አለመመቸትን እንደምክንያት ብንጠቅስ የሚያስኬድ ይመስላል የአካልን ቅርፅ ያሳያልና የሚፀልዩ ሰዎችን  ሀሳብ  ሊበትን ይችላል፡፡ የካህናትም በቅዳሴ ጊዜ ወጥ የሆነ ልብሰ ተክህኖ መልበሳቸዉ እንዲህ ያለ የመንፈስ ዝለትን ለመጠበቅ ነዉ፡፡
ይሁንና በቤተክርስቲያን የቅዳሴ ጊዜ ወይንም የፀሎት ሰዓት ሀሳብን የሚሰርቀው ሱሪ መልበስ ብቻ አይደለም የተጣበቀ ቀሚስና የተቆረጠ ነጠላ ጭምር ሊስተካከሉ
ይገባቸዋል፡፡
            እንግዲህ ሱሪ የለበሱትም ይሁኑ ነጠላቸዉ የተቆረጠውን እህቶቻችንን ከማሸማቀቅና ከማውገዝ ይልቅ ቢማሩና በፍቅር ብንስባቸዉ የሚያልፉበት የቤተክርስቲያን አገልግሎት እንዴት መልበስ እንዳለባቸው ያሳያቸዋልና አቅርቦ ማስተማር ቢቀድም መልካም ነው፡፡ ቬሎ ለብሶ መዳርም በዚህ ርዕስ ላይ ቀድሞ ከተነሳው ጉዳይ /ሀሳብ/ የተለየ ነጥብ የለም አይኖርም፡፡ የዚህ ጽሁፍ አላማ ለምን ተከለከለ ለምን ቀረ ለማለት ሳይሆን ከዚህ ጀርባ ያለውን ሀሳብ መፈተሸ ነው፡፡ ለመሆኑ ቤተክርስቲያኗስ ከልክላለች; ሁሉም የሚያስተውለው እውነት አለ፤ ቬሎ ለመልበስ ካለ ፍቅር የተነሳ የአንድ ሰዉ ሠርግ ሁለቴ ስለመሆኑ! ይህ ችግር ከተራው አማኝ ጀምሮ ተምረናል እስከሚሉት ምሁራን እና አገልጋዮች ድረስ እውነት እየሆነ ይመስላል፡፡ ተክሊል ሀሙስ ሠርግ እሁድ ከዚያም የራቀ ሊኖር ይችላል፡፡
            ''እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው'' ማቴ 19 ይህ ህያው የሆነ የማይሻር የማይለወጥ የማይሻሻል የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ነገር ግን ሀሙስ በስርዓተ ተክሊል አንድ የሆኑ ባልና ሚስት ቅዳሜ ወይም እሁድ ድጋሚ እስኪያገናኛቸው መለያየታቸው ገሀድ የወጣ እውነት እየሆነ
ነው፡፡
            ለቬሎ የሚሰጡት ትርጉሞች ወይም ክልከላዎች የበዙ ቢሆኑም የምዕራባዉያኑ ባህል ነው፤ ስጋዉና ደሙን ያረክሳልና ........ የመሳሰሉት ሲነገሩ ወይም በትምህርት መልክ ሲሰጡ ይሰማሉ፡፡
            አንድ ሰሞን ሚስቶቻቸው ቬሎ እንዳይለብሱ የሚከለክሉ ባሎች እነሱ በሱፍ ተውበዉ ይቀርቡ ነበር፡፡ የኋላ የኋላ ግን ለሁለቱም ስምምነት ሲባል ይመስላል ሀሙስ በነጠላና ቀሚስ እሁድ በቬሎና በሱፍ ሆኗል፡፡

            እስኪ ይህንን ሀሳብ በቀደመው ከውሳኔ ባለመድረስ ሀሳብ በጥቂቱ እንፈትሸዉ፡፡ ቬሎ በእዉነት የእኛ ባህል ስላልሆነ ነዉ ቤተክርስቲያን የከለከለችዉ; በእርግጥስ ከልክላለች; ወይም ምዕመናን እዛዉ ተከላከሉ; በእርግጥ ሰባክያነ ወንጌልም በዚህ ላይ የሰላ ትችት ሲሰነዝሩ ይሰማሉ፤የዉጪ ባህል ነዉ ብለን የምንል ከሆነ ግን ትንሽ ያስቸግራል፡፡ በቤተ ክርስቲያን የውስጥ አገልግሎት ጭምር የምንገለገልባቸው ብዙ የውጪ ባህል መገልገያዎች አሉ፡፡
            ወደ ሥጋወ ደሙ በመቅረቡ የክርስቶስን ስጋና ደም ያረክሰዋል የሚሉም ካሉ ማለታቸዉ ሊያሳፍራቸዉ ይገባል፡፡
ቬሎዉ የጌታን ስጋና ደም ያረክሰዋል ወይስ የጌታ ሥጋና ደም ቬሎዉን ይቀድሰዋል ወይስ የአንድ ሰዉ ጋብቻ ሁለቴ መፈፀሙ ቬሎ ለብሶ ከመቁረብ የተሻለ ነዉ; አንባቢ ይፍረድ፡፡
            ሌላ ሻገር ያለ ምልከታስ ቢኖረን፡፡ አሁን ለሠርግ ልብስ የምንጠቀምበት የሀገር ባሕል ልብስ የማን ልብስ ነዉ; የየትኛዉ ሀገር፤ መቼም ከዳር እስከ ዳር ላሉ ሰዎች የባህል ልብሳቸዉ ነዉ ማለት ይከብዳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቤተክርስቲያንን ሳናዉቀዉ ብሔርተኛ እንዳናደርጋት ያስፈራል፡ ዛሬ ብቻም ሳይሆን ድሮም ነጠላ ያልለበሰ ሰዉ ለማስቀደስ አይችልም፡፡ ዛሬ ደግሞ ለያዉም ነጠላዋን የነጠላ ቁምጣ አድርገዋታል፡፡ ይሁንና ይህች ቤተክርስቲያን ዓለም አቀፋዊት ናትና በዉጪ ያለዉን አማኝ ትተን ወደ ሀገራችን ደቡብ ክልል ቤተ ክርስቲያን እምነቷን ብታስፋፋ ነጠላ ይዛ ልትዞር ነዉ; ወይስ አፋር ቢያምን በግልድም አትቀርብም ሊባል; ስለዚህ ማስተዋል እንጨምርበትና ሠርግን ወደ አንድ ለማምጣት ሁላችንም እሰኪ የበኩላችንን እንበል፡፡

            ይሁንና ይሄ ማለት ነጠላ ለብሶ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አያስፈልግም ማለት ሳይሆን ቤተክርስቲያን ከሚለበሰዉ ነጠላ ሳይሆን ቅድሚያ ከነጠላዉ ስር ስላለዉ አካሉ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነዉን ምዕመን ቅድሚያ ይሰጠዉ ለማለት ነዉ፡፡
ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ አይደል ቃሉ፡፡
መቼም ነጠላ እቤቱ እያለ ምናለበት ብሎ ራቁቱን የሚመጣ ሰዉ በተወዉ ነጠላ ሳይሆን በልቡ ባለ ክፋት እግዚአብሔርን እንዳላከበረ ወይም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ህዝብ እንደማይሆን መናገር ላይከብድ ይችላል፡፡ ታዲያ በዚህ ሰዉ ላይ የሚወሰደዉ የተግሳፅ  እርምጃ የእግዚአብሔር ፍቅር በዉስጣቸዉ እያለና እየተቀጣጠለ የሚለብሱት ነጠላ ስለሌላቸዉ ያለ ነጠላ የሚመጡ ሰዎችን ማስደንገጥ የለበትም፡፡

            የማርያም እናት ሃና የምትለብሰዉ ልብስ ስለሌላት ከቤተ መቅደስ ልትቀር እንደነበር ተአምረ ማርያም ይነግረናል፡፡ (ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ገጽ 48)