Saturday, January 24, 2015

ወንጭፍ ሩቅ የሚሄደው ወደ ኋላ በሚሳበው መጠን ነው፡፡

ረቡዕ ማታ በብሔራዊ ቴያትር የቴዎድሮስ ትዝታ የሚል ቴያትር እየታየ ነው፡፡ ያዘጋጀው ጌትነት እንየዉ ይመስለኛል ሱራፌል/የሰው ለሰው ኩራ ሽመልስ አበራ ጆሮና ሌሎችም ይሳተፉበታል፡፡
እንዳየው የጋበዙኝ ሰዎች ከነገሩኝ በላይ ታሪክን የኋሊት የሚያሳይ ቴያትር ሆኖ አገኘሁት በጣም ያምራል፡፡
የዛሬ ሀሳቤ ስለ ታሪኩ ይዘት፣ አወቃቀር፣ የታሪክ ፍሰቱ ለመናገር አይደለም እንደ አንድ ተመልካች በጣም ቆንጆ ሆኖ ቀርቧል ማለት ይበቃኛል፡፡ አዲስ ተቀምጦ ጎንደርን ጋፋትን መቅደላን እንዲያዩ/በህሊናዎ/ የሚያደርግ ሀይል አለው፡፡
ሌላ ያየሁት ነገር ግን ቲያትሩ ከሚጀመርበት ሰዓት በፊት ምናልባትም ከሁለት ሰዓት በፊት ቀድሞ አዳራሹን የሞላው ተመልካች ምን ያክል በተመስጦ ይከታተል እንደነበር በፍቅር አድናቆቱን ይቸር እንደነበር በታሪክ የኋልዮሽ ምልከታ ስሜቱ ሲነካ በጭብጨባ አዳራሹን ያቀልጥ እንደነበር አይቻለሁ፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ስለ ቴያትሩ ይዘት ለመናገር ሙያም መስመርም ይጠይቃልና ቆንጆ ነው እዩት ከማለት ውጭ ምንም ባልል ከብዙ ነገር አመልጣለሁ፡፡
ምንም ካላልክ ለምን . . . ለሚለኝ ግን እኔ ያየሁት ሰው ምን ያክል ታሪክን ማወቅ መስማትና ማየት እንደሚያስደስተው ነው፡፡ አሁን የምናየው ትውልድ ለታሪኩ ለሀገሩ ለሃይማኖቱ ቁብ የሌለው ነው ተብሎ የሚታማውን ያክል መሰረት ከሌለ ቋሚ ግድግዳ ቤት የለም ብሎ የሚያስብም ብዙ እንደሆነ አይቻለሁ፡፡
ታሪክ አሁን ላለንበት ጊዜ መሰረት ይመስለኛል ታሪክ የሌለው ህዝብ ስለማንነቱ የት መጣነቱ መናገር የሚከብደው የማይችል የሚያፍርም ይመስለኛል፡፡
ረዥም ታሪክ የሌላቸው ሀገራት ራሳቸውን ባለታሪክ እንደሆኑ ለማሳመን በብዙ ሲደክሙ ስናይ እኛ በተቃራኒው ሀገሪቱ የታሪክ ሀብታም ሆና ለሀገሩ ለታሪኩ ለቅርሱ ግድ የሌለው ትውልድ እየገነባን መሆኑ ሲታሰብ ምን እየሰራን ነው ያሰኛል፡፡
ከሀያ ዓመት በፊት ይመስለኛል ፔንፓል/የብእር ጓደኛ/ እየተባለ ብዙ ሰው ከውጭ ዜጎች ጋራ ደብዳቤ ይጻጻፍ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ እጅግ በጣም የገረመኝ ነገር ነበር አንዱ የማውቀው ሰው ጀርመን ሀገር ካለች የብዕር ወዳጁ ጋር ሲጻጸፍ ስለታሪክ ተነሳና ኢትዮጵያ ባለብዙ ታሪክ ሀገር ነች ለምሳሌ ብሎ ጀርመን የምትባል ሀገር የሌለችበት ነገር ግን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን አንድ ካርታ ላከላት ከዚያን ጊዜ በኋላ አልተጻጻፉም ዘጋችው ነው የሚባለው ጥርቅም አድርጋ፡፡
ዛሬ እሷን ሆኜ ሳስበው ታሪካቸው ከኛ ሀገር ታሪክ እኩል ባለመሆኑ ተናዳ ተባሳጭታ ወይም አፍራ መሆን አለበት፡፡
በእንድ ወቅት እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን በገባበት የቃሌ ኪዳን ታቦት እጅግ ታላላቅ ተአምራትን ያደረገና ይህ በአንድ ወቅት የዓለምን ታሪክ ይመራ የነበረ የቃሌ ኪዳን ታቦት የት እንደሚገኝ የማይታወቅና ያልተረጋገጠ ነው ብለው የሚያምኑ ሀያላን ሀገራት የዚህ ታላቅ ታሪክ እና ቅርስ ባለቤት ለመሆን ዓለምን ሲንጧት እያየን ብዙ ታዝበናል፡፡ ምናልባትም በሀገራችን የጽላት ሽያጭ ለታሪክና ቅርስ ግድ የሌላቸው እና ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ ሰዎችን ተገን በማድረግ በሚደንቅ እና መጠኑ በበዛ ገንዘብ እየተቸበቸበ ያለው ምናልባትም የሙሴ ጽላትን ብናገኝ ብለው እንደሆነ ይታመናል፡፡
ይኽ ሁሉ ሰው ለታሪክ ለሀገርና ለቅርስ ያለውን ስሜት የሚናገር ይመስለኛል፡፡ ሀገርን ታሪክን እና ቅርስን ለመውደድና ለማክበር ምክንያት የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡
አሁን አሁን ግን የምናያቸው ነገሮች ከዚህ እየወጡ ይመስለኛል፡፡ ትቅልዱ ለታሪኩና ለቅርሱ ግድ እንዳይኖረው የሚሰብኩ ብዙዎች ናቸው፡፡ መንግስትም እንደመንግስት ሰው ለሀገሩ ለቅርሱና ለታሪኩ ግድ እንዲኖረው የሚጠበቅበትን ሁሉ እየሰራ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ በትምህርት ቤት በዩንቨርሲቲዎች ጭምር የታሪክ ትምህርት ከየ ካሪኩለሙ እየሳሳና እየወጣ ይመስለኛል በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች አማርኛ መናገር የወንጀል ያክል እየታየ መምጣቱ የአደባባይ ምስጢር እየሆነ ነው፡፡ ለሀገር ለታክና ለቅርስ ለሃይማኖትም ግድ የሌለውን ትውልድ ሀገር እያፈራች እና እያሳደገች ይመስለኛል፡፡
ወገኔ ስለ ወንጭፍ ወይም ቀስት አስበህ ታውቃለህ ወንጭፍም ሆነ ቀስት ሩቅ የሚሄደው ወደ ኋላ በሚሳበው መጠን ነው፡፡ እድገት ብልጽግናም ዘመናዊነትም እንደዚሁ ይመስሉኛል፡፡ ታሪክን ወደ ኋላ ባየንው በቃኘነው ቁጥር ይመስለኛል ወደ ፊት በሚገባው ፍጥነት መወንጨፍ የምንችለው፡፡ ‹‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ›› ይባል የለ፡፡
ሕብረተሰቡ በቀና ጎዳና እንዲራመድ ከሚያግዙና ከሚያስተምሩ መንገዶች፣ መድረኮች ወይም ተቋማት መካከል የኪነጥበቡ መድረክ አንዱ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ አሁን በቴዎድሮስ ትዝታ ቴያትር እንዳየሁት አዘጋጁን አደንቃለሁ የጋዙኝን አመሰግናለሁ፡፡
መስመሬ ስላልሆነ በጥልቀት መንካት ባልፈልግም ፊልሞቻችንም ይህንን አርአያ ቢከተሉ እንዴት መልካም ነበር ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ብዙ በታሪክ ላይ የሚያጠነጥኑ ፊልሞችን ሳይ እኛ ታሪክ የለንም ወይስ ታሪክን በፊልም መልክ መስራት ለኛ አልተፈቀደም ብዬ እንዳስብ ያደረገኘ ጊዜ አንዴና ሁለት ግዜ ብቻ አይደለም፡፡ አሁን በእኛ ሀገር በቀን አንድ ፊልም መውጣት ጀምሯል የሚል ነገር እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡ ግን ታሪክን የሚያስተምር የሚያሳይ ፊልም ግን እንዳለ መስማቴን እጠራጠራለሁ፡፡ ብዙዎቹ እሁድ በተቀረጹበት ልብስ ሰኞ ካፌ የሚታዩ ቤት ለምነው የሚቀረጹ አሁን ያለንበትን አኗኗር ብቻ የሚያሳዩ መሆናቸውን ሳይ ወደ ኋላ ተመልሰው ፊልም ለመስራት በጊዜው የነበረውን ገጽታ ለመሳል የሚቻልባቸውን ነገሮች ለማዘጋጀት እና ለፊልሙ የሚሆን መንደር ለመገንባት ወጪ ማውጣት የሚፈሩ ወይም የማይፈልጉ ይመስለኛል፡፡
ተመልካች አናገኝም ብለው እንዳይሆን ግን የቴዎድሮስ ትዝታን ተጋፍቶ ከሁለት ሰዓት በፊት ቀድሞ የሚገኝ ተመልካች ሀሳባቸውን ያፈርሰዋል፡፡
ለሀገሩ ለታኩና ለቅርሱ የሚጨነው ትውልድ ፈጣሪ አያሳጣን
ይብቃኝ በድጋሜ በማየቴ ተደስቻለሁ አዘጋጁን አከብራሉ የጋበዙኝን አመሰግናለሁ ያላያችሁትን ጋዣለሁ ሠላም

Friday, January 9, 2015

የመምህራን የማስተማር ብቃት




2.  ችግሮች በአገልጋዮች በኩል
2.1 የመምህራን የማስተማር ብቃት ማነስ
      ከእድሜያችን ባልበለጠ  ጊዜ የተጀመረውና እየተስፋፋ ያለው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ እጅግ በጣም ጥሩ ውጤት እያስገኘ ያለ ለመሆኑ በጣም ብዙ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ማታ ከሰርክ ጉባኤ የሚወጣው በእለተ ሰንበትና በየክብረበዓላቱ የሚገኘውና የሚያስቀድሰው ሰው ብዛት እንዲሁም አንድ ለአንድ በተወሰነ በተቀደሰ ስርዓተ ተክሊል ጋብቻ ጋብቻቸውን
የሚፈፅሙ ብዙዎች እንደሆኑ እውነት ነው ይህም በቅርብ አመታት የተጀመረው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ፍሬ ነው፡፡ ገና ብዙ የሚቀረው ቢሆንም፡፡ ይሁንና የዚያኑ ያህል ችግር እየታየበት ያለ እንቅስቃሴ ነው በዚህ ላይ ለማየት የተፈለገው ፍፁም ለውጥ ሊመጣ ካልቻለባቸው መንገዶች አንዱ የሰባክያን የማስተማር ብቃት ማነስ ነው፡፡
      የማስተማር ብቃት ሲባል በብዙ መንገድ ሊተረጎም ይችላል በቀጥታ ግን ማስተማር አለመቻል ስለምናስተምረው ትምህርት እኛም በጥልቀት አለማወቅና ለምናስተምረውም ሕዝብ ክብር ስለሌለን የማናነበውንም ያጠቃልላል፡፡

      አፋችን በእግዚአብሔር ቃል ስላልተሟሸ ስላላነበብንም መድረክ ላይ የመውጣት እድሉ ስላጋጠመን ብቻ የተሰጠንን ሰዓት ለመሙላት የባጥ የቆጡን የምንቀባጥር አልፎ ተርፎም የምንሳደብ ብዙዎች ነን፡፡ አንዳንዴ ሕዝቡም የክርስቶስ የማዳኑ ኃይል ከሚሰበክለት ይልቅ ስድብ መስማት የሚናፍቀው ሆኖ ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው መነሻ እና መድረሻ የሌለውንና በስድብ የታጀበውን በሀታውያን ነን ባዮችን ስብከት የሚሰማው ‹‹አንዳንድ ሰባኪና ሹፌር የሚለምዱት በስድብ ነው'' ይባላል፡፡ ሹፌር የሚይዘውን መኪና በአግባቡ እስኪቆጣጠረው ድረስ ሰውም ገባበት እንስሳ ስድብ ይቀናዋል ሰባኪም እንዲሁ
የሚሰጠንን ሰዓት ለመሸፈን ጭንቅ የተሰጠንንም ሰዓት ሳንጨርስ መውረድም ሀፍረት ስለሚሆንብን ሰዓቱን በስድብ ስንሸፍን እንስተዋላለን፡፡ ክፋቱ በዛው ይለምድብንና እውቀቱን በማንበብ ስለማናዳብረው ክርስቶስን መስበክ ትተን አባቶችን ስንሰድብ ውለን እንወርዳለን፡፡
      እንዲህ ያለነው መምህራን በችግርና በሃዘን ግራ በመጋባት ተይዘው ለነፍሳቸው እረፍትን ሽተው ወደቤቱ የመጡትን ምዕመናን ሰድበን አሰድበን የምንልክ ነን፡፡ ምንም እንኳን በቤተ ክርስትያን ውስጥ ሁል ጊዜ ተስፋ ብቻ ነው የሚሰበከው ባይባልም፡፡ እንዲህ ያለ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ እውር እውርን ቢመራው ሁለቱም ገደል ይወድቃሉ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡

2.2 እንደሚናገሩት አለመሆን
ሌላው ለምእመናን በእውቀት መጎልበት ችግር የመምህራን ባህሪይ እንደሚናገሩት ቃል  መልካም ሆኖ አለመገኘት ነው፡፡ ምዕመናን በአብዛኛው ከሚሰሙት ነገር የሚያዩትን ነገር ያምናሉ ከጆሮአቸው ይልቅ ለአይናቸው ይገዛሉ መምህራን ከሚያስተምሯቸው ልብን ከሚሰብር የማዳኑ የወንጌል ቃል ይልቅ የሰባኪውን ህይወት፣ አኗኗር በማየት
የሚሰበከው ይበልጣል ስለዚህ መምህራን ከሚናገሩት የሚኖሩት ነውና የሚሰማው ሰባኪያን ጠንቃቃ ሊሆኑ ይገባቸዋል አትስረቅ እያለ የሚሰርቅ አትግደል እያለ የሚገድል አትጠጣ እያለ የሚሰክር ሰባኪ በወንጌል ከሚወልዳቸው መንፈሳዊ ልጆቹ ይልቅ ከቤቱ የሚያርቃቸው ይበዛሉ
‹‹ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ ይህንንም ብታደርግ አንተንም የሚሰሙህንም ታድናለህ'' ጢሞ 4÷15 

አንዳንድ መምህራንም  የስብከታችን ዘዴ ተሰባኪያንን ወደ እግዚአብሔር ሳይሆን ወደ ራሳችን በማድረጋችን ትናንት የሰበክናቸዉና የመጡ ምእመናን እኛ ስንሰናከልና ስወድቅ እነሱም መዉደቃቸዉ ከቤቱም መቅረታቸዉ ለዚህ ተጠቃሽ ነው መጀመሪያም መምጣታቸው ለሰባኪው ፍቅር በመሆኑ ነው እግዚአብሔርን ካገኙ ግን ማንም ቢናወፅ እነርሱ ይጸናሉ ‹‹ከነዚህ ሰዎች ተለዩ  ተውአቸውም ይህ አሳብ ወይም ይህ ስራ ከሰው እነደሆነ ይጠፋልና  ከእግዚአብሔር እነደሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም'' እንዳለ ገማልያ ሐዋ 5÷39
2.3 ጥሪን አለማዳመጥ
ሌላው የተጠራንበትን ጥሪ ማወቅ፡፡ አንዱ መጠራት ለአገልግሎት (ለስብከተ ወንጌል) ነው ለዚህ ትልቅ አገልግሎት መጠራት መመረጥም ያስፈልገዋል አገልግሎቱ መንጋዎቹን መጠበቅ ነውና ይህም እግዚአብሔርን ለማፍቀራችን መንጋዎቹን መጠበቅ ተግባራዊ ምላሽ ነው፡፡
ሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚወደው ሲጠይቀው ‹‹በርግጥም እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ'' በማለት መለሰለት፤ እኔ እወድሀለሁ እንደምወድህም ሁሉን የምታውቅ አምላክ የውስጤን ታውቃለህ አለው ግልገሎቼን ጠብቅ! ጠቦቶቼንም ጠብቅ! በጎቼንም አሰማራ! የሚል ትእዛዝ ደረሰው በእርግጥ ለዚህ ትልቅ አላማ ነው ፍቅሩን የጠየቀው እንግዲህ ክርስቶስ ኢየሱስን እንወደዋለን ካልን ቀጥሎ በጎቼን ጠብቅ የሚል ትእዛዝ ይጠብቀናል ለዚህም ነው አገልግሎቱ እግዚአብሔርን የማፍቀራችን መገለጫ የሚሆነው፡፡ እግዚአብሔርን እናፈቅረዋለን ስንል መንጎቹን በመጠበቅ በመንከባከብና በማሰማራት ፍቅራችንን ልንገልጥ  ይገባናል፡፡

በጎቹን በአግባቡ እንዲጠብቁ ሳይመረጡ ሳይጠሩ
የመጡትን ተጠርተውም የተዘናጉትን እንዲህ ይላቸዋል  ‹‹በጎቼን ለሚበትኑ ምናምንቴ እረኞች ወየውላቸው''ኤር 23÷1
ይህም ምዕመናኑ በመምህራን የወንጌል ትምህርት ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ያደርጋቸዋል በመምህራኑ ላይ እምነት ከሌላቸው የሚያስተምረውን አይሰሙትም ከሚሰበሰቡት የሚበተኑት ይበልጣሉ ስለዚህም የመምህራኑ መጠራት ፍተሻ ያስፈልገዋል፡፡ ምዕመኑ የህይወት ለውጥ ላለማምጣቱ ተጠቃሽ ችግር ነውና፡፡
‹‹ከጥሩ ወርቅ ቅጠልን ስራ በላዩም ላይ ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ቅረፅበት በሰማያዊም ፈትል በመጠምጠሚያው ፊት ላይ ታንጠለጥለዋለህ በአሮንም ግንባር ላይ ይሆናል አሮንም የእስራኤል ልጆች በሚያቀርቡትና በሚቀድሱት በቅዱስ ስጦታቸው ሁሉ ላይ ያለውን ኃጢአት ይሸከም'' ዘፀ 28÷36
 
ብዙ ምእመናን ለክርስቲያናዊ ህይወታቸው መናጋት ካህናትን ምክንያት ሲያደርጉ እናያቸዋለን አንዳንዴም በጣም ሲበዛ ሰው ሁሉ ለመውደቅ ያዘመመ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ለመውደቁ ምክንያት የሚፈልግ ይመስላል፡፡ አንድ ጊዜ አንዱ የሚያከብረውን መምህር እኔ በህይወቴ በጣም ደክሜያለሁ
አንተ ግን አንድ ነገር ብትለኝ እንደምመለስ አምናለሁ ያለውን መጥቀስ ይበቃል፣ መመለሱ በልቡ ሆኖ መነገርን ይናፍቃል፡፡
ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚለውን ስናይ  የክብር አምላክ የሰማያዊው ንጉስ ባለሟሎች ናቸውና፤ ሰው መሆናቸውን እንኳን ማመን ሳንፈልግ በእግራቸው ስር የምንደፋው መስቀላቸውን ለማግኘት የምንጋፋው በፍፁም እምነት አምነን ሳንጠራጠራቸው ነው፡፡ ሚስት ለባል ባል ለሚስት የምንደብቀውን ሚስጥር መንገራችን ከዚህ ሁሉ ታላቅ እምነት መታመን አኳያ የምናይባቸው ነገር እንድንላላ ቢያደርገንም ጨርሶ ከመሰረታችን ሊነቅለን አይገባም፡፡
v   በርግጥ ካህን ታማኝ መሆን አለበት የማይታመን ዋስ አይሆንምና (ሌባ ለሌላ ሰው ዋስ መሆን ይችላል­­); ቢሆንም ተቀባይነት የለውም፡፡
v   ንፁህ መሆን አለበት ‹‹ከዘርህ በትውልዳቸው ነውር ያለበት ሰው ሁሉ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ'' ዘሌ 21÷16
ነቢዩ ኢሳይያስ ንጉሱ ዖዝያን ማዕጠንት ይዞ  ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ዝም ቢለው በከንፈሩ ላይ ለምፅ ወጥቶ
ከአገልግሎት ርቆ ነበር እግዚአብሔር ለአገልግሎት ሲጠራው ለመልእክት ሲያዘጋጀው ከንፈሩን አነፃለት (ኢሳ 6÷1 -10)
ካህን ለበጎቹ የሚራራ በጎቹን የሚያሰማራ መሆን አለበት፡፡
      ‹‹የራሱን በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል'' ዮሐ 10÷14
      እንግዲህ ከዚህ የምዕራፍ ጥቅስ እንደምንረዳው በእስራኤል በጎች ጠባቂ ወይም የበግ እረኛ ሽመሉን ይዞ በበጎቹ ፊት ጫካውን እየገለጠ እሾኹን እየጠረገ ድንጋዩን እያነሳ ይሄዳል በጎቹም እርሱ በጠረገው መንገድ በመልካም ይከተሉታል ግጦሽ ያለበት ሲደርስ  ሽመሉን ተክሎ ይቆማል በጎቹም ይግጣሉ የካህናትም አገልግሎት እንዲሁ ነው ለምዕመኑ የሚራራ ምዕመኑን የሚያሰማራ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ያለመታደል ሆኖ የኛን ሁኔታ ስናይ  ምእመኑ እሾኹን እየጠረጉ ጫካውን እየገለጡ ድንጋዩን እያነሱ ያልፋሉ የእረኛው ምሳሌ የሆኑ ካህናት በሰላም ይከተላሉ የተገላቢጦሽ መሆኑ ነው፡፡ ጋሪው ፈረሱን ሲቀድም
ከዚህም በላይ ካህኑ ነፍሱን ለበጎቹ አሳልፎ የሚሰጥ
መሆን አለበት ‹‹እውነተኛ እረኛ ነፍሱን ለበጎቹ አሳልፎ ይሰጣል'' ዮሐ 10÷11
       የካህናት አገልግሎት በመቅደስ  (ዘኁ 16÷40) የእግዚአብሔርንም ፍቃድ መጠየቅ (ዘዳ 28÷30) እንደሆነ የህይወታችን መመሪያ የሆነ መፅሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡
       አገልጋይ መሆን የእግዚአብሔርን ቤት ለማገልገል በመፈለግ ብቻ የሚገኝ ስጦታ አይደለም ዛሬ ዛሬ ካህን መሆን ብቻ የሚያስከብር የሚመስላቸው ካህኑ ሲቀድስ ሲባርክ በማየት ብቻ ውስጣዊ መንፈሳቸውን ቅናት ሲጭረው ስልጣነ ክህነት ለመቀበል የሚቀርቡ ብዙ ሆነዋል፡፡ አንዳንድ እህቶችም በተለያዩ ሁኔታዎች ባሎቻቸው ካህን እንዲሆኑላቸው ስለሚፈልጉ ብቻ የተጋነነ ቢመስልም ለጥሎሽ ከሚመጣው ልብስ ጋር የድቁና ካርድ ማየት እየናፈቃቸው ስለመጣ በጋብቻ ዋዜማ ክህነት ይሰጠን ብለው የየሊቃነ ጳጳሳቱን ቤት የሚያንኳኩ የበዙ ሆነዋል አልፎ ተርፎም የማይቀድሱበትን ድቁናና የማይባርኩበትን ቅስና የማይመንኑበት ብህትውና እና ምንኩስና መያዝ ለዛሬ እንግዳ አይደሉም፡፡

        በዚህም ምክንያት ያልተጠሩና ያልተመረጡ ናቸውና የሰማያዊው ዓለም ጉዞ ከብዷቸው እንዳሮጌ ባቡር ተንገጫግጨው ሲቆሙ የሚከተላቸው ሁሉ እየተላተማቸው ይወድቃል፡፡
2.4 የእረኞችና ጠባቂዎች ቸልተኝነት