Friday, February 6, 2015

የእረኞችና ጠባቂዎች ቸልተኝነት



2.4 የእረኞችና ጠባቂዎች ቸልተኝነት
     ከዚህ ቀደም ብሎ በተነሳው ጉዳይ ላይ መቼና መቼም ቢሆን ከእረኞች ወይም ከጠባቂዎች ውጪ ተጠያቂ ሊኖር አይችልም ክህነት የሚሰጡት እረኞቻችን ናቸውና አሁን ባለው አሰራር ዲቁና ቅስናና  ምንኩስና ለመስጠት በተቻለ አቅም ለዲቁናና ለቅስና የሚያበቃውን የቃል ትምህርትና ዜማ በመጠየቅና በዚህ ብቻ እንዲለኩ በማድረግ ክህነት ይሰጣል፡፡ መፅሐፍ ቅዱሳዊ እውቀትና ግብረገብነት ለምንኩስና አይጠየቅም፡፡ በተለይ ህዝበ ክርስቲያኑ በመፅሀፍ ቅዱስ እውቀት በበለፀገበት ዘመን ለክህነት የሚታጩትም ካህናት በአለም ውስጥ የሚያጋጥመውን የችግር መፍቻ ቁልፍ እንደመረከባቸው መጠን የመፅሀፍ ቅዱስ እውቀታቸውም ከምእመኑ በተሸለ መልኩ  ሊሆን ይገባዋል፡፡

       ይሁንና ክህነት የሚቀበሉ እነማንና እንዴት እንደሆነ መቆጣጠር መወሰንና መተግበር የሚገባው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዝም ብሏል፡፡ ለዚህም አሁን ከምናያቸው ያልተገባቸው ካህናት በላይ ምስክር የለም፡፡ በአጠቃላይ የቤተ
ክርስቲያኑ ተከታዮች ሁሉ በመፅሀፍ ቅዱስ እውቀታቸው የበለፀጉ በመንፈሳዊ ህይወታቸው የጠነከሩ ይሆኑ ዘንድ ከላይ እንደችግር የታዩት ሁሉ ፍተሻ ሊደረግባቸው ይገባል፡፡


ክፍል ሦሥት

በዚህ ሦሥተኛ ክፍል ለመዳሰስ የሚሞከረው በክፍል አንድና ሁለት የተነሱ ችግሮች መፍትሄ ሊያገኙ የሚችሉባቸው መንገዶች ሲሆን ባለፉት ክፍሎች ለተነሱ ችግሮች መፍትሄ ወይም መልስ ለመስጠት እጅግ ጥልቅና ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ በመሆኑ ይህንን እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ በክፍል ሁለት ዝግጅት በሰፊው ለመዳሰስ የተፈለገ ቢሆንም ለዚህኛው ዝግጅት እንደማጠቃለያ የተወሰኑ ሀሳቦችን ለመጥቀስ ይሞከራል
 
በምዕመናን በኩል ለተነሱ ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑት ራሳቸው ምዕመናኑ ሲሆኑ መጀመሪያ ፅድቁን መንግስቱን ፈልጉ ሌላው ይጨመርላችኋል ባለው አምላካዊ ቃል መሰረት ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡት መጽሐፍ ቅዱስ የሚማሩት የሚያስቀድሱትም ሆነ ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበሉት፣ የሚመፀውቱት፣ የሚጾሙትም ወዘተ የእግዚአብሔርን መንግስት ለማግኘት የፅድቁ ተካፋይ ለመሆን በመሆኑ ስጋዊ ፍላጎትንና አመለካከትን በሙሉ ወደኋላ በመተው ለመንፈሳዊ ህይወት እድገታችን መትጋት ይጠበቅብናል፡፡ የምንማረውን ትምህርት መስማት ከዚያም መተግበር በበጎ ስራ፣ በፆም በፀሎት በፍቅር
መገለጥ ይጠበቅብናል በኑሯችን ሁሉ ቅዱሳን በአለባበሳችን፣ በአነጋገራችን፣ በአመጋገባችን በአጠቃላይ በበጎ ስራ በመገለጥ ከአለም ተለይተን ለመታየት ይጠበቅብናል፡፡ ‹‹እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን÷ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከብደንን ኃጢአት አስወግደን የዕምነታችንንም ራስና ፈፃሚውን ኢየሱስን ተመልክተን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትግስት እንሩጥ››  ዕብ 12÷1 ና 2

በአገልጋዮች በኩል   መምህራን ለምናስተምረው ምዕመን ክብር መስጠት ለማስተማር ከመውጣታችን በፊት መማር ለማሳመን ከመነሳታችን በፊት  ማመን ይጠበቅብናል አገልግሎታችን የሰማይ አምላክን ፍቅር መግለጥ በበረቱ እንዲሰበሰቡ በፍቅሩ እንዲማረኩ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ ከጨለማ ወደ ብርሃን እንዲወጡ በመሆኑ ፍቃዱን መጠየቅ፣ መፀለይ፣ ማንበብና መዘጋጀት የምናስተምረውን ምዕመን ማወቅ መመጠንና መለካት ወጥና ግልፅ የሆነ ትምህርት ማስተማር በህይወትም ጭምር መስበክ ይጠበቅብናል፡፡
       ጣራ ላይ ለመውጣት መሰላል ወይም ደረጃ እንደሚያስፈልገን የእውቀት ጣራ ላይ ወይም እውነት ላይ ለመድረስ ትምህርትን በደረጃ መማር፣ ማንበብና በየቀኑ

መጋጀት  ማስተማርም ያስፈልጋል፡፡ 
        መጀመሪያ ላመነ ሰው የሚሰበከው፣ ለማእከላዊና ለፍፁማን የሚዘጋጀው ትምህርት አግባብ ባለው መልኩ ተዘጋጅቶ እስካልቀረበ ጊዜ ድረስ ሁሉንም በጋራ ይዞ መጓዙ ከውጤት አያደርስም የቀደመው ሲስብ የቀረው ሲጎትት ከአንድ ቦታ መንቀሳቀስ አይቻልምና፡፡ ‹‹የኃጢአትም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ይገኙ ዘንድ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ስልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ አይናቸውን ትከፍት ዘንድ›› ሐዋ 26÷17ና18

በቤተክርስቲያኒቱ በኩል፡- በቤተክርስቲያኒቱ በኩል ሲባል ቤተክርስቲያኒቱን በሚመሩ አካላት በኩል ለማለት ነው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሰው በፍቅርና በፅድቅ እንዲገለጥ ሊማር የሚገባውን ጠንቅቆ ማወቅ ወጥና ግልፅ ትምህርቶችን ማዘጋጀት ገና ወደ ቤተክርስቲያን ለሚመጣ ሰው በማእከላዊ ደረጃ ላለ እንዲሁም በፍፁምነት ደረጃ ላለ ሰው ሊማር የሚገባውን ማወቅ ማዘጋጀትና ተግባራዊነቱን መከታተል የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት የሚያምኑትን እንዲያውቁ ተከታታይነት ያለው ትምህርት መስጠት በመምህረ ንስሀዎቻቸው በኩል የሚማሩትን፣ ያወቁትን፣ ያመኑትን ውሏቸውንም መከታተል ሸክማቸውን መሸከም ድካማቸውንም ማገዝ ማበረታታት
ያስፈልጋል፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ምዕመናን ከቅናት፣ ከፍርሃት፣ ካለማወቅ እንዲሁም ከየዋህነት የሚወጡ የቤተክርስቲያኒቱን አላማ ከማይገልጡ ይልቁንም ከማመን የሚያዘገዩ ልማዳዊ ህጎችን የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያስወርሱ ከሚችሉ ፍፁም ከሆኑት ከቤተ ክርስቲያኒቱ አላማና ህግ ከዶግማና ከቀኖናዋ መለየትና ማጥራት ወዘተ ያስፈልጋል፡፡
በየጊዜውና በየወቅቱ በምዕመናን በኩል የሚመጡ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታ መንቀሳቀስ በክርስቶስ በማመን የመንግስቱ ወራሾች እንዲሆኑ ማስተማርና ማረጋገጥ እንዳስፈላጊነቱ መገሰፅ ወዘተ ይጠበቅባታል
‹‹ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ አምናችሁም በስሙ ህይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተፅፎአል›› ዮሐ 20 31