ይድረስ ለቅዱስ ሲኖዶስ
የኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ረጅም እድሜ ያስቆጠረችና ከአርባ
ሚሊየን በላይ ተከታይ ያላት ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ በክርስቶስ ደም በሀዋርያት የጠራ ትምህርት ላይ
የተመሰረተች በመሆኗ ለዘመናት የሲኦል ደጆች ሳያናዉጧት እዚህ ደርሳለች፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቀደም ባሉት ነገስታት እስከ
1966 ዓ.ም ድረስ ሀገርን የመምራትን ሀላፊነት ጭምር ደርባ በመያዝ
ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን የእድገት ጎዳና እንድትይዝ ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ ኖራለች፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን
ለኢትዮጵያ ህዝብ ያበረከተችው አስተዋጽኦ መጠኑ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይልቁንም ቀደም ባሉት ነገስታት ዘመን ቅብዓ ሜሮን በመቀባት ከማንገስ ጀምሮ ህግ በማርቀቅ በማውጣት እንደ ፍትህ
ሚኒስቴር፣ ዐፄ ምኒልክ ’’ዳግማዊ ምኒልክ’’ ብለው በራሳቸው ስም
የሰየሙት ትምህርት ቤት እስኪከፈት ድረስ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ቤተ ክርስቲያናትን በአጸድ በማስዋብ በመንከባከብ
እና በመጠበቅ እንደ ግብርና ሚኒስቴር በመሆን በአጠቃላይ ሀገሪቱን አሁን ላለችበት የእድገት ጣሪያ መሰረት በመሆን አገልግላለች፡፡
የኢትዮጵያ
ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ከ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ የሥነ ጽሑፍ ፣የታሪክ፣ የትምህርት በአጠቃላይ የኪነ ጥበብ መገኛ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡
ከነዚህም ገዳማት በትምህርት ተኮትኩተውና አድገው የሚወጡት ዲያቆናት፣ ቀሳውስት፣ መነኮሳትና ጳጳሳት ብቻ ሳይሆን ሀገርን የሚመሩ
ነገስታትም ጭምር ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ በሀገሪቱ በንግስና የሚቀቡ ነገስታት በቤተ ክርስቲያኒቱ በመሆኑ ነገስታት የቤተ ክርስቲያቱ አባል መሆንም ግዴታ ነበረባቸው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱም ይህንን ጭምር
ትከታተል ታስተምርና ትመራ ነበር፡፡ ሀገሪቱን የሚመሩ ነገስታት እንኳን ቢሆኑ ከቤተ ክርስቲያቱ ሥርዓተ እምነት ቢያፈነግጡ ፣አላማቸውን
ቢስቱ ቤተ ክርስቲያን ከንግስና የማዉረድ ስልጣን እንደነበራት ታሪክ ያስረዳል ለምሳሌ አጼ ዘ ድንግል በ1904 እ.ኤ.አ እና አጼ ሱሱኒዮስ በ1962 እ.ኤ.አ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ክደው የሮማን ካቶሊክ እምነት በመቀበላቸው ከስልጣናቸው የተነሱ ሲሆን ልጅ እያሱም የእስልምና
ኀይማኖት ተከትለሃል በማለት ተከሶና ተወግዞ ተለይቷል፡፡
ከዚህም
የተነሳ ነው የኢትዮጵያን ታሪክን ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክን ነጣጥሎ ማየት አይቻልም የሚባለው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ማለት
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ
ክርስቲያን ታሪክ ማለትም የኢትዮጵያ ታሪክ ማለት ነው፡፡
በዚያ
በቀደመው ዘመንም ቤተ ክርስቲያኒቱ የጠነከረ ተቋማዊ አስተዳደር ስለነበራት ምዕመኗን በአግባቡ ስታስተዳድር ስታስተምር ስትመራ ኖራለች፡፡
ችግሮቿን ራሷ ትናገራለች መፍትሄም ትሰጣለች፡፡ ትጠየቃለች እራሷ ትመልሳለች፡፡ እዚህ ላይ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ የንግስና ዘመን
ቤተ ክርስቲያኒቱ ንጉሰ ነገስቱ በሚገኙበት ፓትርያርኩ ባሉበት በወወክማ/ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ/ ጥያቄና መልስ ፕሮግራም
እንደነበረ ማስታወስ ይበቃል፡፡ በዚህ መልክ እራሷን ትመራ ታስተዳድር ነበር፡፡
ከ
1966 ዓ.ም በኋላ ግን ድንገት በመጣ ለውጥ ቤተ ክርስቲያን ባልጠበቀችውና ባላሰበችው ሁኔታ የጠነከረ ተቋምነቷ ከንጉሰ ነገስቱ
ስልጣን ጋር ሲያበቃ አሁን ያለችበትን አስተዳደራዊ መዋቅር ለመዘርጋትና ለመያዝ ልትቸገር እንደምትችል መገመት አያዳግትም፡፡ ይሁን
እና ቤተ ክርስቲያን ከንጉሱ ስልጣን ማብቃት ጋር የቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የሰበካ ጉባኤን በማደራጀትና
በማቋቋም እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በመዘርጋት ፈጣን እርምጃ በመውሰድ
ተቋማዊ ማንነቷን ለማስከበር ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች፡፡ በዚህ የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር የዘመናት ጉዞ ትውልድ የማይዘነጋቸው የቤተ
ክርስቲያኒቱ የቁርጥ ቀን ልጆች እየተፈጠሩ እያለፉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙ አሳልፋለች፡፡ ዛሬ ዛሬ ይህንን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጠንካራ ተቋምነት የሚፈታተኑ ነገሮች
እየታዩ ናቸው፡፡ እንደውም የአንዳንዶቹ ችግሮች መጠንከር፣የማናለብኝ ባዮች መብዛት፣ ተጠያቂና መላሽ ነን ባዮች ከቤተ ክርስቲያኒቱ
የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ የማይገኙ መሆናቸው፣ የቤተ ከርስቲያኒቱም ዝምታ ቤተ ክርስቲያኗ በእውነት አለች? የማን ቤተ ክርስቲያን
ነች? የሚያስብል ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስለኛል፡፡
ይህንን
ጽሑፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ዋናው ሀሳብ በዝቋላ ገዳም ጸበል ቦታ ላይ የእሬቻና በዓል እንከብራለን የመታሰቢያ ሀውልትም እንቆማለት
የሚለውን አስደንጋጭ ዜና ከሰማሁ በኋላ ነው ነገር ግን በዚህ መንፈስ ከተነሳሁ አይቀር በነካ እጄ ብዬ ችግሮች ናቸው ወይም ነገም
ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ ያልኳቸውን ሀሳቦች ለማንሳት ሞክሬአለሁ፡፡
ምንም
እንኳን ቤተ ክርስቲያኒቱ ባደረገችው ከፍተኛ ትግል የታሰበው እና የታለመው ውጥን ባይሳካም ለእኔ ሰነፍ እረኛ ከሩቅ ይመልሳል አይነት
ነው የሆነብኝ፡፡
አንደኛ
ይሄንን ያክል ድፍረት እንዴት ሊታሰብ ቻለ? እኛ ጉዳዩን ዛሬ ሚድያ ላይ ሲወጣ ሰማነው እንጂ ገዳምያኑ ቀደም ባሉት ተከታታይ ዓመታት
ሁሉ ፈተና መከራና እንግልት እንደደረሰባቸው በተጨባጭ ያስረዳሉ፡፡ ሌላው ዛሬ በዚህ መልክ የተነሳው ነፋስ እስከ መጨረሻው ተዳፍኗል
የሚል ጥያቄም ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ጎልቶ የሚታየው ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደ እንድ ተቋም መብቷ ተከብሮ የስርዓተ
አምልኮ፣የቀብር፣ የታቦተ ህግ ማደሪያ/ጥምቀት/ የደመራ ቦታዎቿ የማይከበሩበት ሁኔታ የሚፈጠረው ለምንድን ነው? በአንድ ወቅት አንድ
ቦታ ላይ የሥላሴ ጥምቀተ ባህር ወይም ታቦት ማደሪያውን በጊዜው በነበረው አገዛዝ ይነጠቃል የክፍሉ ሊቀ ጰጳስ/ቀዳማዊ ጎርጎሬዎስ/ በቀጥታ ሃላፊው ጋ ገብተው ስላሴን በፈጠሩት መሬት
ማደሪያ ታሳጣቸው ብለው እንደነበር ታሪክ ሰምቻለሁ፡፡ ታዲያ ይህች ቤተ ክርስቲያን ያደረገችው ሰፊ ውለታ ተረስቶ ባቆየችው ታሪክ፣ባህል በመራችውና ባስተዳደረችው
ሀገር ቦታ መነሳቷ ለምን ይሆን? ዛሬ በዝቋላ ያየነው ሀሳብ በሌሎች ቦታዎችም እንደማይቀጥል ምን ማረጋገጫ አለ? በነደደ ቁጥር
ለማጥፋት ከመታገል ቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታዋን ልታስከብርበት የምትችልበት ህጋዊ ሰውነት ለምን የላትም? እንደ ተቋምስ መብትና ግዴታዋን
ተንትና አብራርታ የያዘችበት፣ የምታስከብርበት፣የመታስወስንበት ህግስ አላት?
ሌላም አሳሳቢ ጉዳይ አለ ቤተ ክርስቲያኒቱ እና
ምዕመናንስ ምን ያክል ይተዋወቃሉ?
1. ቤተ ክርስቲያኒቱ እና ምዕመናን
1.1
ቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመኗን በእርግጥ ታውቃቸዋለች?
ቤተ
ክርስቲያኒቱ ምእመኗን ታውቃቸዋለች ሲባል መጀመሪያ የሚነሳው ጥያቄ አብዛኛው አማኝ ቤተ ክርስቲያን የሚሄደው መቼ ነው? ቤተ ክርስቲያኒቱ
ለምታወጣው ህግስ ምን ያህል ተገዢ ነው? መንፈሳዊ አባቶቹንስ ያውቃቸዋል? ያከብራቸዋል? ለትምህርታቸውን በመንፈስ ይገዛል? ቃላቸውንስ
ያከብራል? የሚሉትን ጥያቄዎች ሊያጠቃልል ይችላል፡፡
ቤተ
ክርስቲያኒቱ የሰበካ ጉባኤ አስተዳደርን በመዘርጋት ከላይ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ ታች አጥቢያ ቤተ
ክርስቲያን ድረስ የተደራጀ እና የተጠና ሰንሰለት በመዘርጋቱ በየትኛውም ቦታ ያለች ቤተ ክርስቲያን በዚህ አስተዳደር ታቅፋለች ትታወቃለች፡፡ ይህም መዋቅራዊ አስተዳደሯ እጅግ የጠነከረ
ለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ነገር ግን ታች ያለችው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የምትታወቀውን ያክል በውስጧ ያሉት ምእመናን ቁጥር፣
ጾታ፣ ክርሰቲያናዊ አቋማቸው በመንፈሳዊ ትምህርት ደረጃቸው ይታወቃል ብዬ አላምንም፡፡ በእርግጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ በየአምስት ዓመቱ
አንድ ግዜ የቤተ ክርስቲያናትን እና ምእመናን ቆጠራ ታደርጋለች፡፡ ነገር ግን በየሀገረ ስብከቱ በየወረዳ ቤተ ክህነቱ ሀላፊነት
ላይ ያሉ አንዳንድ ተጠሪዎችም ሆኑ በየአጥቢያው የሚገኙ የሰበካ ጉባኤ አባላት ተመራጮች ስለ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ምዕመናን/ህዝብ/ቆጠራ
ምንም የማያውቁና ሥልጠናም የማይሰጣቸው ቆጠራዉ የሚሰጠው ጥቅምም ሆነ ጉዳት በውል የማይረዳቸው በመሆኑ ቆጠራው የሚፈለገውን ግብ
እያስገኘ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በዚህ ከላይ በጠቀስነው የቤተ ክርስቲያኒቱ
ኃላፊነት ያሉ ጥቂት ግለሰቦች የጠነከረ ክርስቲያናዊ ማንነት ወይም እምነት የሚያንሳቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አብያተ ክስርቲያናትን
እና ምዕመኗን በአግባቡ አደራጅቶ መጠበቅ ከዚያም በአግባቡ ቆጠራውን
ማከናወን ከሚያስገኘው ከፍተኛ ጥቅም ይልቅ ሥልጠና አልተሰጠንም፣ የሥራ ማስኬጃ አልተመደበልንም አበል አልተቆረጠልንም በሚሉ ጥቃቅን
ምክንያቶች የማያውቁትን እና ያላስተማሩትን ምዕመን ቁጥር በነሲብ ቢሮአቸው ቁጭ ብለው የሞሉትን አሀዝ የሚያስተላልፉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ለዚህ ነው በትክክል ወይም በእርግጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመኗን ታውቃቸዋለች ወይ የሚያስብለው፡፡
1.2
ቤተ ክርስቲያኒቱ በቀጥታ ወደ ምዕመኗ ትደርሳለች
ቤተ
ክርስቲያኒቱ በእጅጉ ልትመልሰውና ልታስብበት የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደ ምእመኗ በቀጥታ ትደርሳለች፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞቿ ከአርባ ሚሊየን በላይ እንደሆኑ ይገመታል፡፡ አብዘኞቹ በየጥጋጥጉ በድህነት የወደቁ፣ አልባሌ በሆነ
ሥራ የተሰማሩ፣ በየ ፍርድ ቤቱ የሚመላለሱት እና በየማረሚያ ቤቶች የሞሉት አብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል የዚህች አንጋፋ እና ታሪካዊ
ቤተ ክርስቲያን አባል ናቸው ወይም አባል ነን ባዮች ናቸው፡፡ ታዲያ በዚሁ ቁጥር ልክ ወይም በሙሉ ማለት ይቻላል በማስተዋል ከመረመርነው
ከስሙ ወይም ከጥላው አንድ መሆን ውጪ በእንድ ቀኖና እና በእንድ ዶግማ ላይ የተለያየ አመለካከት፣ የተለያየ አስተሳሰብ፣ የተለያየ
ትንታኔ፣ የተለያየ ስርዓት፣ የተለያየ አስተምህሮ ይበዛል፡፡ ይህም ችግር ምዕመኑ ከቤተ ክርስቲያቱ የሚወጣውን ህግ፣ሥርዓት፣ ደንብ
አስተምህሮ በቀጥታ ከምንጩ ማግኘት ካለመቻል የሚመጣ ችግር ይመስለኛል፡፡ ምንም እንኳን ዓመት በተለወጠ ቁጥር በዘመን መለወጫ የዓመቱን
አጽዋማትና ስርዓት ወይም ባህረ ሀሳብ በሊቃውንቱ የሚነገር ቢሆንም ይህንን የሚሰማውና የሚያስተውለው ሰው ባለመኖሩ፡፡ የሚሰማው
ቢኖርም እንኳን የተናጋሪዉን ሊቅነት ከማድነቅ በዘለለ በአግባቡ የሚሰማ ባለመኖሩ፡፡ የገና ጾም የሚገባው መቼ ነው? ለምን በዚህ
ቀን ይገባል? ገና ጋድ አለው ጥምቀትስ? ስንት ጋድ አለ? ጋድ ማለት
ለውጥ ማለት ነው የጥምቀት እለት ረቡዕ ወይም አርብ ካልዋለ ምኑን ነው የምንለውጠው ስለዚህ ጾም አይደለም አሳ በጾም ይበላል?
ዶግማና ቀኖና ማለት ምን ማለት ነው? እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ሁል ጊዜ የመድረክ አድማቂዎች ይሆናሉ፡፡ ይሄ እውነት የሚጠቁመን ቤተ ክርስቲያኒቱ በቀጥታ ተከታይዎቿን የምትደርስበት ምንም አይነት መንገድ
አለመኖሩን ወይም በጣም የጠበበ መሆኑን ነው፡፡ ስንቱ አማኝ ቤተ ክርስቲያን የምታሳትመው የራሷ የሆነ ጋዜጣ እንዳላት ያውቃል? በየወሩ የሚታተም እና ለምዕመኑ የሚደርስ መጽሔትስ አላት?፡፡ ለመሆኑ በቀጥታ
መዕመናኗን የምትመክርበት፣ የምታስተምርበት፣የምታጽናናበት መንገድ የትኛው ነው?፡፡
ይህንን
የመሳሰሉ ምዕመኗ ጋ በቀጥታ ሊያገናኛት የሚችል ቋሚ እና አስተማማኝ መስመር ስለሌላት ለቤተክርስቲያኗ ቀናዒ የሆኑና ቀናዒ ነን
የሚሉ ሰባኪያንና ማህበራት እንዲሁም የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ሁሉ ይህንን መስመር በመዘርጋት ምዐመኑ ጋ በመድረሳቸው የተለያየ
መልክ እና እምነት ያላቸው ግን ስማቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አባላት ነን የሚሉ ምዕመናን ተፈጥረዋል፡፡ እነዚህም
ከፊሉ መድሃኒቷ ከፊሉ ደግሞ በሽታዋ ሆነዋል፡፡ እነዚህንም ማረም ወይም ማስተካከል ወደማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ አብዛኛው
ምዕመን እነዚህን ሰባኪያን እና ማህበራት ከቤተክርስቲያኗ መለየት አቅቶታል፡፡ የሚሰማው እና የሚያምነው ማህበራቱና ሰባኪያኑ የነገሩትን
ስለሆነ ስህተት ቢሆኑም እንኳን እነሱን ማረም እና መገሰጽ ከተከታዮቻቸው ጋር መጋጨትን ከዚህ ሲዘልም ቤተክርስቲያንን እስከመክፋፈል
ሊያደር የሚችል ግጭት ሊያስከትል ይችላል የሚል ፍራቻ ያሳድራል፡፡
በእርግጥ
ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታሳትማቸው በራሪ ወረቀቶች እና መጽሔቶች አሏት ቢሆንም ይህ ሥራ በተለይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን የሆነው
ጋዜጣ ዜና ቤተ ክርስቲያን ቀደም ባሉት ጊዜያት በአንድ ሰው ትከሻ
ላይ ብቻ የወደቀ ነበር፡፡ ስለሆነም እሱው ጸሐፊ እሱው አርታኢ ፤አሱው አሳታሚ እሱው አከፋፋይ ወይም ሻጭ በመሆን እየሠራ ከ60
ዓመት በላይ እድሜ አስቆጥሯል፡፡ ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ አንድ ፎርም አዘጋጅታ ለአማኞቿ በሙሉ ቤተ ክርስቲያን የምታሳትማቸው መጽሔቶች
ጋዜጦች በራሪ ወረቀቶች ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትተዳደርበትን ህግ የያዘው የህግ መጽሐፍ ምን? ማን ይባላሉ? ብላ መጠይቅ ብትሰበስብ
ስንት ሰው ይመልስ ይሆን? ይህንን ሀሳብ ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም ብዙ ጊዜ የቤተ ክርስቲያኒቱን እምነት አቋም ትምህርቶች
የያዙ ጠቃሚ መረጃዎችን የሚይዙት የህትመት ውጤቶች የህትመት ቁጥራቸው ጥቂት ከመሆኑ በላይ እነሱም ታላላቅ በዓላትን የንግስ ቦታዎችን
እና ታላላቅ ደብሮቸን ያማከሉ በመሆናቸው ለሁሉም ምዕመን በእኩል መጠን የሚዳረሱ አይደሉም፡፡ አንዳንዴ በታሰበው የንግስ ቦታ ወይም
ታላቅ በዓል ላይ የመጣው ህዝብ የታተመውን ሁሉ መጽሔት ጋዜጣ ወይም በራሪ ወረቀት ተካፍሎ ከጨረሰው አበቃ ለሌላ አይደርስም አከፋፋዮቹም
ህትመቱ ከእጃቸው ተሸጦ ማለቁን እንጂ ጠቃሚ ትምህርት፣ ምክር፣ መረጃ ይዟልና ለሁሉም ይዳረስ ብለው የሚተጉ አይመስለኝም፡፡ አንዳንዴም
በየ ንግስ ቦታዎች በየ በዓላቱ እንዲሰራጩ ተብሎ ወደየ ሀገረ ስብከቱ የሚላኩ የህትመት ውቶችም በሀገረ ስብከቱ ንብረት ክፍል ታጭቀው
የሚቀሩ ቀላል ቁጥር ያላቸው አይደሉም፡፡
1.3
ምዕመኗስ ቤተ ክርስቲያኒቱን በየኔነት ስሜት ያዉቋታል?
ቤተ
ክርስቲያን አማኞቿን በቀጥታ ስለምታገኝበት መንገድ መጨነቅ ያስፈለገው ለምንድን ነው? ብንል ግብረ መልሱ ምንድን ነው? የሚለውን
እንድናይ ያደርገናል እነሱስ ቤተ ክርስቲናቸውን ምን ያክል ያውቋታል? ምን ያክል ለህጓ ይገዛሉ ምን ያክል ቃሏን ይሰማሉ ያከብራሉ
የእኔነት ስሜትስ ይሰማቸዋል?፡፡ አሁን አሁን በትንሹ የረገበ ቢመስልም በአንድ የንግስ ቦታ ፣በአንድ ቤተ ክርስቲያን ፣በአንድ
በዓለ ንግስ ብዙ አይነት መምህራን ይቆማሉ በውስጥ ቅዳሴ በጎን የህብረት ዝማሬ ፤በውጭ የባህታዊ ነን ባዮች ትምህርት ፤የግል ፀሎት፤
እሱኑ የሚያስተጓጉሉ ምጽዋት ሰብሳቢዎች፤ ሞንታርቦዋቸውን ከሁሉም ድምጽ
ከቅዳሴውም ስብከቱም በላይ ከፍ አድርገው ካሴት የሚሸጡ ፤የሚለምኑ ከሚለበስ ልብስ እስከ ቤት አቃ ድረስ ዘርግተው የሚሸጡ
ነገዴዎች፤ ኪስ የሚዳብሱ ዘራፊዎች ሁሉም ይሰለፋሉ፡፡ የሚገርመው ግን ሁሉም ሰሚ አላቸው፤ ሁሉም አድማጭ አላቸው ፤ሁሉም ተሳታፊ
አላቸው ፤ሁሉም ተሰላፊ አላቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ በአንድ ሀሳብ በአንድ ልብ በአንድ ስሜት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ይገዛሉ ቃሏን ያከብራሉ
ማለት አይቻልም፡፡ በአንድ ልብ ያፈቅሯታል ማለት አይቻልም፡፡ ሁሉሙ የእኔ ናት ብለው ይቀኑላታል ማለት አይቻልም፡፡ ውስጥ ያለው
ውጪ ያለውን ሲያወግዝ አብሮ የሚያወግዝ አለ፡፡ ውጪ ሆኖ የውስጡን ሲሳደብ ሲራገም አብሮ የሚሳደብ የሚራገም አለ፡፡ በጎን ሆኖ
ሲዘምር ተው የሚል፣ አብሮ የሚዘምርም አለ፡፡ ለነጋዴውም ለሚለምነውም ጥብቅና የሚቆምም አለ፡፡ ታዲያ ምዕመኑ ቤተ ክርስቲያኒቱን
በእኔነት ስሜት ያከብራታል ማለት ይቻላል? ወይስ በሚሰጠው ልክ እየመለሰ ነው፡፡
1.4
ቃል አቀባይዋስ ማነው?
መንግስታት
ለሚሰሩት ስራ፣ ለህዝባቸው ሊያስተላልፉት ለሚፈልጉት ሀሳብ ወይንም አቋማቸውን ለመግለጥ ወይም ለህዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት ሲያስፈልግ
አሊያም ስለወቅታዊ ጉዳይ ለህዝቡ መድረስ ያለበት ጉዳይ ካለ እንደአስፈላጊነቱ ርእሰ ብሔሩ አሊያም ቃል አቀባዩ ሁኔታውን ይገልጣል
፣ያስረዳል፣ ይጠየቃል ይመልሳል፡፡ ይመለከተኛል የሚል አካል ቢኖር
እንኳን ጉዳዩን ስለሚያውቀው ብቻ መግለጫ አይሰጥበትም፡፡ ማንም ተነስቶ በሚፈልገው ጉዳይ አያወራም፡፡ መልክና ውበት ሥርዓት ባለው
መልኩ በሚመለከተው በተፈቀደለት አካል ብቻ ጉዳዩ መግለጫ ይሰጥበታል፡፡
በቤተ
ክርስቲያቱ ግን እንዲህ ያለ ስርዓትና ህግ የተዘረጋ አይመስለኝም ስርዓቱ ቢዘረጋም እየተጠቀመችበት ነው ብዬ አላምንም፡፡ የቤተ
ክርስቲያኒቱ መሪዎች አልፎ አልፎ ከሌሎች የእምነት ድርጅት ሀላፊዎቸ ጋር ተርታ በመግባት ለዜና በሚመች መልኩ መልካም ተመኝተዋል፣
መልእክት አስተላልፈዋል፣ አቋማቸውን ገልጠዋል ተብሎ ከሚቀርብ ቁንጽል ሀሳብ የዘለለ ሥለ ስርዓቷ እምነቷ አቋሟ ህገ ደንቧ ሲገልጡ
ሲያብራሩ ብዙም አይተን አናውቅም፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ከቤተ ክርስቲያቱ እውቅና ውጪ የቤተ ክርስቲያኒቱ አቋም እስኪመስል ድረስ
የሚሰሙ የሚነገሩ ነገሮች ግን ብዙ ናቸው፡፡
ከዚህ
በተጨማሪም ይህንን ሰፊ ክፍተት በመጠቀም ግለሰቦች፤ግለሰብ ሰባኪያን እና የተለያዩ ማህበራት በተለያየ ጊዜ እንደቃል አቀባይ ሲያገለግሉ
ይታያል፡፡ የስንቱ አቋም እና ዕምነት የቤተክርስቲያኗ እንደሆነ የሚያውቀው አምላክ ብቻ ነው፡፡
ስለሆነም
በየ መጽሔቱና ጋዜጣው ቤተ ክርስቲያኒቱ ከባድ ችግር ላይ ናት! ከባድ ፈተና ውስጥ ገብታለች! የሚፈትኗትም ከባድ ችግር የሆኑትም
እነ እገሌ ናቸው! ይሄ ፍርድ! ይሄ እገዳ! ይሄ ውግዘት! ይገባቸዋል እየተባለ ብዙዎች ይከሰሳሉ፤ ብዙዎች ይወገዛሉ፡፡ በሌላ ጎን
ደግሞ ችግሩ የነሱ አይደለም፣ ችግር ተፈጥሯል የሚሉት ችግር ፈጣሪዎች ራሳቸው ናቸው እኛ እያለን ማን ይነካቸዋል? ማን ይከሳቸዋል? ማን ያወግዛቸዋል? እየተባለ ውጪ ይጠየቃል፡
ውጩ ይመለሳል ፤ውጪ ይከሰሳል፤ ውጪ ማስተባበያ ይሰጣል፤ ውጪ ይታሰራል፤ ወጪ ይወገዛል፤ ውጪ ይፈታል፡፡ከዚህ አለፍ ሲልም ቤተክርስቲያን የሁሉ ናትና በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለውን ዝምታ ተገን
በማድረግ በተለያየ ጉዳይ በመንግስት ያኮረፉ፣የተባረሩ፣የተገፉ ሁሉም በቤተክርስቲያን በመጠለል የተባረሩበትን፣ያኮረፉበትን እና የተገፉበትን አቋማቸውን ከቤተክርስቲያን ሆነው ሲያስተላልፉ ተዉ የሚል
አካል የለም፡፡
በእነዚህ
ሁሉ ጉዳዮች መካከል ቤተ ክርስቲያን ይሄ የኔ ጉዳይ ነው፤ ይሄ የኔ ችግር ነው፤ ማየት፣ መስማት ፣መመርመር ፣መፍረድ እና ማውገዝ
ያለብኝ እኔ ነኝ ብላ ግን መብቷን ስታስከብር አትገኝም፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላሰማራቻቸው ዘበኞች፤ ያልመለመለቻቸው ጥበቃዎች፤ያላሰለጠነቻቸው
ቀሳውስቶች፤ ሰባክያነ ወንጌል/መምህራን/ የማታውቃቸው ጠበቆች፤ የማታውቃቸው ቀሳውስት ያላመነኮሰቻቸው መነኮሳት፤ ያልላከቻቸው አበ
ነብሶች፣ያላቋቋመቻቸው ማህበራት ብዙ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያልጻፈቻቸው መጻህፍት፤
ያላሳተመቻቸው መጽሄቶች ጋዜጦች ያላረቀቀቻቸው ህጎች፤ የማታውቃቸው ድንጋጌዎች፤ያላዜመቻቸው ዜማዎች/እነዚህ ሁሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ስርዓትና ደንብን ተከትለው የታተሙ የተጻፉ የሚል አለባቸው/፤ ያልመረጠቻቸው ቃል አቀባዮቿ ብዙ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያቱ ያልሰደበቻቸው የተሰደቡ፤ያልለየቻቸው የተለዩ፤ያላወገዘቻቸው
የተወገዙ ፤ያላሳደደቻቸው የተሰደዱ ብዙ ናቸው፡፡ ሊወቀሱ ሲገባ ያልተወቀሱ፤ሊታረሙ ሲገባ ያልታረሙ፤ሊለዩ ሲገባ ያልተለዩ፤ሊመከሩ
ሲገባ ያልተመከሩ፤ሊታዩ ሲገባ ያልታዩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ብዙ ናቸው፡፡ በታላላቅ በዓላት እንደ ጥምቀት መስቀል እና በመሳሰሉት
ግዚያቶች የተሰማውን የበዓሉን ሁኔታ የስርዓቱን ማማር ከሚገልጹ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር መእመናን ባሻገር ስርዓቷን፣እምነቷን፣አስተዳደሯን፣ስልጣኔዋን፣እድገቷን፣
የአብያተ ክርስቲያኒቱን አወቃቀር፣የገዳማቷን ስርዓት፣የቆሎ ትምህርት ቤቷን በመሳሰሉት ቤተ ክርስቲያኒቱን እና ቤተ ክርስቲያኒቱን
ብቻ የሚመለከቱ ጉዳዮችን መግለጫና ማብራሪያ የሚሰጡ ሰዎች እና ማህበራት አንዳንድ ግዜ በቤተ ክርስቲያኒቱን ቀጥተኛ የአስተዳደር ሥራ ወይም ሰንሰለት ውስጥ የሌሉ
መሆናቸውን ስናስተውል በቀደመው ጊዜ የሀገሪቱን ህግና ስርዓት የቀረጸች፤ሀገር የመራች፤የሀገር መሪዎችን የመረጠች፣የመከረች እና
የቀጣች መሆኗ ታሪክ እየነገረን፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅሩን፣ሥርዓቱን፣ደንቡን ማብራራትና መግለጥ የሚችሉ፤እምነቷን ማስረዳት
የሚችሉ ሊቃዉንት የላትም እንዴ? ያስብላል፡፡
ይሄ
ሁሉ ችግር የተፈጠረው በኔ እምነት ቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጧንም ይሁን
የውጭዋን ችግሯንም ይሁን መፍትሔዎቹን፤መፍታቷንም ይሁን ማውገዟን በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያኒቱን የተመለከተ ጉዳይ በራሷ ሊቃውንት
በመደበችው ቃል አቀባይ የምትገልጥበትን መንገድ ስላላመቻቸች ለተግባራዊነቱም ስላልተሰለፈች ይመስለኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆቿን
ታስተምራለች፤ካስተማረች በኋላ ትጠላቸዋለች፣ ታሰራለች ከሰሩ በኋል ትገፋቸዋለች፣ ትጠራለች ከጠራች በኋላ ታበራቸዋለች፣ ታሰራለች
አታመሰግንም፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በአብዛኛው ሰዎች በጎ ላልሆነ ስራቸው ተገቢውን ቅጣት ያገኛሉ የወቀሳ፣ የማስጠንቀቂያ፣
የዝውውር፣ የስንብት ደብዳቤዎች ይወጣሉ፡፡ የምስጋና፣ የመልካም ሥራ ውጤት ደብዳቤዎች ግን አይታዩም፡፡
እዚህ
ላይ ግን ቤተክርስቲያኗ ስል በአመራር ላይ ያሉትን መሪዎቿ ማለቴ መሆኑ ይታሰብልኝ ቤተክርስቲያኗ ግን ሎጆቿል አትገፋም፤አታበርም፤አትጠላም፡፡
ከዚህም
የተነሳ ቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመኗን በአንድ ልብ ማግኘት አትችልም፡፡ ገሚሱ ከሚያወግዙት ጋር ያወግዛል፤ከሚተቹት ጋር ይተቻል፤ከሚሳደቡት
ጋር ይሳደባል፤ ከሚያሳድዱት ጋር ያሳድዳል፡፡ ገሚሱ ደሞ በተቃራኒዉ ይቆማል፡፡
ምንአልባት
ብዙ ሰው በሀገር ውስጥ ያለ ሲኖዶስ፤በውጪ ያለ ሲኖዶስ፤ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን እያለ መከፋፈሉን አለመስማማቱን እዛ ላይ ብቻ
ሰቅሎ ያስብ ይሆናል አዉርደን ካሰብነው ግን እዚህም ትናንሽ መከፋፈሎች ብዙ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትለውን የሚሰማ፣ በቅርቡ
ያሉት የሚነግሩትን የሚሰማ ከሁሉም ገለልተኛ ሆኖ የሚያስተውል ብዙ ሰው አለ፡፡ ምናልባትም ቤተ ክርስቲያን የራሷን ተቋማዊ አደረጃጀት
በማጠናከር እስካላስተካከለችው ድረስ የሚቆም አይመስልም፡፡
ስብከተ
ወንጌልንም በተመለከተ ተመሳሳይ ሀሳብ የሚያስነሳ ይመስለኛል ሰባኪያነ ወንጌላቱ እነማን ናቸው ማነው ያሰማራቸው ምን እንዲያስተምሩ
ነው የተሰማሩት በስንት ተከፋፍለዋል ልምንድነው የተከፋፈሉት ከነዚህ መምህራን የተነሳ ከየትኛውም የሀገሪቱ አቅጣጫ የሚመጣ የቤተ
ክርስቲያኒቱ አማኝ/ምዕመን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቱ ተመሳሳይ ነው ወይ እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ብናነሳ መልሱ ውስብስብ ነው ይሔንን
ችግር የሚፈታው ወይም ሊፈታ የሚገባው ማነው ብንል ሁሉንም ችግር እያወቀ ነገር ግን በዝምታ የሚያስተውለው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው
ይቆየን