በ144
ዓ.ም መርቅያን የሚባል ቤተ ክረስቲያኒቱን በእጅጉ ከፈተኑት መናፍቃን መካከል የሚመደብ ሰው ተነስቶ ነበር፡፡ መርቅያን በክህደቱ
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከምናውቃቸው፣ በዘመናችንም ከምንሰማቸው ተጠራጣሪዎች የተለየ ሀሳብ ይዞ ነው የተነሳው፡፡ የመርቅያን ክህደት
በዋናነት በእግዚአብሔር አምላክነት፣ በክርስቶስ የባህሪይ አምላነት ወይም ፈራጅነት አሊያም በጻድቃን መላእክት አማላጅት ላይ ያነጣጠረ
አልነበረም፡፡ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሊቃዉንት ምሁራን መርቅያንን ቤተ ክርስቲያኒቱን ከእንቅልፏ የቀሰቀሰበትን ሀሳብ ያነሳ
መናፍቅ ነው ይልቱል፡፡ መርቅያን የተነሳው ከወንጌላቱ መካከል ከፋፍሎ
ይህንን እቀበላሁ ይህንን አልቀበልም በማለት ነው፡፡ ከአራቱ ወንጌላት የማርቆስን፣ ከጳውሎስ መልእክታት ደግሞ አስሩን ብቻ ነው
የምቀበለው ከዚህ ውጪ ያሉትን ከጳውሎስ መልእክታት አራቱን እንዲሁም የይሑዳን፣ የጴጥሮስን፣ የዮሐንስን መልእክትና ራዕይን አልቀበልም
ብሎ ክህደቱን አወጀ፡፡ ብዙ ሊቃዉንት መርቅያን ይህንን ያለበትን ምክንያት በብዙ መንገድ ለማየት የሞከሩ ሲሆን ብዙዎች ግን መርቅያን
በትንሹም ቢሆን የዘረኝነት መንፈስ አለበት ብለው ያምናሉ የይሁዲነት መንፈስ ይታይበታል የመረጣቸው መጻህፍት ከይሁዲነት ጋር ዝምድና
ያላቸውን መጻህፍት ብቻ ነው መርጦ እቀበላሁ ያለው ብለው ያምናሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ቤተ ክርስቲያን የመርቅያንን ሀሳብ ለመቃወምና
ክህደቱን ለመቀልበስ ብዙ እርቀት እንድትጓዝ ተገዳለች፡፡ ቤተ ክርስያኒቱ የመርቅያንን ክህደት ለመጣል እና ወንጌሎቿ፣የቀሩት የጳውሎስ
መልእክታት እና እንዲሁም የዮሐንስ ራዕይም ሆነ የሀዋርያቱ መልእክታት በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት፣ ያለፈውን ዘመን እንዲያስታዉሱ፣
የነበሩበትን ዘመን እነዲያስተዉሉ፣ የሚመጣውንም ጊዜ እንዲያመለከቱ በማድረግ የተጻፉ እውነተኛ መጻህፍት መሆናቸውን ለማሳመን በተነሳች
ግዜ ያላሰበችው ፈተና ገጥሟታል፡፡ ፈተና የሆነውም የማቴዎስ ወንጌል፣ የማርቆስ ወንጌል ፣የሉቃስ ወንጌል የዮሐንስ ወንጌል እና
መልእክታም እንደዚሁ በስማቸው የተሰየሙ መጻህፍት በተመሳሳይ ስም ነገር ግን በሀሳብ እጅጉኑ ተራርቀው ብዙዎችም በምንፍቅና ሀሳብ
ተበርዘው በቁጥር በዝተው መገኘታቸው ነው፡፡ ይህም ማለት ማንም እየተነሳ የሚፈልገውን ጽፎ የማቴዎስ ወንጌል፣ የሉቃስ ወንጌል፣
የማርቆስ ወንጌል እያለ እየሰየመ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያስገባ ነበር፡፡ በዘመኑ መጻህፍቱ ሳይመረመሩ ፣ሳይጠኑ፣ ማን እንደጻፋቸው
ሳይረጋገጥ ፣መንፈሳቸው ይዘታቸው ሳይታይ እና ሳይመዘን የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስ ወይም የዮሐንስ ወንጌል ስለሚል ብቻ ቦታ
እየተሰጣቸው የተሰበሰቡ ሲሆን፤ መርቅያን ያነሳውን ሀሳብ እና ክህደት ለማረም በተደረገ ጥረት ትክክለኛ የሆኑትን ወንጌላት ልክ
ካልሆኑት ለመለየት ቤተ ክርስቲያን ከሶስት መቶ ሀምሳ እስከ አራት
መቶ ዓመታት እንደፈጀባት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይነግረናል፡፡ ይህም የሆነው በቀላሉ በማቴዎስ ወንጌል ስም ብቻ ይዘታቸው
የተለያየ በምንፍቅና ሀሳብ የተሞሉ እስከ አንድ መቶ ሀያ የሚጠጉ መጻህፍት መገኘታቸው ነው፡፡ ይህንን ትክክለኛ የሆነውን መጽሐፍ ለመለየት ምን ያክል ከባድ እንደሆነ ማንም
ሊረዳው ይችላል፡፡ ከዚህ በኋላም ነው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ቅዱስ ሲኖዶስ በየሶስት ወሩ እየተሰበሰበ በቤተ ክርስቲያኒቱ
ስም የሚወጡ መጻህፍትን እንዲመረምርና እንዲለይ በቀኖና የደነገጉት፡፡
ይሁን እና የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት የሊቃዉንት ጉባኤ ቅዱስ ሲኖዶሱንም ጨምሮ በንቃት ሊከታሉት ባለመቻላቸው መጻሕፍት፣
ዝማሬያትን እና የስብከት ይዘቶችን ለይተው መያዝ ባለመቻላቸው በዘመናችን ባህታዊ የሚመስሉ ሽፍቶች፣ ካህናት የሚመስሉ ተርታ ሰዎች፣
ሰባኪያን የሚመስሉ አጉራ ዘለሎች፣ መንፈሳዊ መጻህፍት የሚመስሉ ልብ ወለዶች፣ መዝሙር የሚመስሉ ዘፈኖች እና ክርስቲያን የሚመስሉ
አህዛቦች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ተከብረውና ቦታ አግኝተው ተሰግስገው
የሚገኙት፡፡ በእርግጥም መርቅያን በዛን ዘመን አንቀላፍታ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ከእንቅልፏ እንድትነቃ ቀስቅሷላታል ማለት
ይቻላል፡፡ ምናልባት ዛሬም ቤተ ክርስቲያኒቱ በየትኛውም ሁኔታ ላይ በመልካም አስተዳደር፣ በፋይናስ ስርዓት፣ በእስታቲክስ፣ በሰው ሀይል አስተዳደር፣ በህትመትና ስርጭት ብቻ በሁሉም ዘንድ ከተኛችበት
ልትነቃ የሚገባበት ዘመን ይመስለኛል፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያኒቱ
ውስጥ ያለው ሁኔታ የቤተ ክርስቲያኒቱ እውነተኛ መምህራንን፣ ሊቃውንትን፣ ካህናትን፣ ሰባክያነ ወንጌልን፣ መዘምራንን፣ አስተዳደርን
ለይቶ ለማወቅ አስቸጋሪና ድብልቅልቅ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
ለጊዜው
ግን ጎልቶ የወጣውና ምእመናኑንም ሆነ የሚመለከታቸውን የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ፈተና ውስጥ የጨመረው የተሀድሶ ነን ባዮች ጉዳይ
ነው፡፡ በዚህ ውጥንቅጡ በበዛበት ዘመን ማንን ከማን መለየት እስኪያቅት ድረስ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በዚህ ግርግር ወቅት ራሳቸውን
ለመግለጥም ሆነ ለማኖር የተመቸ ግዜ ያገኙ አካትም ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ አንዳንዶቹ በዚያኛው ወገን ያለውን ሁኔታ ሲያመቻቹ፣
ሲያደራጁ እና ሲመሩ ቆይተው በየትኛው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንደተመለሱ
ሳይታወቅ አሁን ደሞ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ተቆርቋሪ አካላት መካከል በመገኘት ሲተቹ፣ ሳሳደቡ፣ ሲዝቱ ሲያሳድሙ እና ሊያስወግዙ ሲሯሯጡ
እንመለከታቸዋለን፡፡ አንዳንዶችም በወዲያኛው ወገን አሉ ከሚባሉት በአቋም ከመለየት ወዲህ ማዶ ካሉት ጋር በጥቅም ሲጣሉ ሀይማታዊ
ጉዳይ በማልበስ እሰራልሃለሁ ያሉትን ሀሳብ ይዘው መጥተው አላማቸውን ለማሳካት ሲታገሉ ይታያሉ፡፡ የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ
አካላትም ጉዳዩን መንፈሳዊ በሆነ ምልኩ ከመመርመር ይልቅ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል ስንኩል ተረት አብረው ሲዘምቱ ማየት እንግዳ
መሆኑ ቀርቷል፡፡
መምህራነ
ወንጌልም እንዲህ ያለውን ሀይማታዊ ልዩነት መሰረታዊ በሆነ ትምህርት እየለዩ ከማስተማር ይልቅ መድረክ በደመቀበት እና ሞንታርቦ
በጮኸበት እና ነጣ ነጣ ያለ ልብስ የለበሱ ምዕመናን ባሉበት ብቻ በመገኘት ለየት ያሉና የሚያስደምሙ ጥቅሶችን በመምረጥ ምዕመኑን
በማስደመም ብቻ ይበትኑታል፡፡ ስለዚህ ከእንደዚህ ካሉ ቦታዎች እና መድረኮች ምንም ሳይወለድ ይቀራል፡፡ ከስብከት የሚወለድ መናኝ
የለም ካለም ክዶ ይሞታል፡፡ ከስብከት የሚወለድ አገልጋይ የለም ካለም ራሱን የሚያገለግል ነው፡፡ ከስብከት የሚወለድ ካህን የለም
ካለም የአገልግሎት ሳይሆን የክብር ክህነት ያለው ቀረርቶን ከዜማ የማይለይ ነው፡፡ ከስብከት የሚወለድ ዘማሪ አይኖርም ቢኖርም በዘፈን
ይደመድመዋል ፡፡
በቤተ
ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተጨበጠ ለውጥ ማምጣት ካስፈለገ ደጉን ከክፉው፣ መልካሙን ከመጥፎው፣ ሰባኪውን ከፎካሪው፣ ዘማሪውን ከዘፋኙ
እና ቀዳሹን ከአንጎራጓሪው በአጠቃላይ ተኩላውን ከበጉ ስንዴውን ከእንክርዳዱ መለየት ካስፈለገ አሁን በየአውደ ምህረቱ ያለው የስብከተ
ወንጌል እንቅስቃሴ እንዳለ ሆኖ መሰረታዊ ወደ ሆነ ስር የሰደደ ተካታታይ በቤተክርስቲያኗ ዶግማ እና ቀኖና ላይ እንዲሁም ስርዓተ
ቤተክርስቲያን ላይ ወዳተኮረ ትምህርት መመለስ ያስፈልጋል፡፡መምህራኖቻችንንም አፍ ከሚያስከፍተው የአውደ ምህረታችን ስብከት ባሻገር
በየ ሰንበት ትምህርት ቤቱ በተለዩና ቤተ ክርስቲያኒቱ በምታዘጋጃቸው ልዩ እና ተከታታይነት ባላቸው ጉባኤያት ላይ ልናያቸው ግድ
ይላል፡፡
ያልተጨበጠ
ዶግማ፣ የማይታይ እውነት እና የማይደረስበት ተስፋ የያዙ ቡድኖች እና ግለሰቦች እንኳን ተከታታይነት ባለው መሰረታዊ አስተምህሮታቸው
አድናቂዎቻቸውን እና ተከታዮቻቸው እምነት አስታጥቀው የእውነት ጠብታ ለማይገኝበት ነገር ግን ላመኑበት አላማ ነብሳቸውን እንኳን
እስከመስጠት ቆራጥ ሲሆኑ እናያለን፡፡ እነዚህ አላማን መሰረት ባደረገ እና ተከታታይነት ካለው መሰረታዊ አስተምህሮቶች የሚወለዱ
እና የሚገኙ ፍሬዎች ናቸው፡፡
በተለያየ
መልክ የተደራጁ የማህበራት አባላት እንኳን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጥቅምና ክብር ይልቅ ለማህበራቸው ጥቅምና ክብር በጽናት ሲቆሙ የምናያቸው
ተከታታይነት ካለው አስተምህሮት ስለሚወለዱ ነው፡፡
በቤተ
ክርስቲያኒቱ ውስጥ ግን እንደዚህ ያለውን እውነት ማየት እየጠፋ ያለ ቅርስ እየሆነ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሆዳቸው አምላካቸው
የሆኑ ቅጥረኞች እንጂ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች እየበዙ ያሉት እንዲህ ያለ መሰረታዊና አግባብነት ያለው የትምህርት ወንፊት በመጥፋቱ
ነው፡፡
ዛሬ
ዛሬ ስማቸውን የገነቡ ሰባክያነ ወንጌል ለአገልግሎት በሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ ውስጥ እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትም
በሰርክ ጉባኤ የማይገኙበት ግዜ ነው፡፡ መምህራን በአውደ ምህረት ትምህርተ ወንጌል ሲሰጡ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በአዳራሻቸው
ጸሎት ያደርሳሉ ወይም መዝሙር ያጠናሉ፡፡ አንዳንድ ማህበራትም አባሎቻቸውን በራሳቸው መምህራን ካልሆነ በስተቀር ቤተ ክርስቲያን
አምናበት ባሰማራቻቸው መምህራን ያለማሰበክ ጥብቅ ጥበቃ የሚደርጉበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ምዕመናን መንፈሳዊ አባቶቻቸውን በግልጥ
የማያምኑበት የሚያሙበት የቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ ምንፈሳዊ አባቶችም በልጆቻቸው የሚጨክኑበት ዘመን ሆኗል፡፡
ማህሌታዉያኑ
ከቀዳስያኑ፣ ቀዳስያኑ ከመምራኑ፣ መምህራኑ ከሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ጋር የሰንበት ትምህርት ቤት አባላቱ በተለያየ መልክ
ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊረዱ ምን እናድርግ ብለው ከተደራጁ ማህበራት ጋር በአንድነት ለአንድ አላማ በፍቅር መስማማት እስካልቻልን ድረስ
“የመቀናጆ በሬ ወደየ ሀገሩ ይስባል” እንደሚባለው ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደየ ፍላጎታችን በተለያየ አቅጣጫ እንደብራና ወጥረን እንደምናስጨንቃት
ምንም ጥርጥር የለውም
ጌታ
በደሙ የመሰረታት ቤተ ክርስቲያን አለች በስሙ፣ የተጠመቁ እና የተመዘገቡ ምዕመናንም አሉ ክርስትናው ግን የታለ ያስብላል፡፡
ቤተ
ክርስቲያኒቱ በቁጥር ከሚያታክቱ የውጭ አካላት የሚዘንብባት የመከራ ቀስት አልበቃ ብሎ ለአገልግሎት የተጠሩበትን መንፈሳዊ ስራቸውን
ትተው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት እርስ በስርስ የሚፋለሙበት፣ የሚቋሰሉበት እና የሚጨካከኑባት መድረክ ሆናለች፡፡
በቤተ
ክርስቲያኒቱ የተበላሸ የውስጥ አስተዳደርን ለማቃናት ደፋ ቀና የሚሉትን መጥፎ ስም በመለጠፍ ማሸማቀቅ፣ ሊስተካከል ሊፈተሸ የሚገባውን
ጠማማ መንገድ ለማስተካከል ከመጣር ይልቅ ልዩነቱን ሀይማኖታዊ በማስመሰል ድጋፍ ለማግኘት መጣር የጊዜአችን አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡
ምናልባትም
በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሊስተካከል የሚገባው የተበላሸ አስተዳደር፣ ጽንፈኝነት እና ጉቦኝነት እንዳይታረምና እንዳይስተካከል ይህ
አስተሳሰብ የተሀድሶ መንፈስ ነው የሚለው ጥቁር መጋረጃ ጋርዶ የያዘው ይመስለኛል፡፡ የተሀድሶ መንፈስን እና መልካም አስተዳደርን
ለይቶ የሚያይ አይን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ከመናፍቃን ክህደት እና ከተሃድሶ መንፈስ ይልቅ ቤተ ክርሰቲያኒቱን የዘረኝነት መንፈስ
የመልካም አስተዳደር እጦት ጉቦኝነት አብልጦ ይጎዳት እንደሆነ ማን ያውቃል?
ይህ
ዘመን ለመልካም አስተዳደር ለተኛችው በጥቅም ፈላጊዎች፣ በጉበኞች፣ በዘረኞች፣ በአማኞች ሳይሆን በቅጥረኞች ለተሞላችው የዛሬዋ ቤተ
ክርስቲያን እንደ መርቅያን ዘመን ከእንቅልፏ የምትነቃበት ጊዜ አሁን ይመስለኛል፡፡
ጠላትን
ለይቶ ማሳየት ተገቢ ነው፡፡ ዘመቻውም ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን በዘመቻው የሚሳተፉ ሰዎችን መለየት ያስፈልጋል፡፡ ጠላትን ለይቶ ማወቁ ብቻውንም በቂ አይደለም፡፡መለየት ያስፈልጋል መለየት
ሲባል ሊለይበት በሚገባው መንፈሳዊ አስተዳደር ወይም ሊለይ በሚችለው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል በአዋጅ መለየት ያስፈልጋል፡፡
ቤተ
ክርስቲያኒቱ ከጥቂት ሰዎች ይሁንታዊ አስተዳደር ወጥታ በተጨበጠ እና መሬት ላይ ባረፈ ህግ መገዛት አለባት ወይም በመተዳደሪያ ደንቧ
ላይ የሰፈረውን ህግ ልትተገብረውና ህጋዊ መሰረት ልታስይዘው የመምትችልበት ማንነት ያስፈልጋታል፡፡
በዘመነ መርቅያን ቤተ ክርስቲያኒቱ ደገኛውን እና ክህደት የተሞባቸውን በጻህፍት
በመለየት መጻህፍቶቼ እንዚህ ናቸው እንዚህ በስም እንጂ የእኔ አይደሉም ብላ እንደለየች የዛሬይቱም ቤተ ክርስቲያን ልጆቼ፣ ካህናቱ፣
ሊቃዉንቱ፣ መዘምራኑ፣ ሰባኪያነ ወንጌል፣ ባህታዉያኑ፣ ማህበራቱ፣ምዕመናኑ እንዚህ ናቸው፡፡
እነዚህ ግን በስም እንጂ በግብር ልጆቼ አይደሉም ብላ መለየት እና ማሳወቅ ያለባት ዘመን አሁን ነውና ቤተ ክርስቲያኒቱ ልትነቃ ያስፈልጋል፡
እነዚህ ግን በስም እንጂ በግብር ልጆቼ አይደሉም ብላ መለየት እና ማሳወቅ ያለባት ዘመን አሁን ነውና ቤተ ክርስቲያኒቱ ልትነቃ ያስፈልጋል፡
አለበለዚያ
ግን ያልተለየ ጠላት መብት ያለው በጥባጭ ነውና በአንዳንድ ቦታዎች እንደምነሰማውና እንደምናየው ሁለት መልክ ባላቸው ምዕመናን ቅዳሴያችን በነውጥ እና ድብድብ
ከመቋረጡ በፊት ልንነቃ ያስፈልጋል፡፡
የካቲት
10 ቀን 2008 ዓ.ም
መ.ር
ሰለሞን ፋንቱ