Monday, August 18, 2014

እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ ሉቃ 1 ፣ 19



   
እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ
ሉቃ 1 ፣ 19
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ተልኮ ኢየሱስ ክርስስን እንደምትወልድ ከማብሰሩ ከስድስት ወር በፊት ዮሐንስን እንደሚወል ሊያበስረው ወደ ዘካርያስ መጥቶ ነበር በመሰዊያው ፊት ተገልጦ ዮሐንስን እንደሚወልድ እና እሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንደሚያሰናዳ የነቢዩ የኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ እንደሚሔድ ሲያበስረው ዘካርያስ ግን እኔ ሸምግያለሁ ሚስቴም አርጅታለች ይህ ሊሆን እንደሚችል በምን አውቃለሁ? እያለ ለማመን በዘገየ ጊዜ መልአኩም መልሶ እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ እንድነግርህም ይህችን የምስራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር አለው፡፡
 መልአኩ እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ ሲል ምን ማለቱ ነው?
በእግዚአብሔር ፊት መቆም ማለት ምን ማለት ነው?
ለመሆኑ እግዚአብሔር በፊቱ ይቆሙ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊቱ ወዴት ነው?
መላእክትስ እንደሰው ይቆሙ ይቀመጡ ዘንድ የሚታይ የሚዘረጋና የሚታጠፍ አካል አላቸው?
እነዚህን ጥያቄዎች በትንሹ መመለስ ከቻልን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ ሲል ምን ማለቱ ነው; የሚረዳን ይመስለኛል
በመጽሐፍ ቅዱስ ፊት ማየት፣ በፊት መሄድ፣ በፊት መቆም የሚሉት ቃላት እጅግ በጣም ብዙ ትርጉሞችን ይዘው እናገኛቸዋለን
፡-ለመሆኑ እግዚአብሔር በፊቱ ይቆሙ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊቱ ወዴት ነው
እግዚአብሔር አብ  ንጽህናሽን ባበ ጊዜ ስሙ ገብርኤል የሚባል ብርሃናዊ መልአኩን ወደ አንቺ ላከ መልአኩም መንፈስ ቅዱስ  በላይሽ ይመጣል የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል አለሽ፡፡
ሉቃስ 1፤35
ይህንን ቃል በሀይማኖት የከበረ ቅዱስ አባ ህርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ላይ  መለኮት እያለ ይህንን መለኮት ስጋ እንዴት ቻለው እያለ በማድነቅ እንዲህ ይላል፡፡
ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ ሳይወሰን ጸነስሽው በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር በማህጸንሽ ተወሰነ፡፡
መመጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መለኮት በሆድሽ አደረ ፡፡
በምድራዊ እሳት እንመስለው ዘንድ አይገባም ለእሳትስ መጠን አለው ልክም አለው መለኮት ግን ይህንን ያህላል ይህንንም ይመስላል ሊባል አይቻልም፡፡
ለመለኮት እንደ ፀሐይና እንደ ጨረቃ ክበብ እንደ ሰውም መጠን ያለው አይደለም ፤ ድንቅ ነው እንጂ የሰው ህሊና የመላእክትም አእምሮ በማይደርስበት በአርያም የሚኖር ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት ወርድና ቁመት ላይና ታች ቀኝና ግራ ያለው አይደለም በሁሉ የመላ ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት  የሚዘረጋበትና የሚሰበሰብበት ያለው አይደለም ግዛቱ ባገሩ ሁሉ ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት  በላይ ጠፈር በታችም መሰረት ያለው አይደለም ጠፈሩ እርሱ መሰረቱ እርሱ ነው እንጂ ፡፡
ለመለኮት  ከምድር ከውስጥዋ የሆነውን ያነሳ ዘንድ ማጎንበስ ራስንም ዝቅ ማድረግ ያለበት አይደለም ለጴጥሮስ እንዳሳየው ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት  በሚታይ ገንዘብ በሚወሰንም ገንዘብ ደረትና ፊት የኋላም ጀርባ ያለው አይደለም በነደ እሳት የተሸፈነ ነው እንጂ ፡፡ ነደ እሳት ግን እርሱ ነው ፡፡ መለኮትስ ንጹሕና ጽሩይ ብሩህም ነው፡፡

ስለዚህ እግዚአብሔር በፊቱ ይቆሙ ዘንድ ፊቱ ወደ እዚህ ነው የሚባል አይደለም


በፊት መሄድ በመጽሕፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ቃል መንገድ መጥረግ ማደላደል መንገድ ማቅናት የሚሉትን ሀሳቦች ሲያሟላ እናገኘዋለን፡፡
ዮሐ 10፣4 እውነት እውነት እላችኋለሁ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚመጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፡፡ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው፡፡ ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል በጎቹም ድምጹን ይሰሙታል የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወሰወዳቸዋል፡፡
የራሱንም ሁሉ ጠርቶ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሔዳል በጎቹም ድምጹን ያውቃሉና ይከተሉታል፡፡ ይልና ሐዋርያት ስለምን እንደተናገረ ባልገባቸው ጊዜ እውነት እውነት እላችኋለሁ እኔ የበጎች በር ነኝ፡፡ አላቸው ስለዚህ እውነተኛው እረኛችን ክርስቶስ በፊታችን አንደሚሄድ ሲነግረን ሞትን በመስቀሉ ጠርቆ ከመንገድ ሊያስወግደው ሞታችንን ሞቶ ነጻ ሊያወጣን ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን ሊጠራን ነው፡፡ በፊታችን መሄዱ፡፡
፡-ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሕዝበ እስራኤል ይዞ ከግብጽ ወደ ተስፋይቱ ምድረ ከነዓን  ሲጓዜ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎት ነበር፡፡
በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያስገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአኬን በፊትህ እሰዳለሁ በፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ሰለሆነ ኃጢአት ብትሰሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ ጠላቶችህን እጣላቸዋለሁ የሚያስጨንቁህንም አስጨንቃቸዋለሁ፡፡ ዘፀ 23፣20
ይለል በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሀሳብ መልአኬን በፊትህ እሰዳሁ ማለቱ መንገድህን ያስተካላል ጥረጊያውንም ያቀናል ወዳዘጋጀሁልህ ስፍራም በሰላም ያደርስሃል ማለቱ ነው፡፡
ፊት ማየት የሚለውን ብንመለከትም በቀጥታ መለመን ማለት እንደሆነ እንረዳለን በተለምዶ ወላጆች ልጆቻቸውን በችግር ሲያሳድጉ፡፡ ይህንንም ሲገልጹ የስንት ሰው ፊት አይቼ ነው ያሳደኩህ፣ ፊት ማየት ይከብዳል፣ የሰው ፊት እሳት ነው፣ የሰው ፊት ማየት አልፈልግም ሲሉ እናደምጣቸዋለን እነዚህ ሁሉ ቃላት የሚነግሩን አንድ ነገር ነው፡፡ የሰው ፊት አይቼ ለምኜ የሰው ፊት ማየት አልፈልግም መለመን አልፈልግም የሰው ፊት አሳት ነው ተቸግሮ መለመን ይከብዳል ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
ይህንን እውነታ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ማዛመድ ቢያስፈልግ  ኢዮብ 42፤9 እግዚአብሔርም የኢዮብን ፊት ተቀበለ ይለናል፡፡ ታሪኩ ከቁጥር 7 ጀምሮ የሚመጣ ሲሆን እግዚአብሔር ቴማናዊዉን ኤልፉዝን እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቁጣዬ በአንተና በሁለት ባልጀሮችህ ላይ ነድዶአል፡፡ ስለዚህም ወደ ባሪያ ወደ ኢዮብ ሔዳችሁ እንዲህና እነዲህ አድርጉ ኢዮብም ስለ እናንተ ይጸልያል እኔም እንደስንፍናችሁ እንዳለደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ፡፡ ካለ በኋላ ነው እንግዲህ እግዚአብሔርም የኢዮብን ፊት ተቀበለ የሚለው ይህም እግዚአብሔርም የኢዮብን ልመና፣ፀሎት  ተቀበለ ከማለት ውጪ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡
ማቴ 18፣ 10 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሲያስተምር እንዲህ አለ፡፡ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና፡፡ ከላይ በኢዮብ መጽሐፍ ላይ እነዳየነው ፊት ማየት መለመን ማለት ነውና ኢየሱስ ክርስቶስም ከታናናሾቹ ማንንም አትናቁ ተጠንቀቁ መላእቶቻቸው ዘወትር አባቴን ይለምኑላቸዋልና ያማልዷቸዋልና ሲል ያስጠነቅቃል፡፡
በፊት መቆም  በፊት መቆም የሚለው ቃል ወይም በእግዚአብሔር ፊት መቆም የሚለው፡፡ መለመን፣ ማስታረቅ፣ ማማለድ የሚለውን እውነት እንደሚናገር የሚከተሉትን ጥቅሶች ማየት ይቸላል
መዝ 105 ፣23 ታላቅ ነገርንም በግብጽ ድንቅንም በካራን ምድር ግሩም ነገርንም በኤርትራ ባህር ያደረገውን ያዳናቸውንም እግዚአብሔር ረሱ፡፡
እንዳያጠፋቸው ቁጣውንም ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅስፍቱ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ባይቆም ኖር እስራኤል በቅስበት በጠፉ ነበር፡፡
ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ቆመ የተባለለት ሙሴ ቃልኪዳኑን ቦት ተቀብሎ በሚመለስበት አርባ ቀን ከእግዚአብሔር ጋር በነበረው ቆይታ ህዝቡ አሮንን አስገድደው የጥጃ ምስል ሰርተው ሲያመልኩ በመቆየታቸው የእግዚአብሔር ቁጣ በላያቸው  ነደደ ብዞወችም ሞቱ በመጨረሻም ሊቀ ነቢያት ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ወጣ እንዲህመ አለ እኒህ ህዝብ ታላቅ ሀጢአትን ሰርተዋል ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፡፡ አሁን ይህን ሃጢአታቸውን ይቅር በላቸው ያለዚያ ግን እኔን ከህይወት መጽሐፍ ሰርዘኝ ፡፡ በማለቱ ነው፡፡
በመጽሐፈ ሳሙኤል 1፣1-10 የነቢዩ የሳሙኤል እናት ሃና ልጅ ባለመውለዷ የተነሳ ጣውንቷ ታበሳጫት እንደነበረ በዚህም የተነሳ ለመስዋት ከሚቀርበው አትበላም አትጠጣም ነበር ይልና ቁጥር 9 ጀምሮ እንዲህ ይላል፡፡ በሴሎ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሳች፡፡ ካህኑም ኤሊ በእግዚአብሔር መቅደስ መቃን አጠገብ በመንሩ ላይ ተቀምጦ ነበር፡፡ እርስዋም በልባ ትመረር ነበር በእግዚአብሔር ፊት ቆመች ጽኑ ልቅሶም አለቀሰች፡፡ ይለናል ሐና በእግዚአብሔር ፊት ቆመች ሲል በእግዚአብሔር ፊት ጸለየች ማለቱ ነው፡፡  

በትንቢተ ዳንኤል 12፣1 ላይ በዚያም ዘመን ስለ ህዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል  
የህዝቡ ሃጢአት እጅግ ሲበዛ ደሞ ሙሴና ኤልያስ በፊቴ ቢቆሙም እንኳን ልቤ ወደ እዚህ ህዝብ አያዘነብልም፡፡ ይላል ኤር 15፣1 ሙሴና ኤልያስ ስለዚህ ህዝብ ቢጸልዩ ጸሎታቸውን አልሰማም ማለት ነው፡፡
በመጽሐፈ ኢዮብ 1፣6 ከእለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ ሰይጣንም ደሞ በመካከላቸው መጣ፡፡ ይላል ሰይጣን የመጣው ምዕራፉን ስንጨርስ እንደምናገኘው ለመክሰስ የመጣ በመሆኑ ቆመ አልተባለም መላእክት ግን በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ ሲል ለመለመን ለምልጃ በመሆኑ ቆሙ ይላቸዋል፡፡

ስለዚህ ከላይ ያየናቸው መረጃዎች እንሚያስረዱን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፡፡ ሲል በቀጥታ እኔ ስለሰዎች እግዚአብሔርን የምለምን ነኝ ማለቱ ነው፡፡ ምክንያቱም መላእክት ቆሙ ሲባል እንደ ሰው የሚታጠፍና የሚዘረጋ የሚቆምና የሚቀመጥ አካል የላቸውምና ነው
ስለ መላእክቱም፡፡ መላእክቱን መናፍስት አገልገዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ፡፡ ዕብ 1፣7 በማለት ስለመላእክት ተፈጥሮ ይናገራል፡፡

መላእክት እንዴት ነው የሚማልዱት?  የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ፡፡ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ እነዚህ ሰባ አመት የተቆጣኻቸውን የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከመቼ ድረስ ነው፡፡ ብለው ነው ዘካ  1፣12
በተጨማሪም በአዲስ ኪዳን ስለ መላእክት ምልጃ ሲናገር ከቶ ለማን ብሎአል ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ መናፍስት አይደሉምን ዕብ 1፣14
ከዚህ በተጨማሪ ሁለት የአዲስ ኪዳን መጽሕፍት በማየት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለማላእክት አማላጅነት አንዴት እነዳስተማረ መረዳት ይቻላል

ማቴ 13፣24-28
ቁጥር 24 ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ መንግስተ ሰማያት በእርሻዉ መካክል ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች፡፡ ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላት መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ፡፡ ስንዴውም በበቀለና ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደሞ ያን ግዜ ታየ፡፡
የባለቤቶቹም ባሮች ቀርበው፡፡ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን እንክርዳዱንስ ከመዴት ተገኘ? አሉት፡፡
እርሱም ጠላት ይህንን አደረገ አላቸው፡፡ ባሮቹም እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን አሉት እርሱም ተውአቸው እንክርዳዱን ስትነቅሉ መልካሙን ስንዴ ትነቅላላችሁ እስከ መከር ይቆዩ አላቸው፡፡
ይህንን ምሳሌ በዚሁ ምዕራፍ 38 ላይ ሲያብራራላቸው ወይም ምሳሌውን ሲተረጉምላቸው
ቁጥር 36 የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጉምልን አሉት፡፡ እርሱም መልሶ አንዲህ አላቸው
፡-መልካን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፡፡ እርሻውም ዓለም ነው፡፡
፡-መልካሙ ዘር የመንግስት ልጆች ናቸው
፡-እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው
፡-የዘራዉም ጠላት ዲያቢሎስ ነው፡፡
፡-መከሩም የአለም መጨረሻ ነው፡፡
፡-አጫጆችም መላእክት ናቸው፡፡
እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚጣል በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፡፡
ቁጥር 40
ይህንን ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸውን ምሳሌ እንደያዝን ወደ ሉቃስ 13፣6 ስንሻገር ሌላ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸውን ምሳሌ እናገኛለን
ይህንንም ምሳሌ አለ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፡፡ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም፡፡
የወይን አትክልት ሰራተኛውንም እነሆ ከዚች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም ቁረጣት ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጎሳቁላለች አለው፡፡
እርሱ ግን መልሶ፡፡ ጌታ ሆይ ዙሪያዋን እስክኮተኩትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት ወደ ፊትም ብታፈራ ደህና ነው ያለዚያ ግን ትቆርጣታለህ አለው፡፡ የሚል ትምህርት እናገኛለን፡፡
ይህንን የሉቃስ ወንጌል ምሳሌ በማቴዎስ ላይ ካው ምሳሌ ጋር ስናስተያየው እንዲህ እናገኘዋለን
፡-ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት በለስ ነበረችው
፡-የወይኑ ባለቤት የሰው ልጅ/ኢየሱስ ክርስቶስ/
፡-ወይኑ የሰው ልጆች
፡-የወይን አትክልት ሰራተኛው መላዕክት
፡- የተፈለገ ፍሬ መልካም ስራ
፡- ካላፈራች እንድትቆረጥ ማለት መልካም ምግባር ሐይማኖት አልተገኘባትምና እንድትሞት የተላለፈ ፍርድ ነው
ይህችን በለስ እንዳትቆረጥ ያደረጋት የወይን ተንከባካቢው እንደሆነ ሁሉ ምግባር ከሀይማኖት ሓይማኖት ከምግባር ሳይገኝብን ቀርቶ ሞት ሲታዘዝብን ሞት ሲቆረጥብን በወይን ተንከባካቢው የተመሰሉት መላእክት በጸሎትና በምልጃ ለዚህ ዓመት ተዋቸው እያለ በምልጃ ዘመናችንን እንደሚያረዝምልን ሞትን እንደሚያሻግሩን ያስተምረናል፡፡
ከዘህ የተነሳ ነው በመላእክት አማላጅነት የምናምነው
በዓለማችን መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት አድርገው ኢየሱስ ክርስቶስን እንሰብካለን የሚሉ  በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ቤተ እምነቶች ቢኖሩም መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት በማድረግ የመላእክትን አማላጅነት የምታምን ቤተ ክርስቲያን ብትኖር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አንብባችሁ ለሌሎች ይጠቅማል ብላችሁ ካመናችሁ ሼር በማድረግ ለኁሉም አድርሱ መምህራነ ወንጌል ወንድሞቼ እና አባቶቼ ከዚህ በላይ አምልታችሁ አስፋፍታችሁ ብትጽፉት እጅግ ደስ ይለኛል ላነበባችሁልኝና አስተያይት ለምትሰጡኝ ሁሉ የከበረ ምስጋናዬን ከወዲሁ አደርሳለሁ
  

Sunday, August 17, 2014

እግዚአብሔር ሁሉም ቦታ ስለማይገኝ እናቶችን ፈጠረ



ይህንን ያለው ጸሐፊ በእርግጥ እግዚአብሔር ሁሉም ቦታ የማይገኝ ወይም የማይኖርበት ቦታ ተገኝቶ አይደለም፡፡ ለህጻናት ግን የመጀመሪያ እግዚአብሔሮቻቸው እናቶቻቸው ስለሆኑ ነው፡፡ ይህም እውነት ነው፡፡ ይህንን ዓለም ከመቀላቀላችን በፊት ማህጸናቸውን ዓለም አድርገው ያቆዩናል የእግዚአብሔርን መግቦት እስክንረዳ ድረስ ጡታቸውን እያጠቡ ያሳድጉናል እግዚአብሔርን ማወቅ እስክንችል መጀመሪያ እናቶቻችንን ብቻ እናውቃለን የእግዚአብሔርን እቅፍ እስክናውቅ በእቅፋቸው ያቆዩናል የእግዚአብሔርን ክንድ እስክንረዳ በክንዳቸው እንደገፋን ሁሉን ስናውቅ ለእግዚአብሔር ይሰጡንና ያልፋሉ፡፡ ስለዚህም ይመስለኛል እናቶች ለልጆቻቸው የመጀመሪያ እግዚአብሔር ናቸው የሚባለው፡፡
ስለ መንፈሳዊው ዓለም መንፈሳዊው ጸጋ ስለ ነገረ እግዚአብሔር ነገረ ድህነት ምስጢረ ስጋዌ በአጠቃላይ ስለ የምስራቹ ቃል ስለወንጌል ለመስበክ መጠራት፣ መመረጥ፣ በጸጋ መቀባት፣ በአባቶች እግር ቁጭ ብሎ መማር ይፈልግ ይሆናል፡፡ ስለ እናት ለመስበክ ግን ተወልዶ ማደግ በእናት እቅፍ መሞቅ የእናትን ጡት ጠብቶ ማደግ ወይም ይህንን ማጣት ብቻ በቂ ነው ሰው ስላገኘውም ይሁን ስላጣው ነገር በደንብ መናገር ይችላልና፡፡ ስላገኘው ነገር በኩራት ስላጣው ነገር በቁጭት፡፡
ብዙ ግዜ አባቶች የተረሱ እንኪመስል ድረስ እናት ለልጅ ያላትን ፍቅር ሲተረክ እንሰማለን አባቶችም ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር በኩራት ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡
ይሁን እንጂ በልጅና በወላጅ መካከል ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ለመግለጽ እናት ለልጇ ወይም አባት ስለልጁ ከመናገር ይልቅ ልጅ በወላጁ ያለውን ጥብቅ ፍቅር ማየት ቀላል ይመስለኛል ምክንያቱም
እናት ለልጅ ያላትን ፍቅር መተረክ ቀላል ቢሆንም ሁላችንም ግን እኩል አንረዳዋለን ብዬ አላምንም፡፡ በምድር ላይ ብዙ እናች ቢኖሩም ሁላችንም ግን እናቶች አይደለንም አባት ለልጅ ያለውን ፍቅር ማውራት ቢቻልም ሁሉም ሰው እኩል ስሜቱ እንዲገባው አይጠበቅም በምድር ላይ ብዙ መልካም አባቶች ቢኖሩም ሁሉም አባቶች አይደሉምና፡፡
ነገር ግን ልጅ በእናቱ ያለውን ጥልቅ ፍቅርና ቁርኝት ብንናገር ሁላችንም እኩል የሚገባን የምንረዳው ይመስለኝል ምክንያቱም ሁላችንም በአንድ ወቅት ለእናቶቻችን ልጆች ነበርንና፡፡
እናት የሁሉ ነገር መሰረት ናት  እናታችን በህይወት ትኑርም በሞት ትወሰድም፣ ትክሳም ትወፍርም፣ ይመቻት ትጣም፣ ትጥቆርም ትቅላም እናትን ማወቅ ለጥሩ ህይወት ስብእና መሰረት ናት እናቱን የማያውቅ አባቱን አያውቅምና አባትን ለማወቅ እናት መሰረት ናት ወንድምን አክስትን አጎትን በአጠቃላይ ማህበረሰቡን ለማወቅ እናትን ማወቅ ይቀድማል ፡፡
ሰው እናቱን የማያቅ ከሆነ ጥሩ ዜጋ አይሆንም፡፡ ሰው በየትኛውም ድሎት ውስጥ ቢቀመጥ በጥሩ ቪላ ቢኖር በተሸሞነሞነ አልጋ ቢተኛ ጮማ ቢቆርጥ እናቱን የማያውቅ ከሆነ እናቴ ማን ናት? የሚል ጥያቄ ሰላሙን ሲነሳው ምቾቱን ሲያስረሳው ይኖራል፡፡
ያለ እናት በጥሩ ቪላ ከመኖር በደሳሳ ጎጆ ውስጥ መኖር እንደሚሞቅ ያለ እናት በትሽሞነሞነ አልጋ ከመተኛት ከእናት ጋር በመደብ ላይ ማደር እንደሚመች ያለ እናት ጮማ ከመቁረጥ ከእናት ጋር ቆሎ መቆርጠም እንደሚያጠግብ ያለፉበት ምስክር ይሆናሉ፡፡
እናቱን የማያውቅ ቢበላ የሚጠጋው ቢለብስ የሚያምርበት ቢናገር የሚያሳምን ቢሮጥ የሚቀድም ቢታገል የሚጥል አይመስለኝም፡፡
እናት ልጇን ወደዚህ ምድር ስታመጣ በዓለም ላይ የመጨረሻውን መስዋእትነት ከፍላ ነው ህይወትን በህይወት አሲዛ፡፡ ብዙ እናቶች ልጆቻቸውን ለማስገኘት ህይወታቸውን ያስይዛሉ፣ይሰጣሉ በከባድ መከራ በምጥ ይወልዳሉ፡፡
ስለምጥ ስንናገር  ከላይ ለመጥቀስ እደሞከርኩት በዚህ ልዩ ጸጋ ውስጥ ያላለፍን እህቶችም ብንሆን ወንድሞች አባቶችም ስለምጥ ከባድነት አንረዳም ስለምጥ ከባድነት መዘርዘርም ማስረዳትም ቢሆን በዚህ ጸጋ ውስጥ ባለፉ እናቶች ብቻ ያምራልና ልለፈው፡፡
መጽሐፍ ግን የምጥን ከባድነት ሲዘረዝር  
የዚያን ግዜ መንግስት በምንግስት ላየ ይነሳል እናት የልጇን ጩኸት አትሰማም ፍቅር በምድር ላይ ትቀዘቅዛለች ጦርን እና የጦርነት ወሬን ትሰማላችሁ ይህ ሁሉ የምጥ መጀመሪያው ነው
ይላል እንግዲህ ለሚያስብ ሁሉ ይህን መረዳት ቀላል ነው ይህ ሁሉ ከላይ የሰማንው የምጥ መጀመሪያ ከሆን የምጥ መካለኛው የምጥ መጨረሻይ ምን ይሆን?
እንግዲህ እናት እኛን ወደዚህ ምድር ለማምጣት የምትከፍለው ትልቁ ዋጋ  ነው ምጥ፡፡
ብዙ እናቶችም ከዚህ የተነሳ ህይወታቸውን ያጣሉ በምድራችን ላይ ሕይወት ለማምጣት ሕይወት የሚሰጡ እናቶች ብቻ ናቸው፡፡ ክብር ይገባቸዋል፡፡
እናቶቻችን በማህራዊ ኑሮ ከሌላው ሰው ጋር መግባባት ቢያቅታቸው እጅግም ክፉ ናቸው የሚባሉ ቢሆኑም  ንኳን ለልጆቻቸው ክፉ የሚሆኑ እናቶች የሉም፡፡
እግዚአብሔር እንዴት ባለ ፍቅር ከእናታችን ጋር እንደሚያጣብቀን ስናስብ ይገርማል፡፡ የሰው መልክ አይተን ጠረን አሽትተን በማንለይበት በዚያ በጨቅላነታችን ግራና ቀኙን በማናውቅበት በዚያ የልጅነት ዘመናችን ሁሉን ላቃጥል በሚል ማስተዋላችንን በምናጣበት በዚያ የእሳትነት ዘመናችን እግዚአብሔር ከእናቶቻችን ጋር በሚደንቅ ፍቅር ባያጣብቀን ኖሮ ማን ያነሳን ነበር፡፡
በዚህ ምድር ስንኖር ሁሉም ሰው የሚወደን የሚያቀርበን የሚንከባከበን የሚያበላ የሚያጠጣን የሚያቅፈን የሚስመን መልካም፣ቸር ለጋስ፣ አዛኝ እስከሆንን ግዜ ድረስ ብቻ ነው፡፡
እናታችን ግን ባህሪያችን ጎድፎ በማህረሰቡ ተገለን በክፋትና በተንኮል ተመርዘን መድረሻ ስናጣ ሁሉ ቢኖረንም ብናጣም ትወደናለች፡፡
እንደውም በሚደንቅ ሁኔታ እናቶች መልካም በጎ አዛኝ ቅን ከሚባሉ ልጆች በላይ ልባቸው በፍቅር የሚወድቀው ነብሳቸው የምትታሰረው መጥፎ ጨካኝ አረመኔ ለሚባሉ ልጆቻቸው ነው፡፡
ይህንን ለማረጋገጥ ብዙ እሩቅ መሄድ ብዙ ማጥናት መመራመር የሚያስፈልግ አይመስለኝም አንድ ነገር ማሰብ ብቻ በቂ ነው
እናቶች በቤታቸው ቁጭ ብለው፣ ደክሟቸው  አረፍ ብለው፣ አሟቸው ተኝተው ከጎረቤቶቻቸው ጋር ቡና እየጠጡ ብቻ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነው ጩኸት ቢሰሙ ረብሻ ቢያዩ የተኩስ ድምጽ ቢሰሙ ቶሎ የሚያስቡት ልጄን ብለው የሚነሱት የሚደነግጡት ከተማ ቁጭ ብለው ክፍለ ሀገር ክፍለ ሀገር ከተማ የሚያስቡት መጥፎ ክፉ ጨካኝ ለሚባሉ ልጆቻቸው ነው፡፡
ያለ እነሱ የሚችለው ማንም የለምና ለመልካሙማ ሁሉ እናቱ ሁሉ ወንድሙ ሁሉ ዘመዱ ነው፡፡
መጥፎ በሆንንበት ግዜ ግን እናታችንም አባታችንም ወንድማችንም ዘመዳችንም እናታችን ብቻ ናት፡፡
ከዚህ ሁሉ የተነሳ እናትን ማጣት በሞት መነጠቅ እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡
ብዙዎች አቅም በሰጣቸው መጠን ስለ እናታቸው አቀንቅነዋል ገጥመዋል ለምነውበታል አሳዝነውበታል ብቻ ብዙ ብዙ ግን ይህ ሁሉ ለእናት ሲያንሳት ነው፡፡
ከጎኔም ጎኔን ኩላሊቴን
እናትን ጥሯት መድሀኒቴን
እሷም ባትኖር መቀነቷን

እረሀብ በሆዴ በቅሎ አዘረዘረ
እማምዬ ብትኖር ታጭድልኝ ነበረ
እናቴ ናፈቅሽኝ በሦስት አማርኛ
ሲርበኝ ሲጠማኝ ታምሜ ስተኛ
እናቱን የማይወድ ሰው አለ ቢሉኝ
ሰው ነው አልለውም አውሬ ነው ባይ ነኝ
እናት ለምን ትሙት ትሂድ አጎንብሳ
ጤናን ትሰጣለች በጭለማም ዳብሳ
እንዲህ እንዲህ አያለ ሁሉም የስሜቱን ቢናገርላት እውነት ነው
እማቴ ሆይ ሁሌም እወድሻለሁ ባሰብኩሽ ግዜ ሁሉ በማያቋርጥ ጥልቅ ሀዘን እመታለሁ እግዚአብሔር በዘመኑ ሁሉ እንደማይሳሳት አምናለሁና አንቺን በሰጠኝ ዘመን ሁሉ ልክ እንደሆነና እንዳመሰገንኩት ሁሉ ዛርም በሞት ሲወስድሽ ልክ ነውና አመሰግነዋለሁ፡፡
እናቴ ሆይ ሕይወትሽን አስይዘሽ ህይወት ዘርተሸብኛልና ወልደሽኛልና የእግዚአብሔርን እቅፍ እስክረዳ በእቅፍሽ አሙቀሽኛልና የእግዚአብሔርን መግቦት እስካውቅ ጡትሽን መግበሽኛልና በእግዚአብሔር ክንድ አስክደገፍ ክንድሽን ተደግፌ ቆሜአለሁና እግዚአብሔርን ማጋገር እስክችል ጌታ ሆይ ለጄን ብለሽ ለምነሽልኛልና በመጨረሻም በፍቅርና በእውቀት አሳድገሽ እግዚአብሔርን እንዳውቅ አስተምረሽኛልና  እናቴ ከልቤ አመሰግንሻለሁ፡፡
እማዬ አንቺ መልካመ እናት ባትሆኚ መልካምነትን ከማን እማረው ነበር?
እናቴ አንቺ ትሁት ባትሆኚ ስለ ትህትና ማን ይነግረኝ ነበር?
እማዬ አንቺ ዘመንሽን ሁሉ በጸሎት ባታሳልፊ እግዚአብሔር የሚለመን ሲለምኑትም የሚሰጥ ሲሰጥስ የሚመሰገን አምላክ መሆኑን ማን ይነግረኝ ነበር?
እማዬ አንቺ በእውነት ፍቅር ባትሆኚ ለእኔ ፍቅር ምንድን ነበር?
እማዬ ሞትሽን ማመን እስኪያቅተኝ በልቤ ተተክለሻል
እናት እኮ ስትታጣ ትናፍቃለች በሉ ከዚህ በኋላ በየ ወሩ እየመጣችሁ እንድታዩኝ ስትዪ ሳልረዳ አሁን በሞት ሳጣሽ ምነው በየቀኑ መጥቼ ማየት እችል እንደነበር፤ ትንሽ ነገር የሚያስደስትሽ እናቴ አሁን ብዙ ነገር በማድረግ ላስደስትሽ እችል እንደነበር ለምን ሳጣሽ ትዝ አለኝ እናቴ .. . . . . . . . እወድሻለሁ ፡፡ እናቴ ስለአንቺ ልናገረው ልተርከው የምፈልገው ይህንን ብቻ አልነበረም የልቤን ሀዘን ሀሳቤን ሁሉ እጄ ሊጽፍ አልቻለምና በዚህ ይብቃኝ፡፡
እንግዲህ ምን እላለሁ እናቴ እኔ ወደ አንቺ እስክመጣ ድረስ እግዚአብሔር በአብርሃምና በይስሀቅ እቅፍ ያኑርልኝ፡፡
አምላኬ ሆይ በዘመንህ ሁሉ ስህተት የማታውቅ አምላክ ነህና እናቴን ስትሰጠኝም ትክክል ከኔ ስትውስዳትም ትክክል ነህና ማን ይወቅስሃል በዘመኔ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፡፡