Monday, August 18, 2014

እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ ሉቃ 1 ፣ 19



   
እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ
ሉቃ 1 ፣ 19
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ተልኮ ኢየሱስ ክርስስን እንደምትወልድ ከማብሰሩ ከስድስት ወር በፊት ዮሐንስን እንደሚወል ሊያበስረው ወደ ዘካርያስ መጥቶ ነበር በመሰዊያው ፊት ተገልጦ ዮሐንስን እንደሚወልድ እና እሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንደሚያሰናዳ የነቢዩ የኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ እንደሚሔድ ሲያበስረው ዘካርያስ ግን እኔ ሸምግያለሁ ሚስቴም አርጅታለች ይህ ሊሆን እንደሚችል በምን አውቃለሁ? እያለ ለማመን በዘገየ ጊዜ መልአኩም መልሶ እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ እንድነግርህም ይህችን የምስራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር አለው፡፡
 መልአኩ እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ ሲል ምን ማለቱ ነው?
በእግዚአብሔር ፊት መቆም ማለት ምን ማለት ነው?
ለመሆኑ እግዚአብሔር በፊቱ ይቆሙ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊቱ ወዴት ነው?
መላእክትስ እንደሰው ይቆሙ ይቀመጡ ዘንድ የሚታይ የሚዘረጋና የሚታጠፍ አካል አላቸው?
እነዚህን ጥያቄዎች በትንሹ መመለስ ከቻልን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ ሲል ምን ማለቱ ነው; የሚረዳን ይመስለኛል
በመጽሐፍ ቅዱስ ፊት ማየት፣ በፊት መሄድ፣ በፊት መቆም የሚሉት ቃላት እጅግ በጣም ብዙ ትርጉሞችን ይዘው እናገኛቸዋለን
፡-ለመሆኑ እግዚአብሔር በፊቱ ይቆሙ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊቱ ወዴት ነው
እግዚአብሔር አብ  ንጽህናሽን ባበ ጊዜ ስሙ ገብርኤል የሚባል ብርሃናዊ መልአኩን ወደ አንቺ ላከ መልአኩም መንፈስ ቅዱስ  በላይሽ ይመጣል የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል አለሽ፡፡
ሉቃስ 1፤35
ይህንን ቃል በሀይማኖት የከበረ ቅዱስ አባ ህርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ላይ  መለኮት እያለ ይህንን መለኮት ስጋ እንዴት ቻለው እያለ በማድነቅ እንዲህ ይላል፡፡
ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ ሳይወሰን ጸነስሽው በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር በማህጸንሽ ተወሰነ፡፡
መመጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መለኮት በሆድሽ አደረ ፡፡
በምድራዊ እሳት እንመስለው ዘንድ አይገባም ለእሳትስ መጠን አለው ልክም አለው መለኮት ግን ይህንን ያህላል ይህንንም ይመስላል ሊባል አይቻልም፡፡
ለመለኮት እንደ ፀሐይና እንደ ጨረቃ ክበብ እንደ ሰውም መጠን ያለው አይደለም ፤ ድንቅ ነው እንጂ የሰው ህሊና የመላእክትም አእምሮ በማይደርስበት በአርያም የሚኖር ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት ወርድና ቁመት ላይና ታች ቀኝና ግራ ያለው አይደለም በሁሉ የመላ ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት  የሚዘረጋበትና የሚሰበሰብበት ያለው አይደለም ግዛቱ ባገሩ ሁሉ ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት  በላይ ጠፈር በታችም መሰረት ያለው አይደለም ጠፈሩ እርሱ መሰረቱ እርሱ ነው እንጂ ፡፡
ለመለኮት  ከምድር ከውስጥዋ የሆነውን ያነሳ ዘንድ ማጎንበስ ራስንም ዝቅ ማድረግ ያለበት አይደለም ለጴጥሮስ እንዳሳየው ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው እንጂ፡፡
ለመለኮት  በሚታይ ገንዘብ በሚወሰንም ገንዘብ ደረትና ፊት የኋላም ጀርባ ያለው አይደለም በነደ እሳት የተሸፈነ ነው እንጂ ፡፡ ነደ እሳት ግን እርሱ ነው ፡፡ መለኮትስ ንጹሕና ጽሩይ ብሩህም ነው፡፡

ስለዚህ እግዚአብሔር በፊቱ ይቆሙ ዘንድ ፊቱ ወደ እዚህ ነው የሚባል አይደለም


በፊት መሄድ በመጽሕፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ቃል መንገድ መጥረግ ማደላደል መንገድ ማቅናት የሚሉትን ሀሳቦች ሲያሟላ እናገኘዋለን፡፡
ዮሐ 10፣4 እውነት እውነት እላችኋለሁ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚመጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፡፡ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው፡፡ ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል በጎቹም ድምጹን ይሰሙታል የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወሰወዳቸዋል፡፡
የራሱንም ሁሉ ጠርቶ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሔዳል በጎቹም ድምጹን ያውቃሉና ይከተሉታል፡፡ ይልና ሐዋርያት ስለምን እንደተናገረ ባልገባቸው ጊዜ እውነት እውነት እላችኋለሁ እኔ የበጎች በር ነኝ፡፡ አላቸው ስለዚህ እውነተኛው እረኛችን ክርስቶስ በፊታችን አንደሚሄድ ሲነግረን ሞትን በመስቀሉ ጠርቆ ከመንገድ ሊያስወግደው ሞታችንን ሞቶ ነጻ ሊያወጣን ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን ሊጠራን ነው፡፡ በፊታችን መሄዱ፡፡
፡-ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሕዝበ እስራኤል ይዞ ከግብጽ ወደ ተስፋይቱ ምድረ ከነዓን  ሲጓዜ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎት ነበር፡፡
በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያስገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአኬን በፊትህ እሰዳለሁ በፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ሰለሆነ ኃጢአት ብትሰሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ ጠላቶችህን እጣላቸዋለሁ የሚያስጨንቁህንም አስጨንቃቸዋለሁ፡፡ ዘፀ 23፣20
ይለል በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሀሳብ መልአኬን በፊትህ እሰዳሁ ማለቱ መንገድህን ያስተካላል ጥረጊያውንም ያቀናል ወዳዘጋጀሁልህ ስፍራም በሰላም ያደርስሃል ማለቱ ነው፡፡
ፊት ማየት የሚለውን ብንመለከትም በቀጥታ መለመን ማለት እንደሆነ እንረዳለን በተለምዶ ወላጆች ልጆቻቸውን በችግር ሲያሳድጉ፡፡ ይህንንም ሲገልጹ የስንት ሰው ፊት አይቼ ነው ያሳደኩህ፣ ፊት ማየት ይከብዳል፣ የሰው ፊት እሳት ነው፣ የሰው ፊት ማየት አልፈልግም ሲሉ እናደምጣቸዋለን እነዚህ ሁሉ ቃላት የሚነግሩን አንድ ነገር ነው፡፡ የሰው ፊት አይቼ ለምኜ የሰው ፊት ማየት አልፈልግም መለመን አልፈልግም የሰው ፊት አሳት ነው ተቸግሮ መለመን ይከብዳል ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
ይህንን እውነታ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ማዛመድ ቢያስፈልግ  ኢዮብ 42፤9 እግዚአብሔርም የኢዮብን ፊት ተቀበለ ይለናል፡፡ ታሪኩ ከቁጥር 7 ጀምሮ የሚመጣ ሲሆን እግዚአብሔር ቴማናዊዉን ኤልፉዝን እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቁጣዬ በአንተና በሁለት ባልጀሮችህ ላይ ነድዶአል፡፡ ስለዚህም ወደ ባሪያ ወደ ኢዮብ ሔዳችሁ እንዲህና እነዲህ አድርጉ ኢዮብም ስለ እናንተ ይጸልያል እኔም እንደስንፍናችሁ እንዳለደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ፡፡ ካለ በኋላ ነው እንግዲህ እግዚአብሔርም የኢዮብን ፊት ተቀበለ የሚለው ይህም እግዚአብሔርም የኢዮብን ልመና፣ፀሎት  ተቀበለ ከማለት ውጪ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡
ማቴ 18፣ 10 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሲያስተምር እንዲህ አለ፡፡ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና፡፡ ከላይ በኢዮብ መጽሐፍ ላይ እነዳየነው ፊት ማየት መለመን ማለት ነውና ኢየሱስ ክርስቶስም ከታናናሾቹ ማንንም አትናቁ ተጠንቀቁ መላእቶቻቸው ዘወትር አባቴን ይለምኑላቸዋልና ያማልዷቸዋልና ሲል ያስጠነቅቃል፡፡
በፊት መቆም  በፊት መቆም የሚለው ቃል ወይም በእግዚአብሔር ፊት መቆም የሚለው፡፡ መለመን፣ ማስታረቅ፣ ማማለድ የሚለውን እውነት እንደሚናገር የሚከተሉትን ጥቅሶች ማየት ይቸላል
መዝ 105 ፣23 ታላቅ ነገርንም በግብጽ ድንቅንም በካራን ምድር ግሩም ነገርንም በኤርትራ ባህር ያደረገውን ያዳናቸውንም እግዚአብሔር ረሱ፡፡
እንዳያጠፋቸው ቁጣውንም ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅስፍቱ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ባይቆም ኖር እስራኤል በቅስበት በጠፉ ነበር፡፡
ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ቆመ የተባለለት ሙሴ ቃልኪዳኑን ቦት ተቀብሎ በሚመለስበት አርባ ቀን ከእግዚአብሔር ጋር በነበረው ቆይታ ህዝቡ አሮንን አስገድደው የጥጃ ምስል ሰርተው ሲያመልኩ በመቆየታቸው የእግዚአብሔር ቁጣ በላያቸው  ነደደ ብዞወችም ሞቱ በመጨረሻም ሊቀ ነቢያት ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ወጣ እንዲህመ አለ እኒህ ህዝብ ታላቅ ሀጢአትን ሰርተዋል ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፡፡ አሁን ይህን ሃጢአታቸውን ይቅር በላቸው ያለዚያ ግን እኔን ከህይወት መጽሐፍ ሰርዘኝ ፡፡ በማለቱ ነው፡፡
በመጽሐፈ ሳሙኤል 1፣1-10 የነቢዩ የሳሙኤል እናት ሃና ልጅ ባለመውለዷ የተነሳ ጣውንቷ ታበሳጫት እንደነበረ በዚህም የተነሳ ለመስዋት ከሚቀርበው አትበላም አትጠጣም ነበር ይልና ቁጥር 9 ጀምሮ እንዲህ ይላል፡፡ በሴሎ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሳች፡፡ ካህኑም ኤሊ በእግዚአብሔር መቅደስ መቃን አጠገብ በመንሩ ላይ ተቀምጦ ነበር፡፡ እርስዋም በልባ ትመረር ነበር በእግዚአብሔር ፊት ቆመች ጽኑ ልቅሶም አለቀሰች፡፡ ይለናል ሐና በእግዚአብሔር ፊት ቆመች ሲል በእግዚአብሔር ፊት ጸለየች ማለቱ ነው፡፡  

በትንቢተ ዳንኤል 12፣1 ላይ በዚያም ዘመን ስለ ህዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል  
የህዝቡ ሃጢአት እጅግ ሲበዛ ደሞ ሙሴና ኤልያስ በፊቴ ቢቆሙም እንኳን ልቤ ወደ እዚህ ህዝብ አያዘነብልም፡፡ ይላል ኤር 15፣1 ሙሴና ኤልያስ ስለዚህ ህዝብ ቢጸልዩ ጸሎታቸውን አልሰማም ማለት ነው፡፡
በመጽሐፈ ኢዮብ 1፣6 ከእለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ ሰይጣንም ደሞ በመካከላቸው መጣ፡፡ ይላል ሰይጣን የመጣው ምዕራፉን ስንጨርስ እንደምናገኘው ለመክሰስ የመጣ በመሆኑ ቆመ አልተባለም መላእክት ግን በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ ሲል ለመለመን ለምልጃ በመሆኑ ቆሙ ይላቸዋል፡፡

ስለዚህ ከላይ ያየናቸው መረጃዎች እንሚያስረዱን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፡፡ ሲል በቀጥታ እኔ ስለሰዎች እግዚአብሔርን የምለምን ነኝ ማለቱ ነው፡፡ ምክንያቱም መላእክት ቆሙ ሲባል እንደ ሰው የሚታጠፍና የሚዘረጋ የሚቆምና የሚቀመጥ አካል የላቸውምና ነው
ስለ መላእክቱም፡፡ መላእክቱን መናፍስት አገልገዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ፡፡ ዕብ 1፣7 በማለት ስለመላእክት ተፈጥሮ ይናገራል፡፡

መላእክት እንዴት ነው የሚማልዱት?  የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ፡፡ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ እነዚህ ሰባ አመት የተቆጣኻቸውን የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከመቼ ድረስ ነው፡፡ ብለው ነው ዘካ  1፣12
በተጨማሪም በአዲስ ኪዳን ስለ መላእክት ምልጃ ሲናገር ከቶ ለማን ብሎአል ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ መናፍስት አይደሉምን ዕብ 1፣14
ከዚህ በተጨማሪ ሁለት የአዲስ ኪዳን መጽሕፍት በማየት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለማላእክት አማላጅነት አንዴት እነዳስተማረ መረዳት ይቻላል

ማቴ 13፣24-28
ቁጥር 24 ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ መንግስተ ሰማያት በእርሻዉ መካክል ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች፡፡ ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላት መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ፡፡ ስንዴውም በበቀለና ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደሞ ያን ግዜ ታየ፡፡
የባለቤቶቹም ባሮች ቀርበው፡፡ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን እንክርዳዱንስ ከመዴት ተገኘ? አሉት፡፡
እርሱም ጠላት ይህንን አደረገ አላቸው፡፡ ባሮቹም እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን አሉት እርሱም ተውአቸው እንክርዳዱን ስትነቅሉ መልካሙን ስንዴ ትነቅላላችሁ እስከ መከር ይቆዩ አላቸው፡፡
ይህንን ምሳሌ በዚሁ ምዕራፍ 38 ላይ ሲያብራራላቸው ወይም ምሳሌውን ሲተረጉምላቸው
ቁጥር 36 የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጉምልን አሉት፡፡ እርሱም መልሶ አንዲህ አላቸው
፡-መልካን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፡፡ እርሻውም ዓለም ነው፡፡
፡-መልካሙ ዘር የመንግስት ልጆች ናቸው
፡-እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው
፡-የዘራዉም ጠላት ዲያቢሎስ ነው፡፡
፡-መከሩም የአለም መጨረሻ ነው፡፡
፡-አጫጆችም መላእክት ናቸው፡፡
እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚጣል በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፡፡
ቁጥር 40
ይህንን ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸውን ምሳሌ እንደያዝን ወደ ሉቃስ 13፣6 ስንሻገር ሌላ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸውን ምሳሌ እናገኛለን
ይህንንም ምሳሌ አለ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፡፡ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም፡፡
የወይን አትክልት ሰራተኛውንም እነሆ ከዚች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም ቁረጣት ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጎሳቁላለች አለው፡፡
እርሱ ግን መልሶ፡፡ ጌታ ሆይ ዙሪያዋን እስክኮተኩትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት ወደ ፊትም ብታፈራ ደህና ነው ያለዚያ ግን ትቆርጣታለህ አለው፡፡ የሚል ትምህርት እናገኛለን፡፡
ይህንን የሉቃስ ወንጌል ምሳሌ በማቴዎስ ላይ ካው ምሳሌ ጋር ስናስተያየው እንዲህ እናገኘዋለን
፡-ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት በለስ ነበረችው
፡-የወይኑ ባለቤት የሰው ልጅ/ኢየሱስ ክርስቶስ/
፡-ወይኑ የሰው ልጆች
፡-የወይን አትክልት ሰራተኛው መላዕክት
፡- የተፈለገ ፍሬ መልካም ስራ
፡- ካላፈራች እንድትቆረጥ ማለት መልካም ምግባር ሐይማኖት አልተገኘባትምና እንድትሞት የተላለፈ ፍርድ ነው
ይህችን በለስ እንዳትቆረጥ ያደረጋት የወይን ተንከባካቢው እንደሆነ ሁሉ ምግባር ከሀይማኖት ሓይማኖት ከምግባር ሳይገኝብን ቀርቶ ሞት ሲታዘዝብን ሞት ሲቆረጥብን በወይን ተንከባካቢው የተመሰሉት መላእክት በጸሎትና በምልጃ ለዚህ ዓመት ተዋቸው እያለ በምልጃ ዘመናችንን እንደሚያረዝምልን ሞትን እንደሚያሻግሩን ያስተምረናል፡፡
ከዘህ የተነሳ ነው በመላእክት አማላጅነት የምናምነው
በዓለማችን መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት አድርገው ኢየሱስ ክርስቶስን እንሰብካለን የሚሉ  በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ቤተ እምነቶች ቢኖሩም መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት በማድረግ የመላእክትን አማላጅነት የምታምን ቤተ ክርስቲያን ብትኖር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አንብባችሁ ለሌሎች ይጠቅማል ብላችሁ ካመናችሁ ሼር በማድረግ ለኁሉም አድርሱ መምህራነ ወንጌል ወንድሞቼ እና አባቶቼ ከዚህ በላይ አምልታችሁ አስፋፍታችሁ ብትጽፉት እጅግ ደስ ይለኛል ላነበባችሁልኝና አስተያይት ለምትሰጡኝ ሁሉ የከበረ ምስጋናዬን ከወዲሁ አደርሳለሁ
  

No comments:

Post a Comment