ይህንን ያለው ጸሐፊ
በእርግጥ እግዚአብሔር ሁሉም ቦታ የማይገኝ ወይም የማይኖርበት ቦታ ተገኝቶ አይደለም፡፡ ለህጻናት ግን የመጀመሪያ እግዚአብሔሮቻቸው
እናቶቻቸው ስለሆኑ ነው፡፡ ይህም እውነት ነው፡፡ ይህንን ዓለም ከመቀላቀላችን በፊት ማህጸናቸውን ዓለም አድርገው ያቆዩናል የእግዚአብሔርን
መግቦት እስክንረዳ ድረስ ጡታቸውን እያጠቡ ያሳድጉናል እግዚአብሔርን ማወቅ እስክንችል መጀመሪያ እናቶቻችንን ብቻ እናውቃለን የእግዚአብሔርን
እቅፍ እስክናውቅ በእቅፋቸው ያቆዩናል የእግዚአብሔርን ክንድ እስክንረዳ በክንዳቸው እንደገፋን ሁሉን ስናውቅ ለእግዚአብሔር ይሰጡንና
ያልፋሉ፡፡ ስለዚህም ይመስለኛል እናቶች ለልጆቻቸው የመጀመሪያ እግዚአብሔር ናቸው የሚባለው፡፡
ስለ መንፈሳዊው ዓለም
መንፈሳዊው ጸጋ ስለ ነገረ እግዚአብሔር ነገረ ድህነት ምስጢረ ስጋዌ በአጠቃላይ ስለ የምስራቹ ቃል ስለወንጌል ለመስበክ መጠራት፣
መመረጥ፣ በጸጋ መቀባት፣ በአባቶች እግር ቁጭ ብሎ መማር ይፈልግ ይሆናል፡፡ ስለ እናት ለመስበክ ግን ተወልዶ ማደግ በእናት እቅፍ
መሞቅ የእናትን ጡት ጠብቶ ማደግ ወይም ይህንን ማጣት ብቻ በቂ ነው ሰው ስላገኘውም ይሁን ስላጣው ነገር በደንብ መናገር ይችላልና፡፡
ስላገኘው ነገር በኩራት ስላጣው ነገር በቁጭት፡፡
ብዙ ግዜ አባቶች የተረሱ
እንኪመስል ድረስ እናት ለልጅ ያላትን ፍቅር ሲተረክ እንሰማለን አባቶችም ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር በኩራት ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡
ይሁን እንጂ በልጅና
በወላጅ መካከል ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ለመግለጽ እናት ለልጇ ወይም አባት ስለልጁ ከመናገር ይልቅ ልጅ በወላጁ ያለውን ጥብቅ ፍቅር
ማየት ቀላል ይመስለኛል ምክንያቱም
እናት ለልጅ ያላትን
ፍቅር መተረክ ቀላል ቢሆንም ሁላችንም ግን እኩል አንረዳዋለን ብዬ አላምንም፡፡ በምድር ላይ ብዙ እናች ቢኖሩም ሁላችንም ግን እናቶች
አይደለንም አባት ለልጅ ያለውን ፍቅር ማውራት ቢቻልም ሁሉም ሰው እኩል ስሜቱ እንዲገባው አይጠበቅም በምድር ላይ ብዙ መልካም አባቶች
ቢኖሩም ሁሉም አባቶች አይደሉምና፡፡
ነገር ግን ልጅ በእናቱ
ያለውን ጥልቅ ፍቅርና ቁርኝት ብንናገር ሁላችንም እኩል የሚገባን የምንረዳው ይመስለኝል ምክንያቱም ሁላችንም በአንድ ወቅት ለእናቶቻችን
ልጆች ነበርንና፡፡
እናት የሁሉ ነገር መሰረት
ናት እናታችን በህይወት ትኑርም በሞት ትወሰድም፣ ትክሳም ትወፍርም፣
ይመቻት ትጣም፣ ትጥቆርም ትቅላም እናትን ማወቅ ለጥሩ ህይወት ስብእና መሰረት ናት እናቱን የማያውቅ አባቱን አያውቅምና አባትን
ለማወቅ እናት መሰረት ናት ወንድምን አክስትን አጎትን በአጠቃላይ ማህበረሰቡን ለማወቅ እናትን ማወቅ ይቀድማል ፡፡
ሰው እናቱን የማያቅ
ከሆነ ጥሩ ዜጋ አይሆንም፡፡ ሰው በየትኛውም ድሎት ውስጥ ቢቀመጥ በጥሩ ቪላ ቢኖር በተሸሞነሞነ አልጋ ቢተኛ ጮማ ቢቆርጥ እናቱን
የማያውቅ ከሆነ እናቴ ማን ናት? የሚል ጥያቄ ሰላሙን ሲነሳው ምቾቱን ሲያስረሳው ይኖራል፡፡
ያለ እናት በጥሩ ቪላ
ከመኖር በደሳሳ ጎጆ ውስጥ መኖር እንደሚሞቅ ያለ እናት በትሽሞነሞነ አልጋ ከመተኛት ከእናት ጋር በመደብ ላይ ማደር እንደሚመች
ያለ እናት ጮማ ከመቁረጥ ከእናት ጋር ቆሎ መቆርጠም እንደሚያጠግብ ያለፉበት ምስክር ይሆናሉ፡፡
እናቱን የማያውቅ ቢበላ
የሚጠጋው ቢለብስ የሚያምርበት ቢናገር የሚያሳምን ቢሮጥ የሚቀድም ቢታገል የሚጥል አይመስለኝም፡፡
እናት ልጇን ወደዚህ
ምድር ስታመጣ በዓለም ላይ የመጨረሻውን መስዋእትነት ከፍላ ነው ህይወትን በህይወት አሲዛ፡፡ ብዙ እናቶች ልጆቻቸውን ለማስገኘት
ህይወታቸውን ያስይዛሉ፣ይሰጣሉ በከባድ መከራ በምጥ ይወልዳሉ፡፡
ስለምጥ ስንናገር ከላይ ለመጥቀስ እደሞከርኩት በዚህ ልዩ ጸጋ ውስጥ ያላለፍን እህቶችም ብንሆን
ወንድሞች አባቶችም ስለምጥ ከባድነት አንረዳም ስለምጥ ከባድነት መዘርዘርም ማስረዳትም ቢሆን በዚህ ጸጋ ውስጥ ባለፉ እናቶች ብቻ
ያምራልና ልለፈው፡፡
መጽሐፍ ግን የምጥን
ከባድነት ሲዘረዝር
የዚያን ግዜ መንግስት
በምንግስት ላየ ይነሳል እናት የልጇን ጩኸት አትሰማም ፍቅር በምድር ላይ ትቀዘቅዛለች ጦርን እና የጦርነት ወሬን ትሰማላችሁ ይህ
ሁሉ የምጥ መጀመሪያው ነው
ይላል እንግዲህ ለሚያስብ
ሁሉ ይህን መረዳት ቀላል ነው ይህ ሁሉ ከላይ የሰማንው የምጥ መጀመሪያ ከሆን የምጥ መካለኛው የምጥ መጨረሻይ ምን ይሆን?
እንግዲህ እናት እኛን
ወደዚህ ምድር ለማምጣት የምትከፍለው ትልቁ ዋጋ ነው ምጥ፡፡
ብዙ እናቶችም ከዚህ
የተነሳ ህይወታቸውን ያጣሉ በምድራችን ላይ ሕይወት ለማምጣት ሕይወት የሚሰጡ እናቶች ብቻ ናቸው፡፡ ክብር ይገባቸዋል፡፡
እናቶቻችን በማህራዊ
ኑሮ ከሌላው ሰው ጋር መግባባት ቢያቅታቸው እጅግም ክፉ ናቸው የሚባሉ ቢሆኑም እንኳን ለልጆቻቸው
ክፉ የሚሆኑ እናቶች የሉም፡፡
እግዚአብሔር እንዴት ባለ ፍቅር ከእናታችን ጋር እንደሚያጣብቀን
ስናስብ ይገርማል፡፡ የሰው መልክ አይተን ጠረን አሽትተን በማንለይበት በዚያ በጨቅላነታችን ግራና ቀኙን በማናውቅበት በዚያ የልጅነት
ዘመናችን ሁሉን ላቃጥል በሚል ማስተዋላችንን በምናጣበት በዚያ የእሳትነት ዘመናችን እግዚአብሔር ከእናቶቻችን ጋር በሚደንቅ ፍቅር
ባያጣብቀን ኖሮ ማን ያነሳን ነበር፡፡
በዚህ ምድር ስንኖር ሁሉም ሰው የሚወደን የሚያቀርበን
የሚንከባከበን የሚያበላ የሚያጠጣን የሚያቅፈን የሚስመን መልካም፣ቸር ለጋስ፣ አዛኝ እስከሆንን ግዜ ድረስ ብቻ ነው፡፡
እናታችን ግን ባህሪያችን ጎድፎ በማህረሰቡ ተገለን በክፋትና
በተንኮል ተመርዘን መድረሻ ስናጣ ሁሉ ቢኖረንም ብናጣም ትወደናለች፡፡
እንደውም በሚደንቅ ሁኔታ እናቶች መልካም በጎ አዛኝ ቅን
ከሚባሉ ልጆች በላይ ልባቸው በፍቅር የሚወድቀው ነብሳቸው የምትታሰረው መጥፎ ጨካኝ አረመኔ ለሚባሉ ልጆቻቸው ነው፡፡
ይህንን ለማረጋገጥ ብዙ እሩቅ መሄድ ብዙ ማጥናት መመራመር
የሚያስፈልግ አይመስለኝም አንድ ነገር ማሰብ ብቻ በቂ ነው
እናቶች በቤታቸው ቁጭ ብለው፣ ደክሟቸው አረፍ ብለው፣ አሟቸው ተኝተው ከጎረቤቶቻቸው ጋር ቡና እየጠጡ ብቻ በየትኛውም
ሁኔታ ውስጥ ሆነው ጩኸት ቢሰሙ ረብሻ ቢያዩ የተኩስ ድምጽ ቢሰሙ ቶሎ የሚያስቡት ልጄን ብለው የሚነሱት የሚደነግጡት ከተማ ቁጭ
ብለው ክፍለ ሀገር ክፍለ ሀገር ከተማ የሚያስቡት መጥፎ ክፉ ጨካኝ ለሚባሉ ልጆቻቸው ነው፡፡
ያለ እነሱ የሚችለው ማንም የለምና ለመልካሙማ ሁሉ እናቱ
ሁሉ ወንድሙ ሁሉ ዘመዱ ነው፡፡
መጥፎ በሆንንበት ግዜ ግን እናታችንም አባታችንም ወንድማችንም
ዘመዳችንም እናታችን ብቻ ናት፡፡
ከዚህ ሁሉ የተነሳ እናትን ማጣት በሞት መነጠቅ እጅግ
በጣም ከባድ ነው፡፡
ብዙዎች አቅም በሰጣቸው መጠን ስለ እናታቸው አቀንቅነዋል
ገጥመዋል ለምነውበታል አሳዝነውበታል ብቻ ብዙ ብዙ ግን ይህ ሁሉ ለእናት ሲያንሳት ነው፡፡
ከጎኔም ጎኔን ኩላሊቴን
እናትን ጥሯት መድሀኒቴን
እሷም ባትኖር መቀነቷን
እረሀብ በሆዴ በቅሎ አዘረዘረ
እማምዬ ብትኖር ታጭድልኝ ነበረ
እናቴ ናፈቅሽኝ በሦስት አማርኛ
ሲርበኝ ሲጠማኝ ታምሜ ስተኛ
እናቱን የማይወድ ሰው አለ ቢሉኝ
ሰው ነው አልለውም አውሬ ነው ባይ ነኝ
እናት ለምን ትሙት ትሂድ አጎንብሳ
ጤናን ትሰጣለች በጭለማም ዳብሳ
እንዲህ እንዲህ አያለ ሁሉም የስሜቱን ቢናገርላት እውነት
ነው
እማቴ ሆይ ሁሌም እወድሻለሁ ባሰብኩሽ ግዜ ሁሉ በማያቋርጥ
ጥልቅ ሀዘን እመታለሁ እግዚአብሔር በዘመኑ ሁሉ እንደማይሳሳት አምናለሁና አንቺን በሰጠኝ ዘመን ሁሉ ልክ እንደሆነና እንዳመሰገንኩት
ሁሉ ዛርም በሞት ሲወስድሽ ልክ ነውና አመሰግነዋለሁ፡፡
እናቴ ሆይ ሕይወትሽን አስይዘሽ ህይወት ዘርተሸብኛልና
ወልደሽኛልና የእግዚአብሔርን እቅፍ እስክረዳ በእቅፍሽ አሙቀሽኛልና የእግዚአብሔርን መግቦት እስካውቅ ጡትሽን መግበሽኛልና በእግዚአብሔር
ክንድ አስክደገፍ ክንድሽን ተደግፌ ቆሜአለሁና እግዚአብሔርን ማጋገር እስክችል ጌታ ሆይ ለጄን ብለሽ ለምነሽልኛልና በመጨረሻም በፍቅርና
በእውቀት አሳድገሽ እግዚአብሔርን እንዳውቅ አስተምረሽኛልና እናቴ
ከልቤ አመሰግንሻለሁ፡፡
እማዬ አንቺ መልካመ እናት ባትሆኚ መልካምነትን ከማን
እማረው ነበር?
እናቴ አንቺ ትሁት ባትሆኚ ስለ ትህትና ማን ይነግረኝ
ነበር?
እማዬ አንቺ ዘመንሽን ሁሉ በጸሎት ባታሳልፊ እግዚአብሔር
የሚለመን ሲለምኑትም የሚሰጥ ሲሰጥስ የሚመሰገን አምላክ መሆኑን ማን ይነግረኝ ነበር?
እማዬ አንቺ በእውነት ፍቅር ባትሆኚ ለእኔ ፍቅር ምንድን
ነበር?
እማዬ ሞትሽን ማመን እስኪያቅተኝ በልቤ ተተክለሻል
እናት እኮ ስትታጣ ትናፍቃለች በሉ ከዚህ በኋላ በየ ወሩ
እየመጣችሁ እንድታዩኝ ስትዪ ሳልረዳ አሁን በሞት ሳጣሽ ምነው በየቀኑ መጥቼ ማየት እችል እንደነበር፤ ትንሽ ነገር የሚያስደስትሽ
እናቴ አሁን ብዙ ነገር በማድረግ ላስደስትሽ እችል እንደነበር ለምን ሳጣሽ ትዝ አለኝ እናቴ .. . . . . . . . እወድሻለሁ
፡፡ እናቴ ስለአንቺ ልናገረው ልተርከው የምፈልገው ይህንን ብቻ አልነበረም የልቤን ሀዘን ሀሳቤን ሁሉ እጄ ሊጽፍ አልቻለምና በዚህ
ይብቃኝ፡፡
እንግዲህ ምን እላለሁ እናቴ እኔ ወደ አንቺ እስክመጣ
ድረስ እግዚአብሔር በአብርሃምና በይስሀቅ እቅፍ ያኑርልኝ፡፡
አምላኬ ሆይ በዘመንህ ሁሉ ስህተት የማታውቅ አምላክ ነህና
እናቴን ስትሰጠኝም ትክክል ከኔ ስትውስዳትም ትክክል ነህና ማን ይወቅስሃል በዘመኔ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፡፡



No comments:
Post a Comment