Tuesday, September 2, 2014

ስር ሰዳችሁ እደጉ



ከዚህ ቀደም ቃል በገባሁት መሰረት በ2000 ዓ.ም ካዘጋጀሁተ መጽሐፍ ላይ

ምንም እነኳን የመጽሐፉ ርእስ ክርቲያናዊ ህይወትና አስተዳደጉ የሚል ቢሆንም መጽሐፉን አዘጋጅቼ እስክጨርስ የተከተልኩት ርእስ ስር ሰዳችሁ እደጉ የሚል ነበርና በዚህ ገጽ ይህቺን የትንሽ መጽሐፌን ዝግጅት ለምታነቡ በሁለተኛው ርእስ ወይም ስር ሰዳችሁ እደጉ በሚለው ርእስ ይሁንልኝ  


7

 


መግቢያ

ይህንን ትንሽ ፅሁፍ ለመፃፍ ስነሳ ሁል ጊዜም የሚያሳስበኝን

ነገር በመጠኑም ቢሆን  ለመግለጽ አስቤ ነው፡፡ በክርስትና የሚኖሩና ምዕመናን ሁሉ በአንድነት የምንስማማበት ሁላችንም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት ተከታዮች መሆናችን እንጂ አልፎ አልፎ በተወሰኑ ሀሳቦች ላይ በቁጥራችን ልክ አስተሳሰባችን እና ውሳኔዎቻችን የተከፋፈለ በመሆኑ፤ በዚህም ምክንያት ‹‹ክርስቲያናዊ ሕይወትና አስተዳደጉ››  በሚል ርእስ ይህቺን አጭር ፅሁፍ ለማዘጋጀት ሳስብ በዚህች እምነት ያለን ሁላችንም በአንድ ቃል ፀንተን በፍቅሩ እንድንሳብ በማሰብ ብቻ ነው፡




0





የዚህን ፅሁፍ ዝግጅት ብዙ ጓደኞቼና ምሁራን እንዲያዩት ባደረግሁበት ጊዜ በዝግጅቱ ባነሳኋቸው ጥቂት ሃሳቦች ላይ ሁለት ዓይነት አስተያየት ገጥሞኛል ግማሹ ይሄ አይነካም! ድፍረት ነው፡፡ ሌላው ሃሳቡ ልክ ነውና ሊሆን ይገባዋል የሚሉ ናቸው፡፡ በዚህም አስተያየት ሰጪዎች እንዲህ በሁለት ፅንፍ ከቆሙ ምናልባትም የዚህ ዝግጅት አንባቢያንም እንዲሁ በሁለት ፅንፍ ሊቆሙ እንደሚችሉ ተሰምቶኛል፡፡ ነገር ግን የዚህ ዝግጅት አላማም ሆነ ፍላጎት በአንድ ጎራ ያሉ ምዕመናን በሁለት ፅንፍ ቆመው እንዲከራከሩና እንዲከፋፈሉ

ሳይሆን ምናልባትም በሁለት ሀሳብ የተከፈሉ ካሉ በመወያየትና በመስማማት ለአንዲቷ እናት ቤተክርስቲያን እና በክርስትና ህይወታችንም ጠንክረን ለመቆም እንድንችል ብቻ መሆኑን  መግለፅ እወዳለሁ፡፡

‹‹በክርስቲያናዊ ህይወትና አስተዳደጉ›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀችው መጽሐፍ በሦሥት ክፍሎች የተከፈለች ስትሆን ክፍል አንድ የክርስትና ህይወት ምንነትን መረዳት መስራቿን ማወቅ ጥሪን ማዳመጥና መዘጋጀትን ያካተተ ሲሆን ክፍል ሁለት ምዕመናን ለምን በክርስቲያናዊ ህይወት ስር ሰደው እንዳያድጉ ሆኑ በሚል አብይ ርዕስ ስር በመምህራንና በምዕመናን በኩል ያሉ ችግሮችን ንስሃ ለመግባት ለንስሃ የተመቻቸ ሁኔታ አለመኖር የሚሉ ሃሳቦች ሲኖሩበት ክፍል ሦሥት በአጭሩ ከላይ ለተነሱ ችግሮች ተብለው ለተጠቀሱት መፍትሄዎችን ይጠቁማል፡፡

በአጠቃላይ በክርስትና ላይ ያሉ መዛሎችንና መፍትሄዎቻቸውን ይጠቁማሉና አንባቢዎች ከዚህ በመነሳት አንብበው ለክርስትና ህይወት መጠንከር እንዲበረቱ እመኛለሁ በዚህ ዝግጅት ላይ የሚሰጠኝን አስተያየት ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡

 

 

ክፍል አንድ

1. የክርስትና ሕይወትና አስተዳደግ

      የሰው ልጅ የክርስቶስን አዳኝነት ሲያውቅና ሲረዳ ይልቁንም ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስ ለእርሱ እንደሞተና ህይወትን እንደሰጠው ሲረዳና ሲያምን እንደክርስቶስ ፈቃድና ሀሳብ ሊመላለስ ይገባዋል፡፡

      እርሱ ታላቅ የሆነ አምላክ እኛ ታናሾችን ታላቅ ሊያደርግ ታናሽ እንደሆነ ስናምን ‹‹የባርያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ በምስሉም እንደሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ›› ፊሊ 2÷7- 8

      እርሱ ንፁህ የሆነ አምላክ እኛ ያደፍነውን ንፁህ ሊያደርገን እንደኃጢያተኛ ሲቆጠርና ሲተፋበት ስንመረምር ‹‹እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ ሰለበዳልችንም ደቀቀ የደኅንነታችንም ተግሳጽ በእርሱ ላይ ነበረ›› ኢሳ 53÷ 5

 

      እርሱ አምላክ የሆነ ጌታ እኛ ሰዎችን አምላክ ለማድረግ

ሰው መሆኑን ስንረዳ ‹‹ቃልም ስጋ ሆነ ጸጋንና እውነትንም

ተመልቶ በእኛ አደረ›› ዮሐ 1÷14

 

 እርሱ ንጉስ የሆነ አምላክ እኛ ባሮችን ንጉስ ለማድረግ በባርያ መልክ ተገልጦ በበረት መተኛቱን ስናምን በእርግጥም በእርሱ ልናምን ልንመላለስና በእርሱም ላይ ስር ሰደን ልንታነጽ በመንፈሳዊ ልእልናም በኃይልና በብርታት ልናድግ ይገባናል፡፡

 

እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ ስር ሰዳችሁም በእርሱ ታነ  ቆላ 2÷6

    

በክርስቶስ ልናድግ ይገባናል ስንል እድገትን በሁለት ከፍለን ልናይ እንችላለን

 

አካላዊ እና መንፈሳዊ እድገት

      አካላዊ እድገት:- ሲባል ሰዎች ከተወለዱ በኋላ በተመጣጠነ ምግብ አጋዥነት በየጥቂቱ የሚያድጉት እድገት ነዉ በበሕቀ ልህቀ በየጥቂቱ አደገ  እንዳለ

 

      ለዚህ አካላዊ እድገታችን በቫይታሚን የበለፀጉ እና የተመጣጠኑ ምግቦች ያስፈልጉናል፡፡

 

      እነዚህን ምግቦች ከእናታችን ጡትና ከምድር ከበቀሉ እፅዋትና አዝርዕት እናገኛለን ከእናታችን ጡት የምናገኘዉን ስንመረምር እግዚያብሔር ምን ያህል ግራና ቀኙን በማንለይበትና የምንሄድበትን አይደለም የመጣንበትን በማናዉቅበት በዚያ በሕፃንነት ዘመን ያዘጋጀልንን እንረዳለን፡፡

 

     

ሕፃናት እንደተወለዱ  በአንድ ሰዓት ጊዜ ዉስጥ የሚጠቡት እንገር ብዙዎች በተለምዶ ለህፃናት የማያጠቡ ቢሆንም ለህፃኑ ግን የመጀመሪያ ህክምናዉ ነዉ፡፡ የመጀመሪያ ክትባቱ! ከዚያም በመቀጠል አንድ ህፃን እስከ ስድስት ወሩ ድረስ ከእናቱ ጡት ተመጣጣኝ የሆነ ምግብና ዉሃ ያገኛል፡፡ ያለምንም ተጨማሪ ምግብ እስከ ስድስት ወር ድረስ ከእናቱ ጡት ምግብ እንዲዘጋጅ ያደረገ እግዚአብሔር ነዉ፡፡ ህፃኑን በሚደንቅ ፍቅር ከእናቱ ጋራ የሚያጣብቅ እርሱ እግዚአብሔር ነዉ፡፡

 

       ሰዎች ለአካላዊ እድገታችን በሚጠቅም የምግብ ፍላጎት እንኖራለን፡፡ ሰዉ ታሞም ቢሆን ምግብ ይሰጠዋል፤ ለሰዉ ልጅ ኑሮ መሠረታዊና አስፈላጊ ናቸዉ የሚባሉት መጠለያ፣ ልብስ እና ምግብ ቢሆኑም እጅግ አስፈላጊዉ ምግብ ነዉ፡፡ በተለያየ የተፈጥሮ አጋጣሚ ወይም የአየር ሁኔታ ሰዉ ያለ መጠለያና ልብስ መቆየት ሲችል ያለ ምግብ ግን መቆየት አይቻለዉም ከረሃብ ሰደፍ ይሻላል እንዲል ፡፡

ይህም አካላዊ እድገት ሲሆን ለዚህ አካላዊ እድገት ስር ሰደህ እደግ አይባልለትም ምክንያቱም የተፈጥሮ ሂደት ጊዜዉን ጠብቆ የሚሄድ ነዉና፡፡

መንፈሳዊ እድገት፡- ሰዎች በእግዚአብሔር ፀጋ በመሞላት ለእግዚአብሔር ወደሚገዙበት መንፈሳዊ ልዕልና የሚያደርስ የእዉቀትና የእምነት እድገት ነዉ፡፡

 

ለዚህም መንፈሳዊ እድገት በጥምቀት ከመንፈስ ቅዱስ ከመወለድ ጀምሮ የእግዚአብሔርን ቃል /ወንጌልን/ መስማት ማስቀደስ ቅዱስ ስጋዉን ክቡር ደሙን መቀበል ለመንፈሳዊ እድገት ጠቃሚ ምግቦች ናቸዉ፡፡

 

 

     ስር ሰዳችሁ በእርሱ ታነፁ እንደተማራችሁትም በሃይማኖት ፅኑ ምስጋናም ይብዛላች ቆላ 2÷6

ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ ይህንንም አዘዉትር ለራስህም ለትምህርትህ ተጠንቀቅ ይህንንም ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለ 1ጢሞ 4÷15

 

      በእርግጥ ከእነዚህም መምረጥ ያስፈልጋል የትና እንዴት? ምክንያቱም በአካላዊ እድገታችን የተመጣጠነ ምግብ ካላገኘን ሰዉነታችን እንደሚጎዳና እንደሚጫጭ ሁሉ

በመንፈሳዊ እድገታችንም ለነፍሳችን የሚመችና የተመጣጠነ ምግብ ካላገኘን ነፍሳችን ትጫጫለች ፣መንፈሳችን ይደክማል፡፡

 

      በክስተቶች አጋጣሚ እንደተወለደች  እናትዋ የሞተችባት የበግ ግልገል ስትዳብስ ያገኘችዉን የዉሻ ጡት ጠብታ ብታድግ የዉሻ ጡት ጠብታ በማደጓ ፀጉb እንጂ ዉስÚ በግ ስላልሆነ እንደማትበላ ሁሉ ለመንፈሳዊ እድገታችን የሚያገለግለንን የመንፈስ ምግብ ከእናት ቤተ ክርስቲያን ብቻ እስካላገኘን ድረስ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ህዝብ አንሆንም፡፡

 

     

      ይህ መንፈሳዊ እድገትም ወደላይ ከማደግ በፊት ወደስር ማደግን እና ስር መስደድን ይጠይቃል፡፡

 

      እፅዋት ሲዘሩ፣ ዛፍ ሲተከል ወደ ላይ ከማደጉ፣ ግንድ ከማዉጣቱና ቅርንጫፍ ከማበጀቱ በፊት የሚያድገዉ ወደ ስር ነዉ፡፡ መጀመሪያ ስር ያበቅላል ግንድ ባወጣ ቅርንጫፍ ባበዛ ጊዜ ንፋስ ገፍቶ እንዳይጥለዉ መጀመሪያ መሰረቱን ያጠብቃል ቤትም ሲሰራ እንደዚሁ ነዉ ግድግዳ ከመቆሙ ቆርቆሮ ከመመታቱ በፊት መጀመሪያ ወደ ስር ይቆፈራል ግድግዳ በቆመ ቆርቆሮ በተመታ ጊዜ ንፋስ ገፍቶ እንዳይጥለዉ መሰረት ይጣልለታል፡፡

 

      ሥር የሌለዉ ዛፍ ዘር ይደርቃል ይጠፋል፡፡ ዘሪ ሊዘራ ወጣ ... ሌላዉም ብዙ መሬት በሌለበት  በጭንጫ ላይ ወደቀና

ጥልቅ መሬት ስላልነበረዉ ወዲያዉኑ በቀለ ­ ፀሃይም ሲወጣ ጠወለገ ሥር ስላልነበረዉ ደረቀ­   ማር 4÷6

 

      ሥር የሌለዉ ቤትም ይወድቃል የእግዚያብሔርን ቃል ሰምቶ የማያደርገዉ ቤቱን በድቡሽት ላይ የሰራ ሰዉን ይመስላል፡፡ ንፋስ ነፈሰ ቤቱንም ገፋዉ መሠረት ስላልነበረዉ ወደቀ አወዳደቁም የከፋ ሆነ$ ማቴ 7÷27 በክርስትና ህይወትም ሰዎች ሥር መስደድ እስካልቻልን ድረስ ሥር የሌለዉ  እና በጭንጫ ላይ የወደቀዉ ዘር ወይም በድቡሽት ላይ የተመሰረተዉ ቤት እጣ ይደርሰናል ፡፡

 

      ስለዚህም ሰዎች በክርስትና ህይወት ጠንክረን ለመቆየት ሥር መስደድ ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም ነዉ ሐዋርያዉ ጳዉሎስ ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነፁ ያለዉ፡፡ እንደ ቆላስየስ መልእክት ወደ ታች ማደግ ወይም ሥር ሰዶ ማደግ ሲባል በእዉቀት መበልጸግ ተምሮ ማወቅ አዉቆ ማመን ሲሆን ወደላይ ማደግ ግን ሳያዉቁትና ሳይረዱት የሚያምኑትን ሳያነቡ ያነበቡትን ሳይረዱ ለታይታ ብቻ መቸኮል ለስም ብቻ መጨነቅ ክርስቲያን፣ ሰባኪ፣ ሰንበት ተማሪ፣ ዲያቆን፣ ቄስ፣ መነኩሴ፣ ለመባል መቸኮል ወይም ያለ ጽኑ እምነት ወደዚህ መቅረብ ናቸዉ፡፡ ብዙዎች በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባል በነበሩበት ጊዜ ለድንግል ማርያም ያላቸዉን ፍቅር ሲገልፁ

ይቆዩና ኑፋቄ ሽዉ ባለባቸዉ ማግስት እመቤቴን እንደኔ የሚወዳት አልነበረም ሳይገባኝ ነዉ እንጂ እኔም እኮ ሰንበት ተማሪ፣ ዲያቆን፣ ቄስ፣ ሰባኪ፣ ዘማሪ ነበርኩ ሲሉ ይደመጣሉ ሰንበት ተማሪ ነን  የሚሉትም ከስም ክርስትና በዘልማድ ሰንበት ትምህርት ቤት ከመመላለስ  ዉጪ ዲያቆን ነኝ ባዩም ድምፁን አሳምሮ ተንስኡ ብሎ ከማዜም ያለፈ ምንም አይነት መሰረት የጣለ ዕዉቀት ስላልነበራቸው ነው፡፡

 

      መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዘሪዉን ምሳሌ ለደቀ መዛሙርቱ በፈታላቸዉ ወይም በገለጠላቸዉ ጊዜ #በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸዉ ቃሉንም ስምተዉ ወዲያዉ በደስታ ይቀበሉታል ለጊዜዉ ነዉ እንጂ በእርሱ ሥር የላቸዉም ሁሉም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያዉ ይሰናከላሉ$ ብሏል ማር 4÷18

 

 

አባቶች ለዚህ አባባል ጥሩ ምሳሌ አላቸዉ  በልጅነቱ የመነነ ክዶ ይሞታል  ይላሉ፡፡ እንዲህ ማለት ግን የእድሜን ለጋነት ለመጥቀስ አይደለም ከሚጠቡት አንደበት ምስጋናን ያዘጋጃል ይላልና፤ ኤርሚያስ እና ዮሐንስ ገና ከእናታቸዉ ማህፀን የተመረጡ ስለሆነ ምሳሌያዊ አባባሉ የዕድሜ ለጋነትን ለመግለጥ ሳይሆን የዕምነት ለጋነትን ወይም ልጅነትን ለመጥቀስ ነዉ፡፡ በቀላል አማርኛ ሳይገባዉ ወይም ሳይረዳ

የመነነ ማለት ነዉ፡፡

 

      አንዳንድ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችም እንዲሁ ያለመሰረት ባልተጠራንበት የተገኘን እንሆንና ለራሳችንም ጠፍተን ለሰዉም መሰናክል እንሆናለን፡፡ ይህንን ምዕመናን ለምን ስር መስደድ አልቻሉም በሚለዉ ርዕስ ስር በጥቂቱም ቢሆን እንመለስበታለን፡፡

 

      ወደታች ማደግ ስር መስደድ ሲሆን ይህም በዕምነት መጠንከርና በዕዉቀት መበልፀግ ናቸዉ፡፡ በዕዉቅት ማደግ ወይም መበልፀግ ለቃሉ ወደመታዘዝ የሚያመጣ መንገድ ነዉ፡፡ ለክርስትና ህይወት መሰረትና ደረጃ የሚሆኑ ሶስት ነገሮች አሉ ደረጃቸዉን ጠብቀዉ እስካልተቀመጡ ድረስ ግን መጠነኛ ችግር ያስከትላሉ፡፡ እነሱም ዕዉነት፣ ዕምነትና ስሜት ናቸዉ፡፡ 

 

 

19
 

በእምነት ላይ ብንመሰርተው፡-   ክርስቲያናዊ ህይወታችንን በእምነት ላይ ብንመሰርተዉ የሰዎች ዕምነት ብዙ ጊዜ የፀና አይደለም ዛሬ ያመንነዉን ነገ እንጠራጠራለን አንዱ ያመነዉን ሌላዉ አያምነዉም ምዕመናን ክርስቲያናዊ ህይወታቸዉን በዕምነት ላይ ከመሰረቱ በቀላል ነገር የሚረቱ ፈሪና ድንጉጥ ይሆናሉ፡፡ ይህ ማለት ግን  በእምነት ላይ ከመሰረቱ ሲባል

እምነት ወይም ማመን አያስፈልግም ለማለትና ከእምነት ለማዘግየት ሳይሆን ለቀላል ነገር በእምነት ከተገዙ፣ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ወይም ትዉፊታዊ መሰረት የሌለዉን እዉቀት እምነት አድርጎ መቀበልና ማመን ሌላዉም እንዲያምነዉ ማድረግ ለማለት ነዉ ለምሳሌ ሲጋራ የሚያጤሱትን ወይም ጫት የሚያኝኩትን ለማስተማር ጫትና ሲጋራ የበቀለዉ አርዮስ ፈርስ ላይ ነዉ ብሎ ማመንና ለማስተማር መዘጋጀት እንደ ማለት ነዉ፡፡

 

 

በስሜት ላይ ብንመሰርተው፡- በስሜት ላይ የሚመሰረት የክርስትና ህይወት ስሜት በቀዘቀዘ ቁጥር የሚቀዘቀዝ፤ ስሜት ሲግል ደግሞ የሚሞቅ ነዉ፡፡ ስላመንን የምንደሰት ሳይሆን ደስ ሲለን የምናምን እንሆናለን፡፡ ልበ እምላክ ዳዊት  ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ   ያለዉ ለዚህ ነዉ፤ደስ ስላለኝ ወደ እግዚአብሔር ቤት ልሂድ አላለም፡፡ ለዚህም ይመስላል ብዙዎቻችን ስሜታችን ሲግል በእግዚአብሔር ቤት እንሰበሰባለን ስሜታችን ሲቀዘቅዝ መልሰን እንጠፋለን

 

 

በእውነት ላይ ሲመሰረትሁል ጊዜ ክርስቲያናዊ ህይወታችን በእዉነት ላይ ሊመሰረት ይገባዋል፡፡ እዉነትን

እናምነዋለን ባመንነዉ እምነት ላይ ስሜት እንጨምራለን፡፡ እውነት ለማይናወጥ ክርስቲያናዊ ህይወት መሰረት ይጥላልና

 

ለምሳሌ-   ክርስቶስ ሰዉ መሆኑና ወደዚህ ዓለም መምጣቱ 1ጴጥ 1፣21  1ዮሐ  4፣9  ሐዋ 13፣23

- ስለሰዉ ሐጢአት መሞቱ ፣  ኢሳ 53፣5  ቆላ 2፣14 

- ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱ ሐዋ 2፣24 እውነት ነዉ ይህንን እውነት እናምነዋለን ባናምነውም እንኳን እውነትነቱ አይሻርም ‹‹ታዲያ ምንድን ነው የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን›› ሮሜ 3÷3

        ስለዚህ  እዉነት እምነትና ስሜት ለሰዉ ክርስቲያናዊ ህይወት አስፈላጊ ነገሮች ቢሆኑም ደረጃቸዉን ጠብቀዉ ካልተቀመጡ መንፈሳዊ ዝለትንና መልፈስፈስን ያስከትላሉ፡፡ በኮት ላይ ሸሚዝ በሸሚዝ ላይ ካናቴራ እንደማይሆን ሁሉ የክርስትና ህይወት መመስረት ያለበትም ሳይፋለስ እዉነት እምነትና ስሜት በተገቢው ቦታ ላይ ሆነው ነው፡፡

 

      ስለዚህ ክርስቲናዊ ህይወታችንን በእዉነት ላይ ልንመሰርት ይገባናል፡፡ይህንን እዉነት እናምነዋለን በእምነታችን ላይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ወይም ስሜት እናክልበታለን፡፡

በዚህም ህይወታችን ሥር የሰደደና የተረጋጋ ይሆናል፡፡

 

 

      ሥር ለመስደድ የተለያዩ ፀሃፍት በተለያየ መንገድ መግለፅ ቢችሉም በዚህ ፅሁፍ ግን ከዚህ እንደሚከተለዉ እንመለከታለን፡፡

 

 

No comments:

Post a Comment